ደጃዝማች ኪዳኔ ወልደመድኅን
ኪዳኔ ወልደመድኅን ዓርብ ሌሊት ሐምሌ ፪ ቀን ፲፱፻፯ ዓ.ም ቡልጋ በከሰም ወረዳ፤ የለጥ ቀበሌ፤ ልዩ ስሙ ቡሄ አምባ በሚባለው ሥፍራ ላይ ከናታቸው ከወይዘሮ አስካለ ደጀን እና ከአባታቸው ከቀኛዝማች ወልደመድኅን አዩደረስ ተወልደው ነሐሴ ፲ ቀን በጥምቀት ስም ኪዳነ ማርያም ተሰይመው የለጥ ቅዱስ ጊዮርጊስቤተ ክርስቲያን ክርስትና ተነሱ። አባታችው ቀኛዝማች ወልደመድኅን ትውልድ ሃገራቸው ወበሪ ሲሆን፤ በዘመኑ የታወቁ ስመጥሩ ጠበቃ ነበሩ። ከወይዘሮ አስካለም ጋር የተገናኙት ሁለቱም እወረዳው ፍርድ ቤት ኮረማሽ ለየጉዳያቸው ሄደው እንደነበር ይነገራል። ኪዳነማርያምም እስከ ፲፪ ዓመት እድሜያቸው እዚያው ቡሄ አምባ ከአያታቸው አቶ ደጀን ደብሩ ቤት እንዳደጉና የቄስ ትምህርት ቤት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን እንደተከታተሉ ተጽፏል። ከዚህ በኋላ አባታቸው ቤት እያደጉ የአማርኛና የግእዝ ትምህርት አጠናቀዋል።
አካለ መጠን ሲደርሱ በ፲፰ዓ መታቸው በ፲፱፻፳፭ ዓ.ም. አዲስ አበባ በክብር ዘበኛ ደንብ ተቀጥረው ወዲያው በንጉሠ ነገሥቱ ትዕዛዝ ከስድሳ ዘጠኝ አዲስ ወታደሮች ጋር ባሌ ተመድበው እስከ ፲፱፻፳፯ ዓ.ም ድረስ በተራ ወታደርነት ከዚያም በ ሃምሳ ዓለቃና በባሻነት ማእረግ ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ሊወር ሲመጣ በ፲፱፻፳፰ ዓ.ም በምስራቅ ደቡብ በደጃዝማች በየነ መርድ እና በጄነራል አስፋው ወልደ ጊዮርጊስ መሪነት፤ የመጀመሪያ ልጃቸው ዓለማየሁ በተወለደ በዘጠኝ ቀኑ፤ ጥቅምት ፲፩ ቀን ፲፱፻፳፰ ዓ.ም ከጎባ ወደ ኦጋዴን ዘመቱ።
በዚህ ጦር ግንባር ፱ ወራት ለበሽሊንዲ፤ ዋቢ ሸበሌ፤ እና የመሳሰሉ ሥፍራዎች ከ እነ ባላምባራስ አየለ ወልደማርያም ጋር ሆነው ጠላትን ሲከላከሉ ከርመው ወደ ጎባ ተመለሱ። ከሰኔ ፲፱፻፳፰ ዓ.ም ጀምሮ እስከ ሚያዚያ ፳፫ ቀን ፲፱፻፳፱ ዓ.ም ከአሩሲ፤ ከሲዳሞ፤ ከሐረርና ኦጋዴን ወደ ጎባ በሃይል የመጣውን የጠላት ጦር በራሳቸው መሪነት ሲዋጉ ከርመው፤ መጨረሻ ላይ ተማም ከሚባለው ሥፍራ ላይ በተካሄደው ጦርነት ላይ ማምለጥ በማይቻልበት ኹኔታ በጠላት እጅ ወደቀው ተማረኩ። ጠላትም ለአምስት ወራት በጽኑ እሥራት ከያዛቸው በኋላ፤ በጥር ወር ፲፱፻፴ ዓ.ም ጣሊያን መሳሪያ አስታጥቆ በሽፍን መኪና ከጎባ ወሊሶ አምጥቶ እስር ላይ አዋላቸው። ባሻ ኪዳኔም እዚሁ እስር ቤት እያሉ አብረዋቸው ከታሰሩት መሀል በምስጢር ቃለ መሃላ በመስጠት መቶ ሰዎች አሳብረው እዚያ ያለውን የጠላት ጦር ፈጅተው ለመሸፈት ከወሰኑ በኋላ ወደ ባላምባራስ (በኋላ ደጃዝማች) ገረሱ ዱኪ የሚላክ ሰው በማፈላለግ ላይ እያሉ ጠላት ሰምቶ ኖሮ አጥብቆ ይከታታላቸው ጀመር። ይኼን ሲገነዘቡ ነገሩን አብርደው ሲጠባበቁ ወደ ባላምባራስ ገረሱ የላኩት ብሩ የሚባለው መልክተኛ ጥር ፲፭ ቀን ፲፱፻፴ ዓ.ም በጠላት እጅ ተይዞ ቀኑን ሙሉ ሲመረመር ዋለ። ባሻ ኪዳኔም በዚያው ዕልት ከምሽቱ ፪ ሰዐት ሲሆን በቃለ መሃላ ያደራጇቸውን ሰዎች በያሉበት እየሄዱ ከነመሳሪያቸው እየሰበሰቡ ሲያከማቹ የጠላትም ዘቦች ነቅተው በተንቀቅ ተሰልፈው ይጠብቋቸው ጀመር። ባሻ ኪዳኔ ግን ወገኖቻቸውን ሸልሉ ብለው ሲያሸልሉ የጠላት ዘቦች ተደናግጠው እንዲያውም 'እነሱ ሳይተኩሱ አትተኩሱ' የሚል ትእዛዝ አስተላልፈው ይጠባበቃሉ። ባሻ ኪዳኔም በዚህ ጊዜ ቃለ መሓላ ከሰጧቸው ፻ ሰዎች ውስጥ ፶፭ ወታደር ከነመሳሪያው፤ አራት ድግን መትረየስ፤ አስር ሣጥን ጥይት፤ ስድስት ሽጉጥ ከጠላት እጅ ነጥቀው እየተታኮሱ ሲወጡ የጠላት ኃይል ሃያ ወታደርና አንድ መትረየስ ከ ሁለት ሣጥን ጥይት ጋር ብቻ ገንጥሎ ሲያስቀርባቸው የተረፈውን መሳሪያና ወታደሮች ጋር ድል አድርገው ሸፈቱ። ወዲያውም ኩሳ ኪዳነምሕረት ከሚባል ሥፍራ ላይ ከባላምባራስ ገረሱ ጋር ተገናኙ።
ከባላምባራስ ገረሱ ጋር ከተቀላቀሉ በኋላም በደንዲ፤ በሶዶ፤ በበዳቄሮ እና በመሳስሉ ሥፍራዎች አርበኝነታቸውን እስከ ጥቅምት ፲፱፻፴፩ ዓ.ም ድረስ ሲያካሂዱ ከቆዮ በኋላ በዳቄሮ ከሚባለው ሥፍራ ላይ ከ ዱካ ዳኦስታና ከ ጄነራል ናዚ ተልኬያለሁ የሚለው ሙሴ ቀስተኛ(ሴባስቲያኖ ካስታኛ) (Sebastiano Castagna) የሚባለው ሰላይ ከሦሥት ባላባቶች ጋራ መጣ። አርበኞቹም ቀደም ሲል በ፲፱፻፴ ዓ.ም ይኼው ሰላይ ወደ ባላምባራስ አበበ አረጋይ ዘንድ ሄዶ የጦሩን ኃይል ከአየ በኋላ ብዙ አርበኛ እንዳስፈጀ ሰምተው ስለነበር እነሱንም እንደዚሁ ለማስፈጀት እንደመጣ ስለተገንዘቡት ባሻ ኪዳኔ ወልደመድኅን በመውዜር ጠመንጃ ሲመቱት 'ማማ ሚያ፤ ኢጣልያ ለዘለዓለም ትኑር ለኢጣሊያ ስል ሞትኩላት' ብሎ ሲናገር በሽጉጥ ራሱን መትተው ከገደሉት በኋላ የለበሰውን ሙሉ ገበርዲን ልብስና ካፖርት እንዲሁም የ ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ን ስዕል ያለበትን የብር ሰዐትና በቅሎውን ከነኮርቻው ማረኩት። እሱም እንደተገደለ አብረውት መጥተው የነበሩት ባላባቶች ለጄነራል ናዚ አስታውቀው ኖሮ ያያ አምሥት ባታሊዮን ወታደርና ሃያ ስምንት አውሮፕላን ወደበዳቄሮ ዘምቶ ተርታውን ለሦሥት ቀን ሲከላከሉ ከቆዩ በኋላ አርበኞቹ ተሸንፈው ጠላትም የሙሴ ቀስተኛን እሬሳ አንስቶ ወሰደ። አርበኞቹም ከዚያ ሥፍራ ሸሽተው ሶዶ ላይ እንደገና ልስምንት ቀን ተዋጉ።
ባሻ ኪዳኔ ከባላምባራስ ገረሱ ጋር ከሙሴ ቀስተኛ የተማረከውን አላስረክብም በማለታቸውና በሌላም ምክንያቶች ባለመስማማታቸው፤ በኅዳር ወር ፲፱፻፴፩ ዓ.ም. አባሎቻቸውን አስከትለው ወደ ትውልድ አገራቸው ወደቡልጋ ተጉዘው በአሥራ ሁለት ቀናቸውም ቡልጋ ገቡ። እዚሁም ከፊታውራሪ ኃይለማርያም ማናህሌ እና ከፊታውራሪ ተረፈ ማናህሌ ጋር ተቀላቅለው እስከ መጋቢት ፲፱፻፴፩ ዓ.ም. ድረስ በውሽንግር፤ ጨፌ ዶንሳ ምሽግ፤ ነጭ ድንጋይ ምሽግ፤ ልዝብ ድንጋይ ከተባሉ ቦታዎች ላይ ከጠላት ኃይል ጋር ሲዋጉ ከርመው በመጋቢት ወር በሃገሩ ላይ ገብቶ በነበረው የ እንቅጥቅጥ በሽታ በጽኑ ታመው ከልዝብ ድንጋይ ምሽግና ቤቶች ነጭ ድንጋይ ጦስኝ ምሽግ ከወደምስራቅ ኮረማሽ መካከል ታመው ተኙ:: ወዲያው በሰኔ ወር ሦሥት አምባ ላይ ሰፍረው ሳሉ ጠላት በሦስት አምባ፤ በወይን አምባ እና በጦስኝ በኩል ወርዶ ሲከባቸው ባሻ ኪዳኔ ገመምተኛ ስለነበሩ መሮጥ አቅቷቸው ‘ተማረክ’ እያለ የከበባቸውን የጠላት ጦር እየተከላለከሉ ጫካ ገቡ የጠላትም ወታደሮች የገቡበት ጠፍቶባቸው ሲፈልጉ ባሻ ኪዳኔ ጎርፍ በጀለጣት ዛፍ ተንጠልጥለው ደፍጠው ሲጠባበቁ ጠላት ጫካውን በእሳት ነበልባል ግራና ቀኙን ሲያቃጥልው እሳቸው ያሉባት ሳትቃጠል ሊተርፉ ቻሉ። ከሦስት ቀንም በኋላ ጠላት ለቆ ሲሄድ ባሻ ኪዳኔ ከጅረት ወርደው ውሃ ሲጠጡ ደክመው ወድቀው ሳሉ ወንድማቸውና ሌሎች ሲፈልጓቸው በጥይት ያሉበትን አሳወቋቸውና መጥተው በቃሬዛ አዛውሯቸው፡
ከዚህ በኋላ ክረምቱን ቡልጋ ውስጥ በነጭ ድንጋይ፤ ፍልፍል አፈር፤ ጦስኝ ምሽግ፤ በመስኖ ከነደጃዝማች ኃብተ ሥላሴ በላይነህ፤ ከነፊታውራሪ በለጠ ሳሴና ፊታውራሪ አጎናፍር ሌሎችም ስመጥሩ የቡልጋ ልጆች ጋር ሆነው ጠላትን ሲያጠቁና ሲከላከሉ ቆይተው በመስከረም ፲፱፻፴፪ ዓ.ም በሰገሌ በኩል ተጉዘው ገሊላ ከሚባል ሥፍራ ላይ ከራስ አበበ አረጋይ ጋር ሲቀላቀሉ ባሻ ኪዳኔ የግራዝማችነት ማዕረግ ተሾሙ። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ከ”ጊዲዮን ፎርስ” (Gideon Force) ጋር ወደጎጃምና ወደጎንደር እስከዘመቱ ፲፱፻፴፫ ዓ.ም ድረስ ከራስ አበበ ጋር ጠላትን በየቦታው ሲዋጉ በአርበኝነት ቆዩ። ከብዙ ከተለያዩ ውጊያዎችና ጀብዱዎች በኋላ በየካቲት ፲፱፻፴፫ ዓ.ም መሶቢት ከሚባለው ቦታ ላይ በመሪነት የጠላትን ጦር ድል አድርገው ወደዋናው ሰራዊት ከተቀላቀሉ በኋላ ራስ አበበ የቀኛዝማችነት ማዕረግ ሾሟቸው።
የሰሜን ዘመቻ
ለማስተካከልቀኛዝማች ኪዳኔ በ፲፱፻፴፫ ዓ.ም ዳውንት፤ ተንታ፤ ደብረታቦር ላይ የሰፈረውን የጣሊያን ወታደሮች ከጓደኞቻቸው ጋር እየማረኩ በመስከረም ፲፱፻፴፬ ዓ.ም ጉማራ ላይ ከፍ ያለ ውጊያ አድርገው ጠላትን ድል አደረጉ።
ኅዳር ፲፪ ቀን ፲፱፻፴፬ ዓ.ም ከጎንደር ወደ ቁልቋል በር ላለው የጠላት ጦር ስንቅ ሊያቀብል ከባድ መኪና፤ ታንክና መድፍ ጭኖ የመጣውን ኃይል ገጥመውት አሸንፏቸው ስንቁን አቀብሎ ሲመለስ እንደገና አጥቅተው ብዙ ባንዳዎች ገደሉ።
ኅዳር ፲፰ ቀን ፲፱፻፴፬ ዓ.ም ጎንደር ከተማ ውስጥ ጄነራል ናሲ ከብዙ ሺህ ሰራዊት ጋር አካባቢውን በሽቦ አጥሮ በሽቦው ውስጥና ውጭ ፈንጂ ቦንብ ከምሱሩን ነቅሎ ቀብሮበት ሳለ፡ በእንግሊዛዊው ማጆር ዳግላስ መሪነት ቀኛዝማች ኪዳኔ ይኼንኑ የተቀበረ ቦንብ በመቀስ እየቆረጡ ሌሊቱን ተጉዘው ምሽጉ ሲደርሱ ከበው ሲነጋ ተኩስ ተከፈተ። ጠላትም ከከፍተኛ ተራራ ላይ ወደታች ወደነ ቀኛዝማች ኪዳኔ በቦንባርድና ከባድ መትረየስ ሲያጠቃቸው በተራራው ሥር ሥር አድርገው ወደ ጎንደር ከተማ የሚወስደውን መንገድ ላይ ሲደርሱ ከጎንደር ከተማ የሚመጡ አስመስለው ከኋላው በጨበጣ የጅ ቦንብ እየጣሉ ብዙ ወታደሮች ፈጁ። እንዲሁም ሦስት ቦንባርድና ስድስት የውሐ መትረየስ ማርከው ምሽጉን አስለቅቀው ከያዙ በኋላ ጀነራል ናሲ ወዳለበት ወደጎንደር ቀጠሉ። ጎንደርም ሲገቡ በአሶ ቤተክርስቲያን ምሽግ በኩል ፋሲል ግንብ ምሽግ ሲደርሱ ምሽጉን ለመድፈር የጅ ቦንብ ምሽጉ ላይ በብዛት ሲጥሉ ጠላት ተሸንፎ የሰላም ባንዲራ አውጣ። በዚህ ጊዜ ቀኛዝማች የጠላትን ወታደሮች ለመማረክ ሲጠጉ የነቀሉትን የጅ ቦንብ እረስተውት ኪሳቸው ከተቱ። ወዲያው አራት መቶ ሰማንያ አራት (፬፻፹፬) ነጮች በጃቸው ተማርከው በከተማው የሚገኙትን የዓረብ ተወላጆች ሱቅና ገንዘብ እንዳይዘረፍ በወታደር አስጠብቀው ከምሽቱ ሁለት ሰዐት ላይ ተማራኪዎቹን ለ ማጆር ዳግላስ አስረክበው እረፍት ሲያደርጉ ቀን በ ዘጠኝ ሰዐት ገደማ የነቀሉት ቦንብ ከምሽቱ ሁለት ሰዐት ላይ ከኪሳቸው ላስቲኩ ተነቅሎ ሳይፈነዳ ተወርውሮ ሲጣል ፈነዳ።
የጎንደርም ጦርነት ኅዳር ፲፱ ቀን ፲፱፻፴፬ ዓ.ም ተፈጽሞ ባራት ቀኑ አልጋወራሹ መጥተው ወዲያው ከሳቸው ጋር ወደወሎ ጠቅላይ ግዛት እንዲሄዱ ተደርጎ እዚያው ብዙ ወታደርና መሳሪያ ለመከላከያ ሚኒስቴር አስረከቡ።
የካቲት ፲፰ ቀን ፲፱፻፴፬ ዓ.ም የፊታውራሪነት ማእረግ ተሰጥተው መጀመሪያ በ ወረዳ አስተዳዳሪነት ከዚያም በ፲፱፻፴፮ ዓ.ም የየጁ፤ የዋድላ ደላንታ፤ የመቂት፤ የሸደሃና የዳውንት ብሔራዊ ጦር አዛዥና የጠቅላይ ግዛቱ ጦር አማካሪ ከዚያም እስከ ፲፱፻፵፫ ዓ.ም ድረስ በወሎና በከፋ ውስጥ አውራጃ አስተዳዳሪነት ተመድበው ሲያገለግሉ ቆዩ።
ከፋ ውስጥ እንደተሾሙ (፲፱፻፵፫ ዓ.ም) ከጠቅላይ ገዢው ጋር ባለመስማማታቸው ተሽረው ንጉሠ ነገሥቱ ከስልጣን እስከወረዱ ድረስ በእስራትና በግዞት ሐያ ሦስት ዓመት ሙሉ ለሃገሩ እንዳልተጋደለ፣ በአርበኝነት ደሙን እንዳላፈሰሰ፣ ለኢትዮጵያ ነጻነት መስዋዕት እንዳልሆነ ተቆጥረው፣ ንጉሠ ነገሥቱ ለቅርብ ሎሌአቸው አድልተው ደጃዝማች ኪዳኔን ከሀገር አገልግሎት አስወገዷቸው።
ንጉሠ ነገሥቱ ከስልጣን ከወረዱ በኋላ ክቡር ደጃዝማች ኪዳኔ በመላ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ሊቀመንበርነት ተመርጠው ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ ሃገራቸውንንና ማኅበሩን ወክለው ሮማ ላይ በተካኼደው የዓለም አቀፍ ጸረ ኑክሊየር መሣሪያ ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ ሲጓዙ መስኮብ (Moscow) ላይ ጥቅምት ፱ ቀን ፲፱፻፸፪ ዓ.ም. በተወለዱ በስልሳ አራት ዓመታቸው አረፉ። ቀብራቸውም መንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ጥቅምት ፲፭ ቀን ፲፱፻፸፪ ዓ.ም. ተከናውኗል።
ክቡር ደጃዝማች ኪዳኔ ወልደመድኅን በ ፲፱፻፵፱ ዓ.ም. በተወለዱበት አጥቢያ በቡልጋ የየለጥ ቅዱስ ጊዮርጊስን ቤተ ክርስቲያን በግል ያሠሩ ሲሆን፤ በ ፲፱፻፷፬ ዓ.ም ."ከልደት እስከ ሞት" የተባለች አጭር ኃይማኖታዊ፤ መንፈሳዊና የፍልስፍና መጽሐፍ ደርሰው አሳትመዋል።
የኒሻኖቻቸው ዝርዝር
ለማስተካከል- የዳግማዊ ምኒልክ ኒሻን ባለአምበል
- የአርበኝነት ሜዳይ ከ ፬ ዘንባባ ጋር
- የድል ኮከብ
- የቅዱስ ጊዮርጊስ የከፍተኛ ጀብዱ ሜዳይ ከ ፩ ዘንባባ ጋር
- የኢትዮጵያ የክብር ኮከብ ታላቅ መኮንን ከደረት ኮከብ ጋር
- ከእንግሊዝ መንግሥት የአፍሪቃ ኮከብ
- ከእንግሊዝ መንግሥት የአፍሪቃየድል ሜዳይ
- ከሶቪዬት ሕብረት ሦስት ኒሻኖች
በጠቅላላው ፲ ኒሻኖችን ተሸልመዋል።
ዋቢ ምንጮች
ለማስተካከል- የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር የታሪክ መዝገብ - ታህሣሥ ፲፰ ቀን ፲፱፻፸ ዓ.ም