ደጃዝማች ኃብተ ሥላሴ በላይነህ

ደጃዝማች ኃብተ ሥላሴ በላይነህ በተጉለትና ቡልጋ አውራጃ በከሰም ወረዳ ልዩ ሰሙ ውቢት በሚባለው ሥፍራ፣ ከታወቁት አባታቸው ከአቶ በላይነህ ቢተውልኝ እና ከእናታቸው ከወይዘሮ ማናለብሽ በድሉ መስከረም ፮ ቀን ፲፱፻ ዓ.ም ተወለዱ። በተወለዱ በአሥራ አምስት ዓመታቸው በቤተ መንግሥት የዕልፍኝ አሽከር ሆነው ሲያግለግሉ ከቆዩ በኋላ ጥንታዊ የክብር ዘበኛ ሲቋቋም በወታደርነት ተዛውረው አግልግሎታችውን አበረከቱ።

ደጃዝማች ኃብተ ሥላሴ በላይነህ የካቲት 1፰ ቀን ፲፱፻፴፬ ዓ/ም
የፊታ/ኃብተ ሥላሴ ተከታዮች ስንቅ ለመውሰድ ጎንደር ላይ
የሰሜን ዘመቻ-የውጊያው ካርታ

አርበኝነት

ለማስተካከል

መጋቢት ወር ፲፱፻፳፰ ዓ.ም ማይጨው ላይ በተደረገው ታላቁ ጦርነት ከክብር ዘበኞች ጋደኞቻቸው ጋር ሆነው ከፍ ባለ ጀግንነት ከጠላት ጋር በመዋጋት አገራቸውንና ንጉሠ ነግሥታቸውን አግልግለዋል። ከዚያም እንደተመለሱ በንጉሠ ነግሥታቸው መሪ ትእዛዝ መሠረት የጦርነት ትግላቸውን በመቀጠል አምስት ዓመት ሙሉ በአርበኝነት የጦር መሪ በመሆን እጅግ ከፍ ባለ ጀግንነት ሌት ከቀን ያለ አንዳች አረፍት በየጦር ሜዳው የጠላትን ኃይል ያንበረከኩ ታላቅ ጀግና ነበሩ የገደሏቸውንም የጠላት መኮንኖች ለመጥቀስ ያህል፣

፩. በሐምሌ ወር ፲፱፻፳፰ ዓ.ም አሌልቱ ላይ ፹፰ የጠላት የጦር ከባድ መኪናዎች(ካሚዮን)በተቃጠሉ ጊዜ የጦር መሪ የነበሩት አርበኞች ደጃዝማች ኃብተ ሥላሴ በላይነህና ፊታውራሪ ጂማ ሰንበቴ ነበሩ። ደጃዝማች ኃብተ ሥላሴ በዚሁ ጦርነት ላይ ሁለት የጠላት ከፍተኛ መኮንኖች ግድለዋል።

፪.ክቡር ደጃዝማች ኃብተ ሥላሴ በላይነህ በአሌልቱ ሜዳ ላይ ከኅዳር ፳፩ ቀን ፲፱፻፳፱ ዓ.ም ጀምሮ ሦስት ቀን ሙሉ የፈጀውን ጦርነት ባደረጉ ጊዜ ከጠላት በኩል የኢጣሊያ ፋሽስቶች ብቻ ፺፮ መኮንኖችና ወታደሮች ተግድለዋል።

፫.በ፲፱፻፳፱ ዓ.ም ሸንኮራ አራራቲ ላይ በተደረገው ኃይለኛ ጦርነት ጄኔራል አውጎስቲኒን ግድለዋል።

፬.በ፲፱፻፴ ዓ.ም ቡልጋ ውስጥ ጨመሪ በተባለ ቦታ በተደረገው ከባድ ጦርነት ክቡር ራስ ደስታ ዳምጠውን እና እነደጃዝማች አበራ ካሳን የገደለውን ከፍተኛ የጠላት የጦር መሪ ገድለዋል።

፭.በግንቦት ወር ፲፱፻፴ ዓ.ም በቡልጋ የጉንጭ በተባለ ሥፍራ በተደረገው ብርቱ ጦርነት ጄኔራል ጋሊያኒን ገድለዋል።

ጀኔራል ጋሊያኒ በተገደለ ማግስት ስቻት በተባለው ሥፍራ የጠላት አውሮፕላኖች ብዙ ስንቅና ጥይት ለደጃዝማች ጦር ጥለዋል። ይህም ሊደረግ የቻለው ከጄኔራል ጋሊያኒ ላይ ብዙ የጦር መሣሪያና የአውሮፕላን ምልክት የሆነውን ሰንደቅ ዓላማ ስለማረኩ ነው። ከነዚህም ከገደሏቸው የጠላት መኮንኖች ላይ ብዙ ኒሻን ማርከው አሁን በቤተ መጻሕፍት መወዘክር ለመታሰቢያ ሰጥተዋቸው ይገኛሉ።

የሰሜን ዘመቻ

ለማስተካከል

ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴእንግሊዝ ሠራዊት እርዳታ ሚያዝያ ፳፯ ቀን አዲስ አበባ ሲገቡ በራስ አበበ አረጋይ የሚመራው የሸዋአርበኛ ሠራዊት በሰሜን ኢትዮጵያ መሽጎ የተቀመጠውን የጣልያን ጦር ከ እንግግሊዙ "ጊዲዮን ፎርስ" ሠራዊት ጋር ለማስለቀቅ ሲላኩ፣ ደጃዝማች ኃብተ ሥላሴ አርበኞቻቸውን ይዘው ዘመቱ።

ሸዋ ተነስተው ከ ፭፻ አርበኞች ጋር በ እንግሊዙ 'ቢምባሺ ጋይ ካምቤል' መሪነት በመጀመሪያ ደሴ ላይ የ'ዱካ ዳዎስታ'ን ጦር ድል ካደረጉ በኋላ ጉዟችውን ወደ ጎንደር በመቀጠል በ ፯ሺ የ 'ዳግላስ ፎርስ' ጋር ተቀላቀለው አስከ ጎንደር ድረስ የነበሩትን ታላላቅ የጠላት የጦር ምሽጎች በተለይም ቁልቋል በር እና ፍርቃ በር የተባሉትን ምሽጎች ከነ ፊታውራሪ ከበደ ካሳ እና ደጃዝማች ኪዳኔ ወልደመድኅን አርበኞች ጋር በመተባበር ደመሰሱ።

ነሐሴ ፲፱ ቀን ፲፱፻፴፫ ዓ/ም በጣልያኑ ኮሎኔል አድርያኖ ቶሬሊ የሚመራው ሠራዊት ቁልቋል በር ላይ ለመሸገው ሠራዊት በአምሳ ስምንት የጭነት መኪና ስንቅ አቀብሎ ወደጎንደርሲመለስ አርበኞቹና እንግሊዞች በጣሉበት አደጋ ላይ ከወገን ሠራዊት ፲፬ ሰዎች ሲሞቱ ከቆሰሉት ፴፱ ሰዎች መሃል እግራቸውን በጥይት የቆሰሉት አንዱ ደጃዝማች ኃብተ ሥላሴ ነበሩ።[1]

በመጨረሻም ጎንደር ላይ የሠፈረውን የጀኔራል ጉልዬልሞ ናሲን ሠራዊት በጦር ኃይል የጦር ምሽጉን በመጣስ ከተማው ውስጥ ገቡ። ኅዳር ፲፰ ቀን ፲፱፻፴፬ ዓ.ም ፤ አዲስ አበባ ነጻ በወጣች በ ፯ኛው ወር፣ የጄነራል ጉልዬልሞ ናሲ ሠራዊት ድል ሆኖ የፋሺስት ኢጣልያ ወረራ ጎንደር ላይ አከተመ።

በነጻነት ዘመን

ለማስተካከል

ከዚህ ድል በኋላ፣ ደጃዝማች ኃብተ ሥላሴ ከነሠራዊታቸው ወደ አዲስ አበባ ተመልሰው የካቲት ፲፰ ቀን ፲፱፻፴፬ ዓ/ም በታላቅ ሰልፍና ሥነ ሥርዓት ስድስት ዓመት ከተለዩዋቸው ንጉሠ ነግሥታችው ፊት ቀርበው ቆርጠጥ ቆርጠጥ ጎርደድ ጎርደድ አንዳንዴም በርከክ እያሉ ፤


ኃብቴ ኃብተ ሥላሴ የጠቅል አሽከር የንጉስ ተፈሪ ፤

ለሃይማኖቱ ተከራካሪ ፤

ጄኔራል ገዳይ ኒሻን ያሠረ ፤

ማጆር ማራኪ የተከበረ ፤

ያንተ አሽከር ያንተ ወታደር ፤

በዘመተበት የማያሳፍር ፤

ዘው ዘው ባይ ከጦሩ ማህል ፤

ጄኔራል ናዚ አቤት አቤት ሲል ፤

እያሉ ይህንንና ይህን የመሳሰለውን የፉከራ ቃል እየተናገሩ ከማይጨው ጀምረው እስካሁን ድረስ የሠሩትን ጀብዱ ሲቆጥሩ እንኳን ከዚህ በፊት ሥራ የሰራውን ቀርቶ ያልሰራውንም ዘራፍ ለገናው ለማለት ወኔውን ይቀሰቅሰው ነበር ።ከዚህ በኋላ የማረኳቸውን ከባድና ቀላል መትረየሶች በማበርከት ያደረጓቸውን አግልግሎቶች ጠቅሰው ፤

«እኔ አገልጋይዎ እንኩዋን አይነዎን አይቼ ከፊትዎ ቀርቤ ድካሜንና ሙያዬን ተናግርኩ እንጂ እንግዲህ እኔ ይህንን እድል ካግኘሁ በኋላ እውነተኛ ባሪያዎ ነኝና ምንም አላሳስብምብለው ቢናገሩ» ግርማዊ ጃንሆይ «ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን ከመውደዱ የተነሣ እንግዲህ እናንተ ጌቶች ናችሁ እንጂ ባሮች አይደላችሁም እንዳላቸው ተወዳጅ ልጅ ነህ እንጂ ባሪያ አይደለህም ሥራህም በማንም አፍ የተመሰገነ ነው»።<refባንዲራችን ጋዜጣ ፩ኛ ዓመት፣ ቁጥር ፴፱ የካቲት ፲፰ ቀን ፲፱፻፴፬ ዓ/ም</ref> ብለው ሞገሳዊ ቃል ሰጥተዋቸዋል። በዚሁ ዕለት የደጃዝማችነት ማዓረግ ተሰጣቸው።

ከዚያም ወዲህ

፩/የክብር ዘበኛ ከፍተኛ መኮንን ሆነው በአስፈላጊው ቦታ እየተዘዋወሩ ፀጥታ ነሺዎችን የጦር ኃይል እያዘዙ ፀጥታ አስከብረዋል።

፪/በ፲፱፻፴፱ ዓ.ም ክፍለ ጦራቸውን እያዘዙ የጉርሱምና የጊሪ አውራጃ ገዥ ሆነው ተሹመዋል።

፫/በ፲፱፻፵፯ ዓ.ም በግርማዊ ንጉሠ ነግሥት መልካም ፈቃድ የጨቦና ጉራጌ አውራጃ ገዥ ሆነው ተሹመዋል።

፬/በ፲፱፻፶፪ ዓ.ም የምሥራቅ ሸዋ ብሔራዊ ጦር አዛዥ ሆነው ተሹመዋል።

፭/በ፲፱፻፶፫ ዓ.ም የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባል ሆነው በመሾም እስከ ዕለተ ሞታቸው ጊዜ ድረስ አግልግለዋል።


የተሸለሟቸው ኒሻኖችና ሜዳዮች

  • የቅዱስ ጊዮርጊስ የጀብዱ ሜዳይ ባለ ፪ ዘንባባ ፤
  • የአርበኝንት ሜዳይ ፤
  • የኢትዮጵያ የክብር ኮከብ ኮማንደር ያለ ፕላክ ፤
  • የኢትዮጵያ የክብር ኮከብ ከነ ፕላኩ ፤
  • ከእንግሊዝ መንግሥት፦ የአፍሪቃ ኮከብ እና የአፍሪቃ የድል ኮከብ ሜዳዮች ፤
  • የኢትዮጵያ የድል ኮከብ ሜዳይ ናቸው።

ክቡር ደጃዝማች ኃብተ ሥላሴ በላይነህ ፈጣሪያቸውን ፈሪ፤ ሀገራቸውንና ንጉሠ ነገሥታቸውን አፍቃሪ ፤ ድኅ መጋቢና አሳዳሪ ፤ ሽማግሌዎችን ጧሪ ፤ ጓደኞቻቸውን አክባሪ ነበሩ። ብዙ ጊዜ ያማቸው በነበረው የጉበትና የልብ ድካም ህመም ሚያዝያ ፲፩ ቀን ፲፱፻፷ ዓ.ም በተወለዱ በ፷ ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ። ግርማዊ ቀዳማዊ ንጉሠ ነገሥት ኃይለ ሥላሴ ፤ የተከበሩ ልዑላውያን ቤተሰቦች፤ የተከበሩ ሚንስትሮችና ከፍተኛ የጦር ባለስልጣኖች በተገኙበት በከፍተኛ ወታደራዊ ሥነ ሥርዓት በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ለሀገራችው ታላላቅ አገልግሎት ለፈጸሙ ጀግኖች አርበኞች በተዘጋጀው ሥፍራ በክብር አርፈዋል።

  1. ^ Shirreff(1995) p243