ካም (ዕብራይስጥ፦ חָם /ሓም/፤ ግሪክ፦ Χαμ /ቃም/፣ ዓረብኛ፦ حام, /ሓም/) በኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ 10 መሠረት የኖኅ ልጅና የኩሽምጽራይምፉጥ፣ እና ከነዓን አባት ነበር።

ልደት ለማስተካከል

ካም የተወለደው ከማየ አይኅ አስቀድሞ እንደ ነበር ይታመናል። ኦሪት ዘፍጥረት 5፡32 እንደሚለን፣ «ኖኅም የአምስት መቶ አመት ሰው ነበረ፤ ኖኅም ሴምን ካምን ያፌትንም ወለደ።» በመጽሐፈ ኩፋሌ አቆጣጠር፣ ኖህ በዓመተ ዓለም 707 ተወልዶ፣ ሴምን በ1207 ዓ.ዓ. ወለደ፤ በ1209 ዓ.ዓ. ካምንም፣ በ1212 ዓ.ዓ. ያፌትንም ወለዳቸው። በዚህ አቆጣጠር በ1308 ዓ.ዓ. ማየ አይኅ ወይም የጥፋት ውኃ በደረሰበት ዓመት የካም ዕድሜ 99 ዓመት ያህል ነበር። በዚያ ዘመን የአበው ዕድሜ እስከ ሺ ድረስ ሊሆን ስለሚችል ይህ እንደ ወጣት መቆጠሩ ማለት ነው።

የሚስቱ ስም በዘፍጥረት ባይጻፍም በኩፋሌ ግን ስሟ ናኤልታማኡክ (ኔኤላታማኡክ፣ አኤልታማኡክ)<note> የተለያየ ስም እንደተጠራች ያመላክታል</note> እንደ ነበር ይተረካል። በሌላ ጥንታዊ ምንጮች ዘንድ ስሟ ናሐላጥ፣ ኖኤላ፣ ናሕላብ፣ ወዘተ. የሚመስል ነበር። እነዚህ ሁለቱ ከውኃው በኖህ መርከብ ያመለጠው የ8 ሰዎች ቤተሠብ መካከል ነበሩ።

የከነዓን መረገም ለማስተካከል

በዘፍጥረት 9፡20-27 አንድ ታሪክ ስለ ካም አለ። ትንሽ ከጥፋት ውኃ በኋላ ቤተሠቡ ገና በአራራት ተራራ ሲኖሩ አባቱ ኖህ ሰክሮ ካም በዕራቁትነቱ እንዳየው ይላል። ስለዚህ ኖኅ ተቆጥቶ በካም ታናሽ ልጅ ከነዓን ላይ ርጉም ጣለ። በኩፋሌ ዘንድ ይህ የሆነበት በ1321 ዓ.ዓ. ወይም መርከቡ ከቆመው 12 ዓመታት በኋላ ነበር። ካም ከዚያ ወጥቶ ከተማ በአራራት ደቡብ ገጽ በሚስቱ ስም እንደ ሠራ በኩፋሌ ይጨመራል። ከዚያ ሴምና ያፌት በሚስቶቻቸውም ስሞች ለራሳቸው ከተሞች በዙሪያው ሠሩ ይላል።

የምድር አከፋፈል ለማስተካከል

በኩፋሌ ዘንድ በ1569 ዓ.ዓ. ምድር በኖህ 3 ልጆች መካከል በ3 ክፍሎች ተካፈለች። እንዲሁም በነዚህ 3 ዋና ክፍሎች ውስጥ ለኖህ 16 ልጅ-ልጆች 16 ርስቶች ተሰጡ። ለካምና ለልጆቹ የደረሰው ክፍል ከግዮን ወንዝ ወደ ምዕራብ ያለው ሁሉ፣ ከዚያም ከገዲር ደቡብ ያለው ሁሉ ሆነ። ይህም የምድር አከፋፈል በብዙ ሌሎች ጥንታዊ ምንጮች ይጠቀሳል። ማንም የወንድሙን ርስት በግድ እንዳይዝ የሚል ተጨማሪ ርጉም እንዲኖር ተዋዋሉ።

በ1596 እስከ 1639 ዓ.ዓ. ድረስ፣ የሰው ልጆች በዝተው በሰናዖር ሰፍረው የባቢሎን ግንብ ሠሩ። በዚህ ላይ ንጉሣቸው የካም ልጅ ኩሽ ልጅ ናምሩድ እንደ ነበር በብዙ ምንጭ ይባላል። ከ1639 ዓ.ዓ. ጀምሮ የኖህ ልጆች ወገኖቻቸውን ወደየርስቶቻቸው ይወስዱ እንደ ጀመር ደግሞ በመጽሐፈ ኩፋሌ አለ። በዚህ ሰዓት ካም፣ 4 ልጆቹና ቤተሠቦቻቸው ሁሉ ከሰነዓር ወደ አፍሪቃ ወደ ድርሻቸው ይጓዙ ጀመር። ዳሩ ግን በሊባኖስ ዙሪያ ሲደርሱ ከነዓን በዚያ ቁጭ ብሎ እሱ መጀመርያ መሓላቸውን ሰበረ። ያው አገር በሴም ልጅ አርፋክስድ ርስት ስለ ነበር ነው። አባቱ ካምና 3 ወንድሞቹ መንገዱን እንዲከተል ቢለምኑትም ከነዓን እምቢ እንዳላቸው በኩፋሌ ይነባል። ካም ግን ከ3ቱ ልጆቹ ጋር እስከ አፍሪካና እስከ ግዮን ወንዝ ድረስ መንገዳቸውን ተከተሉ።

የኢትዮጵያ ልማድ ለማስተካከል

በአንድ ኢትዮጵያዊ ልማድ ዘንድ፣ ከባቢሎን ግንብ ውድቀት ቀጥሎ ካም የአገሩ መጀምርያው ንጉሥ ነበረ። ለ78 ዓመታት ገዛ፣ ከዚያም በኲሩ ኩሽ በዙፋኑ ተከተለው ይባላል። ይህ መረጃ የሚገኘው በ1919 ዓ.ም. ራስ ተፈሪ (በኋላ አጼ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ) ለጸሐፊው ቻርልስ ረይ ካቀረቡት ልማዳዊ የኢትዮጵያ ነገሥታት ዝርዝር ላይ ነው። ከዚህ ዘመን በኋላ ካም ሶርያን በወረረበት ጊዜ እንደ ተገደለ በአንዳንድ የሀገር ታሪክ ጸሐፍት ይጨመራል።

«ሐሣዊ ቤሮሶስ» በተባለው ዜና መዋዕል ለማስተካከል

1490 ዓ.ም. በጣልያናዊ መነኩሴ አኒዩስ ዴ ቪቴርቦ የታተመው «ሐሣዊ ቤሮሶስ» የተባለው ዜና መዋዕል ስለ ካም ሕይወት ብዙ ተጨማሪ መረጃ አለው። በዚህ በኩል፣ የኖህ ቤተሠብ ከመርከብ ወጥተው በአርሜኒያ ገና ሲኖሩ፣ ካም ከጥፋት ውኃ በፊት የነበረውን ክፉ አስማት ተማረ፤ ደግሞ እሱ መጀመርያው ዞራስተር የተባለው ሆነ። ሌላ ስሙ «ካም ኤሴኑስ» (ካም መረኑ) እና ሳቱርን (ክሮኖስ) እንደ ነበር ይላል። ኖህ ከጥፋት ውሃ በኋላ ሌሎችን ሕጻናት ስለ ወለደ፣ ካም ኤሴኑስ በተለይ ቀናተኛ ሆነና አባቱን ጠላው። አንድ ቀን አባቱ ኖህ በድንኳኑ ሲሰከር በእራቁቱም ሲተኛ ካም አይቶ የሟርት ዘፈን በመዘምሩ በዚህ ምታት ጠንቅ ጊዜያዊ የወንድ አለመቻል በኖህ ላይ ደረሰበት፤ ኖህም ከዚያ ለጥቂት ወራት ልጅን መውለድ አልቻለም ነበር።

በኋላ አሕዛብ ወደ ርስቶቻቸው ተበትነው ካም ወደ አፍሪካ ሔዶ፣ ከጊዜ በኋላ በግብጽና በገዢው Oceanus (ውቅያኖስ) ላይ ወረደ፣ በዚያ አስማት በማስተማሩ የሰው ልጆች መልካም ጸባይ አወከ። አሕዛብ ከተበተኑ 112 አመታት በኋላ ካሜሴኑስ ከብዙ ሕዝብ ጋራ ከአፍሪካ በጣልያን ላይ ደረሰ፤ እዚያም መንግስቱን ይዞ ወንጄል አሰተማረ። ከ25 አመት በኋላ ግን ያኑስ በጣልያ ደርሶ ካሜሴኑስ ጥፋት በማስተምር አግኝቶት ይህንን ሁኔታ ለ3 ዓመት ከታገሠ በኋላ ያኑስ ካሜሴኑስን ከጣልያን አባረረው። ካሜሴኑስም ወደ ሲሲሊያ[1] እንደ ሸሸ ይጻፋል።

በዚህ ሰዓት፣ የካም እኅት የኖህም ሴት ልጅ ሬያሊብያ ንጉሥ ሃሞን ንግስት ስትሆን ሃሞን ግን ከሌላይቱ ሴት ከአልማንጤያ ጋር ልጁን ዲዮኒስዮስን ወልዶ ሬያም በቅናት ተቆጥታ፣ ልጁን በኒሳ ከተማ በሥውር እንዲያድግ ተላከ። (ይህም ታሪክ ከጥንታዊ ግሪክ ትውፊቶች ጋር ተመሳሳይነት አለው።) ሆኖም ሬያ በቅናቷ ተይዛ ከሃሞን ለቅቃ ወጥታ ወደ ወንድሟ ወደ ካሜሴኑስ በሲኪሊያ ሄደች። ካሜሴኑስ ሕጋዊ ሚስቱን ኖኤላን (በመርከብ ያመለጠችው የአፍሪካውያን ዘር እናት) ከዚህ በፊት ትቶ ነበር፤ አሁንም ካምና እህቱ ሬያ በሲኪሊያ ብዙም ታላላቅ አይነት ሰዎች ዘር ወለዱ። ካሜሴኑስና ሬያ ከ16 'ቲታኖች' ጋር ከዚያ የሃሞንን መንግሥት ሊብያን ወረሩ፤ ሃሞንንም ከሊቢያ ወደ ክሬታ ደሴት አባረሩት። ያንጊዜ ካሜሴኑስ ወይም ካም ለግዜው የሊቢያ ንጉሥ ሆነ፤ በዚያም ሬያ ዩፒተር ኦሲሪስን ወለደችለት። ነገር ግን የሃሞን ልጅ ዲዮኒስዮስ አድጎ ከኒሳ ደርሶ የአባቱንም ቂም በቅሎ ካምንና ሬያን ከሊቢያ አባረራቸው። ዲዮኒስዮስም ልጃቸውን ኦሲሪስን ማርኮት እንጀራ-አባቱ ሆነና እሱን የግብጽ ፈርዖን እንዲሆን አደረገው።

ካምና ሬያ ግን ከሊቢያ ወደ ግብጽ በስደት ተመለሡ። በዚያ (አሕዛብ ከተበተኑት 171 ዓመታት በኋላ) አንዲትን ሴት ልጅ «ዩኖ አይጊፕቲያ» ወይም ኢሲስን ወለዱ። ካሜሴኑስ ግን ከግብጽ ወደ ባክትሪያ (በፋርስ) ሄደ፣ በዚያም ሕዝቡን በተንኮል መራቸው። አሕዛብ የተበተኑት 250 አመት ሳይደርስ፣ ካሜሴኑስ ከባክትሪያ ገስሶ በአሦር ንጉሥ ኒኑስ ላይ ጦርነት አድርጎ በዚያ ዘመቻ ግን ተገደለና ኒኑስ ራሱን አቋረጠው። የኖህ ልጅ ካም መሞት እንዲህ ነበር ዮሐንስ ዴ ቪቴርቦ ጥንታዊ ነው ብሎ ያሳተመው ዜና መዋዕል እንደሚነግረን። ይህም በ16ኛው ክፍለ ዘመን ዓ.ም. በሰፊው የሚታመን ከሆነ፣ በኋላ ግን የአውሮጳ መምህሮች ጽሁፉ በሙሉ ሓሣዊ መሆን አለበት ብለው ገመቱ።

አል-ታባሪ ለማስተካከል

የፋርስ ታሪክ ጸሐፊ ሙሐማድ ኢብን ጃሪር አል-ታባሪ በ907 ዓ.ም. ግድም በጻፈው የነቢያትና የነገሥታት ታሪክ ስለ ካም ተጨማሪ ትውፊት አለው። ይህ በጣም ግሩም ትውፊት ግን ስለ ካም ሕይወት ዘመን ነው ሊባል አይችልም። በዚህ አፈ ታሪክ ዘንድ፣ አንድ ቀን የኢየሱስ ሐዋርያት ስለ ኖህ (ኑኅ) መርከብ ምስጢራዊ መረጃ ለማወቅ ኢየሱስን ለመኑት። ኢየሱስም መልሶ ለጥቂት ጊዜ የኖህን ልጅ ካም ከሞት አነሣው። ያንጊዜ ካም እራሱ ስለ መርከቡ አንድ ትምህርት ይሰጣቸዋል። ካም በሰጣቸውም መረጃ ዘንድ፣ በመርከቡ ላይ ቆሻሻ በበዛበት ጊዜ፣ ያስወግዱት ዘንድ ኑህ በተዓምር ዐሣማዎች ከዝሆን ኩምቢ አወጣ፤ እንደገና አይጥ ያለ ፈቃድ በመርከቡ ስለ ገባ ድመትአንበሣ አፍንጫ ፈጠረ አላቸው። እነዚህ ተአምራት በቁርዓን ስለማይገኙ ግን ብዙዎቹ እስላሞች አይቀብሉዋቸውም።[2]

  1. ^ በሲሲሊያ ደሴት አሁን አቺሬያሌ በተባለው ከተማ ልማድ፣ ከተማው «ካሜሴና» ተብሎ በካሜሴኑስ (ካም) እራሱ እንደ ተመሠረተ የሚል ጥንታዊ ጽሑፍ ተቀርጾ ይገኛል። Brydone's Tour through Sicily & Malta, 1840, p. 73-74.
  2. ^ አል-ታባሪ፣ የነቢያትና የነገሥታት ታሪክ (እንግሊዝኛ)