መጽሐፍ ቅዱስ መሠረት የዕብራውያን ታሪክዔቦር ተወላጅ በአብርሃም (መጀመርያ አብራም ተብሎ) ይጀምራል።

ከአብርሃም እስከ ሙሴ

ለማስተካከል

እንደ ብሉይሐዲስ ኪዳን አቆጣጠር አብርሃም (አብራም) ለአዳም ፳፩ኛ ትውልድ ነው። የተወለደውም ከአርፋክስድ ወገን በከለዳውያን ከተማ በከላውዴዎን ዑር ነው። ኦሪት ዘፍጥረት 11፡31 እንደሚለው፣ ይህ አብራም ከአባቱ ከታራ ቤተሠብ ጋራ ከዑር ተነሥተው ወደ ከነዓን ይሄዱ ዘንድ በካራን አገር ተቀመጡ። ስለዚህ ዑርና ካራን የተለያዩ ቦታዎች ናቸው። የከለዳውያን ዑር የሚባለው ስፍራ በአርፋክስድ ርስት ሲሆን፣ አብርሃም የደረሰበት ሥፍራ ካራን ግን በአራም ርስት በፓዳን-አራም ወይም አራም-ናሓራይም (አራም በሁለቱ ወንዞች መካከል ወይም መስጴጦምያ) ተገኘ።

አብርሃም በዚህ ስፍራ በልማድም በዝምድናም ተሳስሮ አብሮ ተቀምጦ ሳለ እግዚአብሔር ተገለጠለትና እንዲህ ሲል አዘዘው። «ካገርህ ውጣ፤ ከዘመዶችህም ካባትህም ቤት ተለይ እኔ ወደማሳይህ ምድር ሂድ፤ ታላቅም ሕዝብ አደርግኻለሁ። ለበረከትም ትሆናለህ» (ዘፍ፡ ም፡ ፲፪፡ ቁ፡ ፩-፲።) ይህ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት ምናልባት 2119 ዓመት ግድም ነው። እንግዲህ አብርሃም በአንዱ እግዚአብሔር በቻ ለማምለክና እሱና ዘሩ ለእግዚአብሔር የተመረጡ እንዲሆኑ የተጠራበት ዘመን ነበር። ከዚህም ዘመን አስቀድሞ፣ ኦሪት ዘፍጥረትና መጽሐፈ ኩፋሌ እንደሚተርኩት፣ አሕዛብ ሁሉ እንደየኖኅ ልጆች ወገኖች ከባቢሎን ግንብ ሥፍራ ከሰናዖር ወደየአገራቸው ተበትነው ነበር። የካም ልጅ ከነዓን ግን የኩፋሌ ውላቸውን ፈርሶ ወደ ማዶ ባሕር በመርከብ ለመጓዝ ፈቃደኛ ሳይሆን በአርፋክስድ (በሴም) ርስት ተቀመጠና በልጁ ሲዶና ስም ከተማ ሠራ። በዚያው ዘመን አሕዛብ ሁሉ በስኅተት ተመርተው ወደ ጣኦት ቢዞሩም በከነዓን የተነሡት ሕዝቦች ልማድ በተለይ እግዚአብሔርን እንዳስጠላው ይላል።

አብርሃም ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ ታዘዘ ከወገኖቹ ከከለዳውያን ተለይቶ ቤተሰቡን ይዞ ወንድሙን ሎጥን፤ ከነቤተሰቡ አስከትሎ ወደ ከነዓን አገር (ዛሬ ኢየሩሳሌም ወይም ፓለስቲን ወደሚባለው) ሄዶ ተቀመጠ። በዚያም ሲኖር ከሸመገለ በኋላ ይስሐቅን ከሚስቱ ከሳራእስማኤልን ከገረዱ ከአጋር ወለደ። ነገር ግን ከገረዱ የተወለደው ወደ ፊት ለአብርሃምና ለዘሩ የተመደበውን አገርና ዕድል አይወርስም ተብሎ በእግዚአብሔር ትዕዛዝ እስማኤልን ከነናቱ አስወጥቶ ወደ ፋራን በረሓ (ዐረብ) ሰደዳቸው። ዛሬ እስላሞች ሁሉ ዓረቦች በእስማኤል በኩል የአብርሃም ልጆችና ወራሾች ናቸው ይላሉ። በተለይ ፳ኤሎች ግን በአብርሃም ልጅነት የሚመኩት በደንበኛው ልጁ በይስሐቅ በኩል የመጣውን ትውልድ በመከተል ነው። አንዳንድ ክርስቲያን ደግሞ እንደ ዮሐንስ ምጥምቁ ቃል መዳን በአብርሃም ተወላጅነት የሚሰጥ አይደለም ባዮች ናቸው። (ማቴ 3፡9፤ ሉቃስ 3፡8)

ይስሐቅም ከሚስቱ ከርብቃ ኤሳውንና ያዕቆብን ወለደ። ያዕቆብ የኤሳው ታናሽ ሆኖ ሳለ ብኵርናን በምስር ወጥ ከኤሳው ከገበየ በኋላ ዐሥራ ሁለቱን የእስራኤልን የነገድ አባቶች ወለደ። ከዐሥራ ሁለቱም አንዱ ከብንያም በላይ የመጨረሻው ልጅ ዮሴፍ ነው። በዛሬ አባቶች ዘንድ እንደ ተለመደ ትንሹን ዮሴፍን አባቱ ያዕቆብ ከሌሎቹ አብልጦ ይወደው ነበርና በዚሁ ቅናት የያዛቸው ወንድሞቹ ከምድያም በከነዓን በኩል ወደ ግብፅ ለሚሔድ ነጋዴ ዮሴፍን ሸጡት። ገዥውም ዮሴፍን ይዞ ወደ አገሩ ወደ ግብፅ ከገባ በኋላ ለጶጢፋር ሸጠው። ጶጢፋርም በቤቱ እንደ አሽከር አድርጎ አስቀመጠው። ጌታውም ለጉዳዩ ወደ ውጭ በሔደበት ሰዓት የጌታው ሚስት ለሥጋ ፈቃድ ተመኘችውና ጠየቀችው። እሱም «ጌታዬ ባያይ እግዚአብሔር ያያል» የሚል የሚያስደነግጥ መልስ ሰጠና እንቢ አላት። እሷ ግን ሳታፍር ሳትደነግጥ ለማስገደድ ልብሱን ብትይዘው ልብሱን ተወላትና ወደ ውጭ ሸሸ።

ከዚህ በኋላ ጌትዮው ከመንገድ ሲገባ «ይኸ ለአሽከርነት ያመጣኸው ዕብራዊ ካላነቅሁሽ ብሎ ስንተናነቅ ብጮኽበት ልብሱን ጥሎኝ ሔደ» ብላ አሳየችው። ጌትዮም ነገሩን ሳይመረምር የሚስቱን ቃል ብቻ በማመን ጻድቁን እንደ ኅጢአተኛ እወህኒ ቤት አገባው። ከዚህ ከወህኒ ቤት በሕልም አፈታት ምክንያት ወጥቶ ከግብፅ ንጉሥ ከፈርዖን ጋራ ተዋወቀና ባለሟል ሆነ። ቀጥሎም ዮሴፍ የንጉሡ የፈርዖን እንደራሴ ለመሆን በቃ። በዚህ ዘመን ግብፅን ይገዙ የነበሩት የመካከለኛው መንግሥት ፈርዖኖች ነበሩ።

በዚህ ዘመን በከነዓን አገር ረኃብ ተነሥቶ ነበርና፤ የሚሸመት እኽል ለመፈለግ የሸጡት ወንድሞቹ ከከነዓን ወደ ግብፅ መጡ። እሱም ወንድሞቹን ዐወቃቸው፤ የሚፈልጉትንም እኽል ሰጣቸው። የአባቱንም ሕይወት ጠይቆ ከተረዳ በኋላም ከአባታቸው ከያዕቆብና ከሚስቶቻቸው ጋራ ከከነዓን ወደ ግብፅ መጥተው እንዲቀመጡ ነገራቸው። ከዚህ በኋላ ከእግዚአብሔር ለአባታቸው ለአብርሃምና ለዘሩ የተሰጣቸውን አገራቸውን ከነዓንን ትተው ያዕቆብና ልጆቹ በድምሩ ፸ ነፍስ ሆነው ግብፅ መጥተው ተቀመጡ። ወደ ግብጽ የወረዱበት ጊዜ፣ በመጽሐፈ ኩፋሌ ሲቆጠሩ፣ ከፍጥረት 2172 ዓመታት አለፉ፣ ይህም ከክርስቶስ ልደት በፊት 1900 ዓመታት ያህል ነው። ዮሴፍ ካለፈ በኋላ፣ በአባይ ወንዝ አፍ ወይም በጌሤም ለትንሽ ጊዜ ለእጭታዊ (ለ13ኛው ሥርወ መንግሥት) ተገዥ 14ኛ ሥርወ መንግሥት ተነሣ፤ እነዚህ ከከነዓን የደረሱ ሴማዊ እረኞችና ነጋዴዎች ሲባሉ የዕብራውያን ዘመን በግብጽ ሊያብራራ ይችላል።

ከሙሴ እስከ ዳዊት

ለማስተካከል

በግብፅ ፻ ዓመት ያኽል እንደ ተቀመጡ ዘራቸው በረከተና የግብፅን መንግሥት እማሥጋት ደረሱ። ስለዚህ በበረከቱበት በመጨረሻ ጊዜ የነበረው የግብፅ ንጉሥ በእስራኤሎች ላይ በኃዘን እስኪጮሁ ድረስ አገዛዝ አጸናባቸው። ይህ ጭቆና ሙሴ በተወለደበት ሰዓት ያህል ጀመረ። እግዚአብሔር ግን ለበረከት ትሆናላችው ብሎ ለራሱ አምልኮ የመረጣቸው ሕዝቦች ናቸውና ሥቃያቸውን ተመልክቶ አዘነላቸው። ሙሴም አድጎ ወደ ምድያም ሸሽቶ የያህዌን ራዕይ በደብረ ሲና ላይ አይቶ ሕዝቡ ከግብጽ እንዲያመልጡ ታዘዘ። በሙሴም አማካይነት በልዮ ልዮ ተአምራት ከግብፅ አወጣቸው። ፈርዖኑም ከግብጽ በር ስያባርራቸው ሥራዊቱ በታላቅ ተዓምር በቀይ ባሕር ጠፋ።

የዚህ ፈርዖን መታወቂያ በሰፊ ተከረክሯል። ለምሳሌ ዳግማዊ ራምሴስ እንደ ነበር የሚያስቡ ብዙ አሉ። ሆኖም ይህ ፈርዖን የገዛ በ1200 ዓክልበ. ግድም ስለ ሆነ፣ ከዳዊት ዘመን በፊት ለእስራኤል ዘመነ መሳፍንት (በመጽሐፈ መሳፍንት) ከዘጸዓት በኋላ ጊዜው አይበቃም። በመጽሐፈ ኩፋሌ ቁጥጥር ከግብጽ ታሪክ ጋር ሲስማማ፣ ዘጸዓት የሆነው በ1661 ዓክልበ. ስለ ሆነ የጠፋው ፈርዖን መርነፍሬ አይ (ከ13ኛው ሥርወ መንግሥት) ይመስላል። በመርነፍሬ አይ ዘመን መጨረሻ፣ ዕብራውያን የወጡበት ዓመት፣ የግብጽ ኃይል እጅግ ደክሞ አንድ አሞራዊ ወገን «ሂክሶስ» ወይም 15ናው ሥርወ መንግሥት ወደ ግብጽ ስሜን ወረረ፤ እነዚህ ከከነዓን ስለ ደረሱ ብዙ ጊዜ ከእብራውያን ጋር ተደናግረዋል። ኢያሱ ወልደ ነዌ ከነዓንን እያሸነፈው፣ ሂክሶስ መላውን ግብጽ ያሸነፉ ተዋጊዎች ነበሩ፣ በ1548 ዓክልበ. ፈርዖኑ አህሞስ ሂክሶስን ከግብጽ አባረራቸው እንጂ ይህ የእብራውያን ዘጸአት አልነበረም። ለእስራኤል ወደ ፊትም የሚተዳደሩበትን ሕግ በሙሴ አማካይነት ሰጣቸው። ከዚያም በኢያሱ መሪነት የከነዓንን ነገሥታት አሸንፈው ለአባታቸው ወደ ተሰጠው ወደ ከነዓን አገር ገቡ።

በአብርሃምና በያዕቆብ ጊዜ ያንድ የትልቅ ሰው ቤተሰብ ብቻ የነበሩት አሁን ግን ከያዕቆብ እስከ ሳሙኤል ድረስ ፷፻ ዓመት በሚያኽል ጊዜ ውስጥ በርክተው በበረቱባቸው ጊዜዎች መንግሥት ለማቆም በቁ። መጽሐፈ መሳፍንት እንደሚተርክ፣ በሌሎች ወቅቶች በአረመኔ ጎረቤታቸው በአሕዛብ ጣኦታት ከተሳሳቱ በኋላ፣ አይሁዶች ለጊዜ ተገዥ ይሆኑ ነበር። በየተራ ለሶርያ፣ ለሞአብ፣ ለአሞን፣ ለምድያም ወዘተ. ይገዙ ነበር፣ እያንዳንዱም ጊዜ ዕብራውያን ወደ እግዜር በተመለሱበት ወቅት የሚያድናቸው ፈራጅ ወይም አለቃ ይልካቸው ነበር። ጎቶንያልናዖድዲቦራባራክጌዴዎንም በዚህ አይነት ነበሩ፣ የአረመኔ ሃይሎችን ያሸንፉ ነበር። በነዚህም ክፍለዘመናት በሥነ ቅርስ በተገኙት በሌሎች ታሪካዊ ሰነዶች እንደሚታወቅ፣ «ሃቢሩ» ወይም «አፒሩ» የተባለ ብርቱ ወገን ከከነዓናዊ ጎረቤቶቻቸው ጋራ ይታገሉ ነበር፤ ሆኖም የነዚህ «ሃቢሩ» መታወቂያ ለዘመናዊ ምዕራባውያንና አይሁዳውያን ሊቃውንት የ«ሚኒማሊስም» (ክህደት) ፍልስፍና ተከታዮች ስለ ሆኑ አጠያያቂ ጉዳይ ሆኗል።

ከጌዴዎን ቀጥሎ አቢሚለክ ለሦስት ዓመታት (1252-1249 ዓክልበ. ያህል) የእስራኤላውያን አምባገነን በሴኬም ተደረገ። በእርሱ አስተዳደር ግን ሃይማኖታቸው የአረመኔ ጣኦት በአልብሪት አምልኮት ሆነ። መጨረሻውም በእርስ በርስ ጦርነት ደረሰ (መሳፍንት 9)። በሚከተሉት ፈራጆች ዘመን ዕብራውያን በተለይ በገለዓድኤፍሬም ሠፈሮች ይጠቀሳሉ እንጂ መላውን አገር እንዳልያዙ ይመስላል። በ1155 ዓክልበ. ግን እንደገና ፍልስጥኤም በርቶ እስራኤልን ይገዛ ጀመር። በ1135 ዓክልበ. በፍልስጥኤማውያን ሥር እየቆዩ ሶምሶን የእስራኤላውያን አለቃ ሆነ። በ1115 ዓክልበ. ኤሊ የእስራኤል ፈራጅ ሆነ። በ1076 ዓክልበ. ፍልስጥኤማውያን ታቦትን ማረኩ፤ በሚከተለው አመት ግን ሳሙኤል አስመለሰው።

ስለዚህ በመጀመሪያ ጊዜ በነጌዴዎን፤ በነሶምሶን በመሳፍንቱ፤ ከዚያም በነኤሊ፤ በነሳሙኤል በካህናቱ ሲተዳደሩ ቆይተው በመጨረሻ እንደ ጎረቤቶቻቸው እንደ ፍልስጥኤማውያን፤ እንደ ሞዓባውያንና እንደ አሶራውያን «ንጉሥ» ይደረግልን ብለው ጠየቁና በእግዚአብሔር ፈቃድ በ1055 ዓክልበ. ሳሙኤል ሳኦል የእስራኤል ንጉሥ እንዲሆን አደረገ።

ከዳዊት እስከ ባቢሎን ምርኮ

ለማስተካከል

ከዚያም ዳዊት ቀጥሎም ልጁ ሰሎሞን ነገሠ። በዳዊትና በሰሎሞን ዘመነ መንግሥት የእስራኤል ልጆች መንግሥታቸው ታላቅ መሆኑ በሁሉ ዘንድ ታወቀ። እነዚህ የእስራኤል ዘሮች ምንም እንኳን ቀድሞ በግብፅና በሲና በረሓ በኋላም በአገራቸው በከነዓን ሳሉ አንዳንድ ጊዜ አብረው በአሉት ሕዝብ ልማድና አምልኮ እየተዋጡ ጣዖት ማምለካቸው ባይቀር ከአብርሃም ጀምሮ እስከዚህ እስከ ሰሎሞን መንግሥት ድረስ፤ ከሰሎሞን ጀምሮም እስከ ዛሬ ድረስ በአንዱ በእግዚአብሔር ያመልካሉ። በሰሎሞንም ጊዜ ለእግዚአብሔር ትልቅ ቤተ መቅደስ ተሠራ። ስለዚህ የእውነተኛው እግዚአብሔርና የነሱም የዳዊትና ይልቁንም የሰሎሞን ስም በዓለም ታወቀ። ከክርስቶስ ልደት በፊት በሺ ዓመት ላይ ንግሥታችን ንግሥተ ሳባ የሰሎሞንን ጥበብ ለማየት ወደ ይሁዳ ከተማ ወደ ኢየሩሳሌም የሔደቸው በዚህ ምክንያት ነው።

ነገር ግን ከዚያ ወዲህ የተነሡት የሰሎሞን ተከታዮች አንዳንድ ነገሥታት የጎረቤቶቻቸውን የጢሮስንና የሲዶናን የባቢሎንንም አማልክት ብኤልንና ሞሎክን እያመለኩ እግዚአብሔርን አሳዘኑት። አንዱ ንጉሥ ተነሥቶ ለጣዖት አትስገድ አታምልክ፤ የሰገድህ አንደ ሆነ በአሕዛብ እጅ ትወድቃለህ የሚለውን የኦሪትን ቃል በካህናቱና በነቢያቱ አፍ ለሕዝቡ እያስነበበ ጣዖታቱን እንዲያጠፉና ሕዝቡ እውነተኛውን እግዚአብሔርን ብቻ እንዲያመልክ ሲያደርግ፤ አንዱ ንጉሥ ደግሞ የማይታየውን እውነተኛውን እግዚአብሔርን ከማምለክ የሚታየውን ሐሰተኛውን ጣዖት ማምለክ ስለ መረጠና ሕዝቡም ስለ ተከተለው እስራኤል ከአምላካቸው ከእግዚአብሔር ተጣሉ። የውድቀታቸውም ዋዜማ ሲሆን ወደ ሁለት መከፈል ጀመሩ። ከሙሴ ጀምሮ እስከ ሰሎሞን ድረስ በ፩ መሪ ይተዳደሩ የነበሩት አሁን በሮብዓም ዘመን ወደ ሁለት ተከፈሉና ዐሥሩ ነገዶች ከኢየሩሳሌም በሰሜን በኩል ያለውን ሰማርያን ያዙ። የመጀመሪያውም ንጉሣቸው ኢዮርብዓም ሆነ። ሁለቱ የይሁዳና የብንያም ወገኖች በታችኛው በዚሁ በኢየሩሳሌም ቀርተው ለየብቻ ይተዳደሩ ጀመር። ስማቸውም የላይኛው የእስራኤል መንግሥት የታችኛው የይሁዳ መንግሥት ይባል ጀመር።

እነዚህ ወደ ሁለት የተከፈሉት መንግሥታት አንዳንድ ጊዜ እየተጣሉ እርስ በራሳቸው ሲዋጉ፤ አንዳንድ ጊዜ እየተፋቀሩ አንድ ሆነው የእስራኤልን መንግሥት ጠላት አሶርን የይሁዳን መንግሥት ጠላት ባቢሎንን ሲወጉ ብዙ ዘመን በነጻነት ቆዩ። ከዚህ ቀጥሎ ግን ነፃነታቸው በአሶርና በባቢሎን ተደምስሶ በሰማርያ ከነገሡት ነገሥታት እነአክዓብ (አሐብ) በይሁዳ ከነገሡት እነሮብዓም፤ እነምናሴ «እኔ ነኝ አምላካችሁ ከባርነት ቤት ከምድረ ግብፅ ያወጣኋችሁ፤ ከኔ በቀር ለሌሎች አማልክት አትስገዱ» ያለውን ችላ እያሉ ሞሎክንና ብዔልን እያመለኩ ስለ አስቸገሩት፤ በወሰናቸው ያሉት በእርሱ የማያመልኩት የአሶርና የባቢሎን መንግሥታት እንዲያይሉባቸው አደረገ።

ስለዚህ በሰሜን ያለውን የእስራኤልን መንግሥት አሶራውያን፤ በደቡብ በኩል ያለውን የይሁዳን መንግሥት ባቢሎናውያን በጦርነት ደመሰሱት። በሰሎሞን ጊዜ አምሮ የተሠራውም ቤተ መቅደስ ፈረሰ። የዚህ ቤተ መቅደስና የነገሥታቱም መሣሪያ ከነገሥታቱና ከሕዝቡ ጋራ በምርኮ ወደ ባቢሎን ተጋዘ። ወደ ኢየሩሳሌምም ከባቢሎን ከአሶር ከሰማሪያ ድብልቅ ዘሮች ከሰሜን፤ የኤዶምያስ ሰዎች ከደቡብ እየመጡ በየቀኑ ተሰደዱበት።

ከባቢሎን ምርኮ እስከ ኢየሱስ ልደት

ለማስተካከል

እንግዲህ እሰከ አሁን ድረስ ምንም እንኳን በየስፍራቸው የሰዎቹ መኖር የታወቀ ቢሆን ፋርሶችግሪኮችሮማውያንታናሽ እስያንና የአፍሪካን ሰሜን ወረው ገና በገናንነት አልተነሡም። ነገር ግን ከኋላ ከረጅም ጊዜ በግምት ከ፬ ሺሕ ዓመት ጀምሮ እስከ አሁን እስከ ፮ኛው መቶ ዓመት ድረስ ከክርስቶስ ልደት በፊት የታወቁም ሥልጣኔም ኃይልም ያላቸው ግብፅ፤ አሶር፤ ባቢሎን፤ ኢትዮጵያ (ናፓታ)፤ ህንድ፤ ቻይና ናቸው። ነገር ግን በኋላ የታናሽ እስያን አገሮችና ግብፅን እስራኤሎችን ጭምር ቀጥቅጦ የገዛውን በነናቡከደነጾር ጊዜ የገነነውን የባቢሎንን መንግሥት የሚጥል የፋርስ መንግሥት ተነሣ። ከፋርስ በፊት ጎረቤቱ የሜዶን (ሚድያ) መንግሥት ለጥቂት ዘመን አይሎ ነበር። እስከ ባቢሎንና እስከ አሶር እስከ ኢየሩሳሌምም ደርሶ ነበር። ፋርስንም የራሱ ግዛት አድርጎት ነበር። ነገር ግን ፋርሶች ጊዜ ሲመቻቸው ከውስጣቸው ቂሮስ የሚባለውን ብልኅ ንጉሥ ባነገሡ ጊዜ የሜዶንም የአሶርም የባቢሎንም ትልቅነት ወደ ውድቀት ማዘንበል ጀመረ።

ቂሮስ ከክርስትና በፊት በ፭፻፶ ዓመት በፋርስ ላይ ነገሠና መጀመሪያ የሜዶንን ቀጥሎ የልድያን መንግሥት አሸንፎ ያዘ። ከዚያም በናቡናኢድ ዘመነ መንግሥት ትልቁን የባቢሎንን ከተማ በ፭፻፴፰ ዓመት ከቦ አስጨነቀ። በመጨረሻም በጦር ኃይል አሸንፎ ያዘና ትልቁን የባቢሎንን ግዛት የፋርስ የአውራጃ ግዛቱ አደረገው። ከዚህ በኋላ በናቡከደናጾር ጊዜ በምርኮ የሄዱት የኢየሩሳሌም (የእስራኤል) ሹማምንት ተፈትተው ሁሉም ተሰብስበው ድል አድራጊው ቂሮስ ፊት በቀረቡና ባያቸው ጊዜ አዘነላቸው።

ስለዚህ ምርኮኞቹ ፳ኤሎች አለቆቻቸውን ዕዝራነሕምያዘሩባቤልን ይዘው በነፃነት ወደ አገራቸው ወደ ኢየሩሳሌም እንዲመለሱ ፈቀደላቸው። ከኢየሩሳሌም ቤተ መንግሥትና ከቤተ መቅደስም ተዘርፎ በባቢሎን ከተማ ለጊዜው የተገኘውን ንዋየ ቅድሳት ይዘው ሄደው የፈረሰውን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ መልሰው እንዲሠሩ አዘዛቸው። ከራሱም እርዳታ ጨመረላቸው። እስራኤሎችም ቂሮስን ተሰናብተው በሹማምንት በነዘሩባቤል በሊቀ ካህናቱም እየተመሩ በደስታ ወደ አገራቸው ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰው የከተማውንና የቤተ መቅደሱን ሥራ ጀመሩ። ሥራውንም እጅ በእጅ ብለው ቅጥሩን ሠርተው አዳረሱት። ዳሩ ግን በመካከሉ የሚያሳዝን ነገር መጣ። «እነዚህ ሰዎች ከተማቸውንና ቅጥራቸውን ሠርተው ከፈጸሙ በኋላ አይታዘዙልህም፤ የቀድሞ ታሪካቸውንም ስንመረምር አዋኪ ሰዎች መሆናቸውን ተረድተናል» ብለው ነገረ ሠሪዎችና የፋርስ መንግሥት ተመልካቾች ለንጉሡ ላኩ። ንጉሡም ምንም ደግና ብልኅ ቢሆን በእንደዚህ ያለ ዘውዱንና ገዥነቱን በሚያሠጋ ነገር መገንገኑ አይቀርምና ሥራው ይቁም የሚል ትእዛዝ አስተላለፈ። ቢሆንም በቂሮስም በዳርዮስም ጊዜ ሲከለከልም ሲፈቀድም በቀን ብዛት የኢየሩሳሌም ከተማና ቤተ መቅደስ ተሠርቶ አለቀ። ይህ ሁሉ በብሉይ ኪዳን በመጽሐፈ ነገሥትና በመጽሐፈ ዕዝራመጽሐፈ ዜና መዋዕል፤ በመጽሐፈ መቃያንና በዜና አይሁድም ተጽፏል።

የፋርስ መንግሥት በቂሮስና በነዳርዮስ ዘመን ቅልቅ የንጉሠ ነገሥት መንግሥት ሆኖ እስከ ፫፻፴፬ ዓመት ድረስ ከቆየ በኋላ በዚህ ዘመን ከመቄዶንያ (ግሪክ) ትልቁ እስክንድር ተነሥቶ ጦሩን ይዞ ከመጨረሻው ከፋርስ ንጉሥ ከዳርዮስ ፫ኛ ጋራ ተጋጥሞ አሸንፏል። እስክንድርም የዳርዮስን ጦር ካሸነፈ በኋላ የፋርስና የግዛቱ የባቢሎን የአሶር የፓለስቲን የግብፅ ባለቤት ሆኖ፤ እስከ ህንድ ወንዝ ድረስ ገፍቷል። እስክንድር በነገሠ በ፲፫ በተወለደ በ፴፫ ዓመቱ ስለ ሞተ ግዛቱን «ዲያዶክ» የሚባሉት የጦር አለቆች ተከፋፍለው እስከ ሮማውያን መምጣት ድረስ ገዝተዋል።

በፓለስቲን ያሉት እስራኤሎች ከባቢሎን ወደ ፋርስ፤ ከፋርስ ወደ ግሪክ (ከገዥ ወደ ገዥ) ከዚያም ወዲህ ቶሎሜውስ (በጥሊሞስ) በሚባሉት በግብፅ ገዥዎች ቀጥሎ ደግሞ ሴሌውሲድ በሚባሉት በሶርያ ነገሥታት ውስጥ ጥገኛም ተገዥም እየሆኑ ከክርስቶስ ልደት በፊት የሁለቱንና የአንደኛውን መቶ ዓመት ጊዜያቸውን አሳለፉ።

ቶሎሜውስና ሴሌውኩስ የሚባሉት የትልቁ እስክንድር ፪ የጦር አለቆች ነበሩ። እስክንድር ከሞተ በኋላ ቶሎሜውስ በግብፅ ነገሠና ቶሎሜይ የተባለውን፤ ሴሌውኩስ በአሶርና በባቢሎን ነግሦ ሴሌውሲድ የተባለውን ቤተ መንግሥት (ዲናስቲ) የመሠረቱ ናቸው።

ከዚህ በኋላ ሮማውያን ከኢጣሊያ ተነሥተው እነሺፒዮኔ የአፍሪካን፤ ሰሜን፤ እነማሪዮ እነቼዛሬ ኦታቪያኖ የፈረንሳዊን የኤስፓኝን የእንግሊዝን (ጋልያብሪታንያኤስጳንያን)፤ እነሲላ እነፓምፔዎ የባልካንን አገሮችና የታናሽ እስያን መንግሥታት ሲወሩ ፓምፔዎ (ዮሐንስ መደብር ፉምፍዮስ የሚለው) እንደ ኤውሮፓ አቆጣጠር በ፷፪ ዓመት ላይ ድል አድርጎ ፓለስቲንን ያዘ።

ከዚህ በኋላ በ፳፱ ዓመት ከክርስቶስ ልደት በፊት ሮማውያንን ካዩ ጁሊዎ ቼዛሬ አታቪያኖ የሚሉት በኋላ ግርማ ያለው ጠቅላይ አለቃ ለማለት «አውግስጦስ» የሚባል የማዕረግ ስም የተጨመረለት፤ እኛ ኢትዮጵያውያን በዚሁ ይዞታ አውግስጦስ ቄሳር የምንለው በሮማ ነገሠ። ከአውግስጦስ ቄሳር ንጉሥ ቀደም ብሎ በዮልዩስ ቄሳር ጊዜ በሮማ የበላይ ገዥነት ውስጥ ትልቁ ሄሮድስ የሚባለው ንጉሥ ተብሎ ከሮማ ምክር ቤት በአርባ ዓመት ከክርስቶስ ልደት በፊት ተፈቅዶ በይሁዳ (ፓለስቲን) ተሾሟል።

ሄሮድስ የኤዶምያስ ተወላጅ ነው። የኤዶምያስም ዘር ከያዕቆብ ታላቅ ወንድም ከኤሳው ትውልድ የመጣ ነው ይባላል።

ሄሮድስ በይሁዳ በነገሠ ጊዜ የግሪክና የሮማን ሥልጣኔ በአገሩ ለማስገባት ፈቃደኛ ሆነ። በሮማ የነገሠውን አውግስጦስ ቄሳርንም ከልቡ ይወደው ነበርና በቀያፉ በታች በባሕር ዳር የምትገኘዋን ከተማ አሠርቶ ለእርሱ ስም መታሰቢያ እንድትሆን ቂሳርያ ብሎ ሰየማት። በዚህ ሁሉ ምክንያት ሄሮድስ በሮማውያን ዘንድ የታመነና የተወደደ ሆኖ በፓለስቲን በንጉሥነት ብዙ ጊዜ ቆየ። እንዲሁም ምንም እንኳን ባህሪዮና ምግባሩ እንደ ወገኖቹ እንደ ኤዶምያስ ቢሆን፤ ሃይማኖቱ ወደ እስራኤል የሚያደላ ስለነበር የአይሁድን ሃይማኖትና ልማድ ያከብርና ነበርና እነሱም እርሱን ይፈሩትና ያከብሩት ነበር። ዛሬ ግን በክርስቲያኖች ዘንድ ጌታችን የተወለደ ጊዜ ንጉሥ የሚሆን ሕፃን ተወለደ ማለትን ሰምቶ ከኔ በቀር ማን ንጉሥ ሊሆን ነው ብሎ ጌታችንን አብሮ ያገኘ መስሎት ብዙ ሕፃናት በማስፈጀቱ ለወዳጁ ለሄሮድያዳ ሲል የዮሐንስ መጥምቁን ራስ በማስቆረጡ እንደ ትልቅ ጨካኝና አመፀኛ የተቆጠረ ሰው ነው።

ይህ በመጽሐፍ ቅዱስ የሚገኘው የ፳ኤሎች ታሪክ ነው።