ወሎ
ወሎ የሀይማኖት፣ የጥበብና የጀግንነት እንዲሁም የዉበትና የብዝሃነት አምባ ነዉ ስንል እንዲሁ አይደለም።
ወሎ የኢትዮጵያ አራቱ የዜማ ቅኝቶች አምባሰል፣ ባቲ፣ ትዝታና አንቺሆዬ ዜማዎች ፍለቂያ የጥበብ ምድር ስለሆነች ነዉ። በተጨማሪም ወሎ የበርካታ ከያንያንና ፃህፍት መፍለቂያ ፣ የጥበበኞች ምድር ናት።
ወሎ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ብዝነት እንዲሁም የአንድነትና የመቻቻል ማሳያ ድንቅና ቅድስት ምድር ናት። የወሎ ምድር የክርስትናና የእስልምና ሃይማኖቶች የየራሳቸዉን የደመቀ ታሪክ ጠብቀዉ አንድ አካል አንድ አምሳል ሆነዉ የሚኖሩበት ቅድስት ምድር ነዉ።
የኦርቶዶክስ ክርስትና እና የእስልምና ሃይማኖቶች ከፍታን የሚገትፁ ድንቅዬና ብርቅዬ የአምልኮ ቦታዎችና የአስተምህሮ ባለቤቶች የሚገኙባት ቅድስት ምድር ናት ወሎ።
የአማራ ሳይንት ተደባበ ማሪያም መገኛ ወሎ ነዉ። የግማደ መስቀል መገኛ ግሸን ማሪያም መገኛ አምባሰል ወሎ ነዉ።
ከእስልምና እምነት አንፃርም የነብዩ መሀመድ የመጀመሪያዉ መዉሊድ ከተበረበት የጀማ ንጉሰ ነገስት መስጊድ መገኛ ወሎ ነዉ። ወሎ እስልምናና ክርስትና አንድ አምሳልና አንድ አካል ሆነዉ ለዘመናት አብነት የዘለቁበት ሰፊ ሚስጢር በውስጣቸው ይዘው ሁለቱን ሀይማኖቶች አቻችለዉ ትዉልድ ያዘለቁ የእነ መምህር አካለ ወልድ፣ ቤተ ክርስቲያን ሲያሰሩ ፣ መስጊዱን አብረዉ የሚያሳንፁ የእነ ባህታዊ አባ ምስክርና የእነ ሀጂ መሀመድ ገታ ቃል ኪዳን ስላለበት ነዉ።
ሙስሊሙ ከክርስቲያኑ ክርስቲያኑ ከሙስሊሙ የሚጋባበት፣ የስም አወጣጥ ባህሉ ድንበር የሌለዉ ፍቅርን የሚያንፀባርቅ የወሎ ምድር ነዉ።
ከዚህ ጋር በተያያዘ የአካባቢዉን ስነ ቃል ልዋስና ልጅየዉ ሰለሞን አባቱ መሀመድ፣ ምንኛ ደስ ይላል ወሎ ላይ መወለድ፣ የተባለለት ምድር ነዉ ወሎ ።
በረጅምና ዘመን ተሻጋሪ የኢትዮጵያና የአማራ ህዝብ ታሪክ ዉስጥ ወሎ የታሪክ ሀብትና ጉልህ አሻራዎች መገኛ ነዉ።
በኢትዮጵያ የመካከለኛዉ ዘመን ታሪክ ዉስጥ የብዙ ነገስታት ዋና የአቅም ግንባታ ማዕከልና የሀይቅ እስጢፋኖስ ገዳም መገኛዉ ወሎ ነዉ።
በነፃነት ታሪካችን የአድዋ ፍልሚያ ምክንያት የሆነዉ የዉጫሌ ስምምነት የታሰረበት ይስማ ንጉስ መገኛዉ ወሎ ነዉ።
የዳግማዊ ሚኒሊክ የአድዋ ጦርነት የክተት አዋጅ ነጋሪት የተጎሰመበት ወረኢሉ መገኛዉ ወሎ ነዉ። የጣሊያን ወራሪ ሀይል በማይባር ሀይቅ ዙሪያ ልኩን ያሳዩት የእነ ደጃች መንገሻ አብዬ ምድር ነዉ ወሎ
ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስና ፊትአዉራሪ ገብርዬ የመሰሉ ጀግኖች ለኢትዮጵያ አንድነት ሲዋደቁ በክብር ያረፉበት የመቅደላ አምባ ታሪካዊ ስፍራ መገኛዉ ወሎ ነዉ።
ወሎ በኢትዮጵያ አማራ እና አርጎባ ህዝብ የስነ መንግስት ታሪክ መሰረት የጣሉ አርቆ አሳቢ ነገስታቶችን ለአብነትም እነ ራስ አሊ እና ንጉስ ሚካኤል(ኢማም መሀመድ አሊ… …ወላስማ ካሶ የተገኙበት ብርቅዬ ምድር ነዉ። ምስራቃዊው ክፍል በአብዛኛው የሚሸፍነው ሙስሊም ማህበረሰቦችን ሲሆን ምእራባዊው ክፍል ደግሞ ክርስቲያኑና ሙስሊሙ ተሳስሮ የሚኖርበት ምድር ነው።
ይህ ሁሉ ማሳያዎችን ጠቅሱ ለማለፍ እንጂ የወሎ የታሪክ ሀብታምነት በዚህ ብቻ የሚያልቅ አይሆንም።
ወሎ የቆንጆዎችና የገራገሮች ምድር ነዉ።ወሎ የአማራ አቃፊነትማሳያ፣ የብዝሃነት ተምሳሌት ነዉ
ወሎ የአማራዉ፣ የኦሮሞዉ፣ የአፋሩ፣ የአርጎባዉ እና ሌሎችም በፍቅርና በመዋደድ አብረዉ ለዘመናት የዘለቁበት ምድር ነዉ። ብዝሃነት ለወሎ ጌጥ እንጂ ስጋት ሆኖት አያዉቅም።