ዮቅጣን
ዮቅጣን (ዕብራይስጥ፦ יָקְטָן ፤ አረብኛ፦قحطان /ቃሕጣን/) በብሉይ ኪዳን መሠረት ከኤቦር 2 ልጆች ታናሹ ነበረ። ታላቅ ወንድሙ ፋሌክ ነበረ። ልጆቹም (ዘፍ. 10፡26-29) ኤልሞዳድ፣ ሣሌፍ፣ ሐስረሞት፣ ያራሕ፣ ሀዶራም፣ አውዛል፣ ደቅላ፣ ዖባል፣ አቢማኤል፣ ሳባ፣ ኦፊር፣ ኤውላጥና ዮባብ ናቸው።
የመጽሐፍ ቅዱስ ቅርሶች (Biblicarum antiquitatum liber ወይም «ፕሲውዶ-ፊሎ») በተባለው ጽሑፍ ዘንድ (70 ዓ.ም. ያሕል)፣ ከኖህ ዘመን በኋላ ዮቅጣን የሴም ወገኖች ልዑል የተደረገ ሲሆን፣ እንዲሁም ናምሩድም የካም ወገኖች ልዑል፣ ፌኔክም (የሮድኢ ያዋን ልጅ) የያፌት ወገኖች ልዑል ተደረጉ። ሦስቱም መሳፍንት ሰው ሁሉ ጡብ ለባቢሎን ግንብ እንዲሠራ ቢያዝዙም፣ 12 ሰዎች ግን እምቢ አሉ። ከነዚህ 12 እምቢተኞች መካከል፣ የዮቅጣን ልጆች ስሞች አልሞዳድ፣ ዮባብ፣ አቢማኤል ሳባና ኦፊር ይታያሉ። ተቆጥተው መሳፍንቱ ይሙት በቃ ቢፈርዱባቸው፣ ዮቅጣን ግን በስውር ከሰናዖር ወደ ተራሮቹ እንዲያመልጡ ረዳቸው።[1] እንዲህ ያለ ትውፊት በአይሁዳዊው ጽሑፍ የየራሕሜል ዜና መዋዕል (1140 ዓ.ም. ገደማ) ይደገማል፤ በክርስቲያኑም መምህር ጴጥሮስ ኮመስቶር መጽሐፍ ዘንድ (1162 ዓ.ም.) ሦስቱ መሪዎች ዮቅጣን፣ ናምሩድና ለያፌት ወገን «ሱፌኔ፣ ወይም ሱስቴኔ» ይባላሉ።
ተመሳሳይ ልማድ በኢትዮጵያ ተዋሕዶ ታሪኮች ይገኛል፤ የዮቅጣን ልጆች በግንቡ መሳተፍ ስላልወደዱ የቀድሞው ግዕዝ ቋንቋ ለመጠብቅ እንደ ተፈቀዱ ይላል። በአለቃ ታዬ ታሪክ መጽሐፍ ዘንድ፣ 5ቱ ልጆች ሳባ፣ ኦፊር፣ ኤውላጥ፣ ዖባልና አቢማኤል ከወንድሞቻቸው ጋር ቦታ ስላላገኙ በየመን ሠፈሩ። ለጊዜ ለኩሽ ነገሥታት (ከቀይ ባሕር ማዶ) ተገዙ። ከዘመናት በኋላ የሕንድ ንጉሥ ራማ በወረረበት ጊዜ የሳባ፣ ዖባልና ኦፊር ነገዶች ተሻግረው ራማን አስወጡ። ከዚያ ሳባ ወይም አግዓዝያን በትግራይ፣ ዖባል በአዳል፣ ኦፊር በውጋዴን ሠፈሩ፤ ኤውላጥና አቢማኤል በየመም ቀሩ።
በዓረባውያን ልማዶች ደግሞ የየመን ጥንታዊ ኗሪዎች ከቃህጣን (ዮቅጣን) ተወለዱ። ኢብን ዓብድ ራቢህ (852-932 ዓ.ም.) «አንድያው ድሪ» በተባለ መጽሐፍ የየመንን ሐረጎች ሲተርክ የቃህጣን ልጆች እነዚህ ናቸው ይለናል፦ ያሩብ (ያራሕ)፣ ሳባ፣ አል-ሙስሊፍ (ሣሌፍ)፣ አል-ሚርዳድ (ኤልሞዳድ)፣ ዲቅላ፣ አቢማል፣ ዑባል፣ ኡዛል፣ ጁርሁም ወይም ሀዱራም፣ ኡፊር፣ ሁዋይላ (ኤውላጥ)፣ ሐድረማውት እና ኑባት (ዮባብ) ይባላሉ።
ዳሩ ግን አንድንድ ጸሐፊ እንደ ዮሴፉስና አቡሊድስ የዮቅጣን ልጆች በሕንዱስ ወንዝ ላይ እንደ ሠፈሩ ይላል።
የጀርመን ታሪክ ጸሐፊ ዮሐንስ አቬንቲኑስ 1513 ዓ.ም. ባሳተመው መዝገቦች ዘንድ፣ ዮቅጣን በሌላ ስሙ «ኢስተር» ይባላል። በርሱ ታሪክ፣ ኢስተር፣ ናምሩድና ሦስተኛው ሳሞጤስ መጀመርያ 3ቱ መሪዎች ነበሩ። ሕዝቡ በተበተኑበት ጊዜ ኢስተር፣ አባቱ ኤቦርና አያቱ ሳላ ከቱዊስኮን ጋራ ወደ አውሮፓ ገቡ፣ በአሁኑ ኦስትሪያ ሠፈሩ። ስለዚሁ ኢስተር (ዮቅጣን) የዳኑብ ወንዝ ስም «የኢስተር ወንዝ» ተባለ። ከኢስተር ልጆች ደግሞ ብዙ በአውሮፓ ሠፈሩ፦ ሳርማቴስ (ሐስረሞት) በሳርማትያ፣ ዳልማታ (አልሞዳድ) በድልማጥያ፣ አዛሉስ (አውዛል) በባቫሪያ፣ አዱላስ (ሐዶራም) በስዊስ፣ ያዳር (ያራሕ) በሊቡርኒያ፣ ኤፖሩስ በኤፒሩስ ክፍላገራት እንዳቆሙ ይለናል። የ12ኛው ክፍለ ዘመን ታሪክ ጸሐፊው ሚካኤል ሶርያዊው ደግሞ በሱርስጥ ቋንቋ ሲጽፍ ከዮቅጣን ልጆች አንዳንድ በዳኑብ ወንዝ ላይ ምድር እንደ ወረሰ ይላል።
ስለ ዮቅጣን 3 ልጆች ስለ ሳባ፣ ኦፊርና ኤውላጥ የሆነ ተጨማሪ መረጃ በአንዳንድ ጥንታዊ አረብኛ ወይም ግዕዝ ጽሑፍ ተገኝቷል፤ እንደሚከተለው፦
- «ኪታብ አል-ማጋል»፦
- እርሱ (ናምሩድ) በራግው ዕለታት ሞተ፣ ይህም አዳም ከተፈጠረው 3ኛው ሺህ ነበረ። በቀኖቹ የግብጽ ሰዎች «ፍርንፍስ» የተባለ ንጉሥ በላያቸው አቆሙ። እርሱ ለ68 አመታት ነገሠባቸው። በቀኖቹ ደግሞ አንድ ንጉሥ በሳባ መንደር ነገሠ፣ የኦፊርና ኤውላጥም ከተሞች ለመንግሥቱ ጨመረ፤ ስሙም «ፈርዖን» ነበረ። ኦፊርን ከወርቅ ድንጋይ ሠራ፤ የተራሮቹ ድንጋዮች ጥሩ ወርቅ ናቸውና። ከርሱ በኋላ በኤውላጥ «ሃዩል» የተባለ ንጉሥ ነገሠ። እርሱ ሠራውና መሠረተው፤ ከፈርዖንም መሞት በኋላ እስከ ዳዊት ልጅ ሰሎሞን ዘመን ድረስ ሴቶች (ንግስቶች) በሳባ ላይ ይነግሱ ነበር።
- «የመዝገቦች ዋሻ»፦
- በራግው ዕለታት፣ ግብጻውያን የሆኑት የ«መስራየ» ሰዎች መጀመርያ ንጉሣቸውን ሾሙ፤ ስሙ «ፑንቶስ» ሲሆን ለ68 ዓመታት ነገሰባቸው። በራግውም ዕለታት፣ ንጉሥ በሳባ፣ በኦፊርና በኤውላጥ ነገሠ። በሳባም ከሳባ ሴት ልጆች 60 ነገሡ። ለብዙ አመታት እስከ ዳዊት ልጅ ሰሎሞን መንግሥት ድረስ ሴቶች በሳባ ገዙ። የኦፊርም ማለት የስንድ ልጆች ንጉሣቸው እንዲሆን «ሎፎሮን» ሾሙ፤ እሱም ኦፊርን ከወርቅ ድንጋይ ሠራ። አሁን በኦፊር ያሉት ድንጋዮች ሁሉ የወርቅ ናቸው። የኤውላጥም ልጆች ንጉሣቸው እንዲሆን ሃዊል ሾሙ፣ እርሱ ኤውላጥን ማለት ሕንድን ሠራ።
- በነዚያ ዕለታት የራግው ዕድሜ 180 ዓመታት ነበረ፤ በ140ኛው ዓመት «ያኑፍ» በግብጽ አገር ላይ ነገሠ። እርሱ በላዩ የነገሠው መጀመርያው ንጉሥ ነው፤ እርሱም ሜምፎስን ከተማ ሠርቶ በራሱ ስም ሰየመው። ያው ማለት ስሙ ምስር ወይም «ማስሪን» የሆነው ነው። ይህ ያኑፍ ሞተ፤ በፈንታው በራግው ዕለታት፣ አንድ ከሕንደኬ ነገሠ፣ ስሙም «ሳሰን» የሆነ፣ እርሱም የሳባ ከተማ የሠራ ነው። በዚያም አገር የነገሡ ነገሥታት ሁሉ ከከተማው ስም «ሳባውያን» ተባሉ። ከዚያ «ፋርአን» በሳፊር (ኦፊር) ልጆች ላይ ነገሠ፤ እርሱም የሳፊርን ከተማ ከወርቅ ድንጋዮች ሠራ፤ ያውም የ«ሳራኒያ» አገር ነው፤ ስለነዚህም ወርቅ ድንጋዮች፣ የዚያው አገር ተራሮችና ድንጋዮቹ ሁሉ የወርቅ እንደ ሆኑ ይላሉ። ከዚያ የሕንድ አገር «ለበንሳ» ልጆች ንጉሣቸው እንዲሆን «ባኅሉል» የተባለውን አደረጉ፤ እርሱም ባኅሉ ከተማ ሠራ። ከዚያ ራግው በ289ኛው አመቱ ሞተ።
ማጣቀሻ
ለማስተካከል- ^ Biblical Antiquities (Pseudo-Philo) (እንግሊዝኛ)