ሳላ (የኤቦር አባት)
ሳላ (ዕብራይስጥ፦ שלח /ሼላሕ/) በኦሪት ዘፍጥረት 10፡24፣ 11፡14፤ በመጽሐፈ ዜና መዋዕል ቀዳማዊ 1፡18፣ እንዲሁም በሉቃስ ወንጌል 3፡35 መሠረት የቃይንም ልጅና የዔቦር አባት ነበረ። የአማርኛ (ኢኦተቤ) ትርጉም እንደ ግሪክ ትርጉም እንዲህ ይላል። ሆኖም በዕብራይስጥ ብሉይ ኪዳን ትርጉም የቃይንም ስም አይታይም፣ በርሱ ፈንታ አርፋክስድ በቀጥታ የሳላ አባት ያደርገዋል።
ዘፍጥረት 11፡14-15 ስለ ሳላ እንደሚለው፣ የሳላ ዕድሜ 130 ዓመት ሲሆን ዔቦርን ወለደ፣ ከዚያም ሳላ 330 ዓመት ኖረ። እነዚህ ቁጥሮች ከግሪኩ ትርጉም ሲገኙ የዕብራይስጥና ሳምራዊው ትርጉም ቁጥሮች ግን ይለያያሉ። በእብራይስጥ ትርጉም በ30 ዓመት ዔቦርን ወለደ፣ ከዚያም 403 ዓመት ኖረ፤ በሳምራዊውም በ130 ዓመት ኤቦርን ወለደ፣ ከዚያም 303 ዓመት ኖረ።
በመጽሐፈ ኩፋሌ 8፡38 ሳላ ከአባቱ ቃይንምና ከእናቱ ሜልካ በ1432 አመተ አለም ተወለደ። በ1499 አ.አ. ሚስቱን ሙአክ አገባ፣ እርስዋም የአርፋክስድ ልጅ የኬሴድ ሴት ልጅ ትባላለች። በ1503 አ.አ. ሙአክ ዔቦርን ወለደችለት ይላል።
የጀርመን ታሪክ ጸሐፊ ዮሐንስ አቬንቲኑስ 1513 ዓ.ም. ባሳተመው መዝገቦች ዘንድ፣ አሕዛብ ከሰናዖር ከተበተኑ በኋላ ሳላ ከዔቦርና ኢስተር (ዮቅጣን) ጋራ በአሁኑ ኦስትሪያ ዙሪያ ሠፈረ። ሳላ ከሠራቸው ከተሞች መካከል ማሪያ ዛልና ዛላሉቩ ይጠቅሳል። የሳላ አባት «ፓኖ» ደግሞ በፓኖኒያ ሠፈረ ይላል። የሳላ ዕድሜ 433 አመት ሲሆን እንዳረፈ ይጨምራል።