ኮረማሽ
ኰረማሽ በአማራ ክልል ውስጥ፤ በሰሜን ሸዋ በ 9°13′ ሰሜን ኬክሮስ እና 39°18′ ምሥራቅ ኬንትሮስ ላይ የምትገኝ ወረዳ ናት።
ኮረማሽ | |
ከፍታ | 2658 ሜትር (8724 ጫማ) |
ከአዲስ አበባ በምሥራቅ በኩል ሰማንያ አምሥት ኪሎሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ሥፍራ ስትሆን፣ በ ‘ስምጥ ሸለቆ’ (Rift Valley) ምሥራቃዊ ፍንጭ አናት ላይ ያላት ገዥ ይዞታ ከአፋር (የቀድሞው አዳል) እና ከሶማሌ በኩል በታሪክ ዘገባ ይመነጩ የነበረቱን እስላማዊ አጥቂዎች ለመከላከል የተመቸች ቦታ በመሆኗ የተመሠረተች ጥንታዊ ምሽግ ናት። ከፊት ለፊትዋ የመገዘዝ ተራራ፤ እንኮይ፤ ሰንበሌጥ፤ ቡልጋ እና ወደ ምሥራቅ የደረቂት እና አማሪት ወንዞች ከከሰም ወንዝ ጋር ሲቀላቀሉ እንዲሁም የመስኖ ዘንባባ ተራራ እና የመስኖ ማርያም ቤተ ክርስቲያን፤ ሜዳማው የሾላ ገበያ ወደደቡብ ምሥራቅ ደግሞ ከማዶ የክርስቶስ ሰምራ ትውልድ አገር እና ምንጃር ቁልጭ ብለው ይታያሉ።
የአካባቢው ቃለ ታሪክ ሥፍራዋ በዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ አያት ንጉሥ ሣህለ ሥላሴ እንደተመሠረተች ሲያረጋግጥ፤ የልጅ ልጃቸው ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ ደግሞ የሸዋ ንጉሥ በነበሩ ጊዜ እስካሁን ድረስ ያለውን ታላቅ የመሣሪያ ምሽግ እና በግቢው ውስጥ ያሉትን አሥራ አንድ ቤቶች እንዳሠሩ ብዙ የጽሑፍና የቃል ታሪኮች እንዲሁም ሕንጻዎቹ እራሳቸው ምስክር ናቸው። ከነኚህ አሥራ አንድ ሕንጻዎች ሁለቱ በ ፲፱፻፸፯ ዓ/ም በሉተራን ኃይማኖታዊ ተልዕኮ ልገሣ ታድሰው የ ጥራ ጥሬ እና የ እህል ምርት ማከማቻ ጎተራ ሆነዋል። ሌሎቹ ቤቶች የወረዳው ፍርድ ቤት፤ የቤተ ክህነት ጽ/ቤት ፤ የወረዳው የፖሊስ ጽ/ቤት እና የመሳሰሰሉ መንግሥታዊ ቢሮዎችን ይዘዋል።
በጥቅምት ወር ፲፱፻፱ ዓ/ም አዲስ በተመሠረተው የንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ እና የራስ ተፈሪ መኮንን መንግሥት ላይ ጦርነት አውጀው ከወሎ የዘመቱትን የልጅ እያሱ አባት ንጉሥ ሚካኤልን ሊከላከል የተሰለፈው የፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ሠራዊት ጥቃቱን ያደራጀው እዚሁ ኮረማሽ ላይ ሲሆን፡ ኋላም ዓርብ ጥቅምት ፲፯ ቀን ራስ ተፈሪና ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ሰገሌ ሜዳ ላይ ንጉሥ ሚካኤልን ድል ያደረጉት ከዚሁ ደጀን ቦታ ነው።[1]
በዚች ወረዳ ውስጥ ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ ያስገነቡት የቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ይገኛል።
በ፳፻፩ ዓ/ም ከ ዓለም ባንክ በተገኘ ብድር የኤሌክትሪክ መሥመር ተዘርግቶ ለዚች መንደርና ለአካባቢው የቡልጋ ሕዝብ የልማት መስፋፊያ ጮራ ተገልጾለታል።
በዘመናዊ መልክ የተገነባው የየለጥ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በተመረቀበት ዋዜማ፣ ጥቅምት ፳፩ ቀን ፳፻ ዓ.ም ከሐሙስ ገበያ እስከ ኮረማሽ ድረስ ባለው የአሥራ ሦስት ኪሎ ሜትር የጥርጊያ መንገድ ላይ በሳምንት ሁለት ጊዜ፤ ማለትም ሐሙስ እና ቅዳሜ ለገበያ የሚያመች የሕዝብ መመላለሻ የአውቶቡስ መሥመር አገልግሎቱን ጀምሮ፣ በተለይም ቆለኞቹ ምርታቸውን ወደ ገበያ በማቅረብ ላይ የነበረባቸውን የእግር ጉዞ እንግልት ቀንሶላቸዋል። ወደፊትም ገብያቸውን ሐሙስ ገበያ ድረስ ከመሄድ እዚችው ኰረማሽ ላይ ለመመሥረት ተስፋ ሰጥቷቸዋል። ለ የለጥ ቅዱስ ጊዮርጊስም ምረቃ ሥነ ስርዐት የተጓዙ እንግዶች በዚሁ የአውቶቡስ አገልግሎት ከሐሙስ ገበያ እስከ ኮረማሽ ድረስ ቢያንስ የሦስት ሰዐት የእግር ጉዞ ቀርቶላቸዋል።
ዋቢ ምንጮች
ለማስተካከል- (English) The Ethiopia Heritage Trust, ‘Twenty One-Day Trips From Addis Abeba (1997)
- ^ "ተፈሪ መኮንን - ረዥሙ የሥልጣን ጉዞ"፤ ዘውዴ ረታ፡ ሦስተኛ እትም ሐምሌ 1999 ዓ.ም.