አርፋክስድ
አርፋክስድ (ዕብራይስጥ፦ אַרְפַּכְשָׁד /አርፓክሻድ/፣ አረብኛ፦ أرفخشذ /አርፋሕሻድ/) በኦሪት ዘፍጥረት ምዕ. 10 ዘንድ የሴም ልጅና የቃይንም አባት ነው። (በዕብራይስጥ ትርጉም ግን የቃይንም ስም የለምና በቀጥታ የሳላ አባት ነው።)
በመጽሐፈ ኩፋሌ 8፡15 አማርኛ ትርጉም የሴም ልጆች ኤላም፣ «አቡር»ና አርፋክስድ ከማየ አይህ ፬ኛ አመት በኋላ ተወለዱ ሲል፣ በሌሎቹ ትርጉሞች (እንደ ግሪክ፣ ሶርያ) ግን ኩፋሌ ከዘፍጥረት ጋር በመስማማት በ«አቡር» ፈንታ «አሹር» (አሦር) አለው (ዘፍ. 10፡22)፤ አርፋክስድም በማየ አይህ ፪ኛ አመት እንደ ተወለደ (ዘፍ. 11፡10) ይላል[1]።
በኩፋሌ 8፡34 መሠረት አርፋክስድ ሚስቱን የኤላም ልጅ ሱስን ልጅ ራሱአያ አገባትና ልጁን ቃይናምን ወለደች። ቃይናም መጻሕፍት ከአባቱ ከአርፋክስድ እንደ ተማረ ይጨምራል።
በኦሪት ዘፍጥረት 11 ዘንድ፣ አርፋክስድ ቃይንምን ሲወልድ ዕድሜው 135 አመት ሆኖ ከዚያ 400 አመት በጠቅላላ 535 አመታት ኖረ። እነዚህም ቁጥሮች ከግሪኩ ትርጉም ተገኙ። በእብራይስጥ ትርጉም ግን ሳላን ሲወልድ ዕድሜው 35 አመት ሆኖ ከዚያ 403 አመት በጠቅላላም 438 አመታት ኖረ ይላል። ሳምራዊው ትርጉም እንደገና ሦስተኛ ድምር ይሰጣል፦ ዕድሜው 135 ሆኖ ሣላን ወልዶ ከዚያ 303 አመት ኖሮ በጠቅላላ 438 አመት ነው። በኩፋሌ ዘንድ ደግሞ አርፋክስድ በአመተ አለም 1310 ተወልዶ ቃይናምን በ1375 አ.አ. ወለደ።
በኩፋሌ 9፡18 መሠረት የአርፋክስድ ክፍለ ምድር ከላውዴዎንን ሁሉ እስከ «ኤርትራ ባህር» (ቀይ ባሕር) ድረስ ይጠቅልላል። ክፍሉ በምሥራቅ በኤፍራጥስ ወንዝ ይወሰናል። በውስጡም የሲና ወሽመጥና አማና አገር ይገኛሉ። በሌላ ትርጉም ሊባኖስ ደግሞ ትጠቀሳለች[2]። በ9፡26 ደግሞ የ«ክማቱሪ ደሴቶች» በአርፋክስድ ክፍል ውስጥ መሆናቸውን ይወስናል፤ በ9:10 «የከፍቱር ደሴቶች» ተብለው በሴም ዕጣ መሆናቸውን ያረጋግጣል። ፕሮፌሰር ቻርልስ ይህ ማለት የቀፍቶሪም ደሴቶች (ምናልባት ቆጵሮስና ቀርጤስ) ይሆናል በማመን ጽፈዋል።
አብራም (በኋላ አብርሃም) ከአርፋክስድ ወገን በከለዳውያን ዑር ተወለደ። በኩፋሌ 10፡24 ይህ በኬሴድ ልጅ በዑር ተሠርቶ ነበር። የሥነ ቅርስ ሊቅ ሌዮናርድ ዉሊ ይህን ከተማ በዑር ሱመር በኤፍራጥስ ምዕራብ ዳርቻ ላይ እንደ ነበር አመነ፤ የቀድሞው አይሁድና አረብ ልማድ ግን «የከላውዴዎን ኡር» በሶርያ እንደ ተገኘ ይላል።
አርፋክስድ የከለዳውያን ወገን አባት ብቻ ሳይሆን፣ በተጨማሪ የዮቅጣን፣ የእስማኤልና የያዕቆብ ቅድማያት በመሆኑ አረብ፣ ሣባ እና እስራኤል ሁሉ ከአርፋክስድ ወገን እንደተወለዱ ይባላል።
ሌላ አርፋክስድ የሚባል የሜዶን ንጉሥ በመጽሐፈ ዮዲት ሲገኝ ይህ ለታሪካዊው ሜዶን ንጉስ ስም «ሗክሻጥራ» የተሳተ ይሆናል።