ሮድኢ (ዕብራይስጥ፦ דודנים /ዶዳኒም/ ወይም רודנים /ሮዳኒም/፤ ግሪክኛ፦ Ρόδιοι /ሮዲዮይ/) በኦሪት ዘፍጥረት 10:4 ፩ ዜና መዋዕል 1:7 መሠረት የያዋን ያፌት ፬ኛ ልጅ ነበር።

ሳምራዊው ትርጉምና በአንዳንድ ዕብራይስጥ ቅጂ ስሙ ሮዳኒም ተጽፎ መታወቂያው የሩድ (ግሪክኛ፦ ሮዶስ) ደሴት ሰዎች አባት እንደ ነበር ይገመታል።[1] እንዲሁም በግሪክኛው ትርጉም ሮዲዮይ ሲባል ይህም ማለት የሩድ ሰዎች ሊሆን ይችላል። በዕብራይስጥም ይህ «ሮዳኒም» የያዋን ልጅ ስም ቢሆንም «-ኢም» የሚለው መድረሻ ብዙ ጊዜ ለብዙ ቁጥር (ለብሔር ስም) ይጠቀማል። በሌላ አስተሳሰብ ፈረንሳያዊው ምሁር ሳሙኤል ቦሻር «ሮዳኒም» በደቡብ ፈረንሳይ ካለው ከሮን ወንዝ (በጥንት፦ «ሮዳኑስ ወንዝ») ስም ጋር ግንኙነት እንደ ነበር አሰቡ።

በሌላ በኩል ዶዳኒም የሚለው አጻጻፍ በብዙዎች ቅጂዎች በመገኘቱ፣ ግንኙነት ከዶዶናኤጲሮስ (ስሜን-ሜራብ ግሪክ እና አልባኒያ) ወይም ደግሞ ከዳርዳኒያ (የዛሬው ኮሶቮ አካባቢ) ጋር እንዳለው ታስቧል። እነዚህ አገሮች በግሪኮችና በእልዋሪቆን መካከል ነበሩ። ዳርዳኖይ የሚባል ብሔር በሆሜር ዘንድ በትሮአስ ወገን ተዋጉ። በግብጽም መዝገቦች «ዳርዳናዩ» የተባለ ግሪካዊ ብሔር በ፫ አመንሆተፕ ዘመን (1394-1355 አክልበ.) ሲጠቀስ፤ በኋላ ደግሞ በቃዴሽ ውግያ (1283 ዓክልበ.) «ዳኑኒም» የተባለ ጎሣ በኬጢያውያን ወገን ተዋጉ። እነዚህ ሕዝቦች ምናልባት ከ«ዶዳኒም» ጋር አንድላይ እንደ ሆኑ የሚያስቡ ደራስያን አሉ።[2]

62 ዓ.ም. ግድም የተጻፈው አይሁዳዊ መጽሐፍ «የመጽሐፍ ቅዱስ ቅርሶች» (ሐሣዊ-ፊሎ የተባለው መጽሐፍ) እንደሚለው፣ ስሙ ድዎደኒም ተብሎ ልጆቹ ኢጤብ፣ በዓጥ እና ፌኔክ ይባላሉ። ይህ መጨረሻ ልጅ ፌኔክ በባቢሎን ግንብ ወቅት የያፌት ልጆች አለቃ ሆነ (ናምሩድዮቅጣንካምሴም ልጆች አለቆች ሲሆኑ ነው)።


ዋቢ ምንጮች ለማስተካከል

  1. ^ «መጽሐፍ ቅዱስ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ከማጥኛ ጽሑፎች ጋራ» ስሙ «ሮዲኢ» ተጽፎ «ሮዴስ በተባለች የግሪክ ደሴት ላይ የሚኖሩትን ሕዝቦች የሚገልጽ ስም ሳይሆን አይቀርም» ሲል፣ «ሮዴስ» የሚል አጻጻፍ ከእንግሊዝኛው ትርጉም አጻጻፍ ("Rhodes") ተበድሯል፤ ሩድ ወይም ሮዶስ ደሴት ማለት ነው።
  2. ^ Kitchen, Kenneth A. (2003). On the Reliability of the Old Testament. Grand Rapids and Cambridge: William B. Eerdmans Publishing Company. p. 593. ISBN 9780802849601.