ቱዊስኮን (ቱዊስኮ) ወይም ቱዊስቶ በጥንታዊ ጀርመን ነገዶች አፈ ታሪክ የጀርመኖች ሁሉ አባት ነበረ።

ቱዊስኮ፣ በ1545 ዓ.ም. ሠዓሊ አስተያየት

የቱዊስቶ ወይም ቱዊስኮ ስም ከሮሜ ጸሐፊው ታኪቱስ ታሪክ ገርማኒያ (90 ዓ.ም. የተጻፈ) ተጠቅሶ ይታወቃል። ታኪቱስ እንደ ገለጸው፣ በጀርመናውያን «ጥንታዊ ዘፈኖች» ውስጥ ይህ ቱዊስቶ «ከምድር የተወለደ አምላክ» ሆኖ ይከብር ነበር። በተጨማሪ በነኚህ ዘፈኖች በኩል፣ ልጁ ማኑስ እራሱ ሶስት ልጆች ነበሩት፣ እነኚህም 3 ልጆች የኢንጋይዎን፣ የኢስታይዎን እና የሄርሚኖን ብሔሮች ወለዱ።

1490 ዓ.ም. አኒዩስ ዴ ቪቴርቦ የተባለ ጣልያናዊ መነኮሴ ባሳተመው ጽሑፍ ዘንድ፣ የባቢሎን ታሪክ ጸሓፊ ቤሮሶስ (290 ዓክልበ.) ስለ ኖህ ልጆች ብዙ መዝገቦች አቅርቦ ነበር። በዚህ በኩል፣ አሕዛብ በምድር ሲበተኑ የኖህ ልጅ ቱዊስኮን ከብዙ ሕዝብ ጋር በሳርማትያ አገር ሠፈረ። በናምሩድ 25ኛው ዓመት ቱዊስኮን የሳርማትያ እና የጀርመን አገሮች መጀመርያ ንጉሥ ሆነ። የቱዊስኮን ግዛት ከራይን ወንዝ እስከ ዶን ወንዝ ያለው ሁሉ ያጠቀልል ነበር። በቱዊስኮን 98ኛው አመት ደግሞ ሕግጋት ለአገሩ እንዳወጣ ይላል። በሙሉ 152 ዓመታት ከነገሠ በኋላ ልጁ ማኑስ እንደ ተከተለው ይጨምራል።

1513 ዓ.ም. ግድም ጀርመናዊው መምህር ዮሐንስ አቬንቲኑስ የጀርመን ዜና መዋዕል ጻፈ፤ በዚህ ውስጥ ስለ ጀርመን መጀመርያው ንጉሥ ቱዊስኮን ዘመን ብዙ ተጨማሪ ልማዶች አቀረበ። ከቱዊስኮን በታች 20 አገረ ገዦች ነበሩት፤ ቱዊስኮንም አሁን ዱይስቡርግ፣ ጀርመን የሚባል ከተማ ሠራ። ሕግጋቱንም በግጥም ነበር የጻፈው። ለምሳሌ በዚህ ሕገ መንግስት የጋብቻ ፈቃድ በ20 አመት ዕድሜ ለወንድም ሆነ ለሴት ይገኝ ነበር።[1] ቱዊስኮን ደግሞ ግሪኮች ከቶ ሳያውቁት መጀመርያ የግሪክ አልፋቤት የተባለውን ጽሕፈት እንደ ፈጠረው ይላል።

ሌሎች ሊቃውንት ይህ ቱዊስኮን መታወቂያና የአስከናዝ (ጋሜር) ማንነት አንድላይ እንደ ነበር ጻፉ። በራይን ወንዝ ላይ ዱይስቡርግ ብቻ ሳይሆን ዱይስዶርፍ (አሁን ቦን)፣ ዶይትዝ (አሁን ኮልን)፣ እና ዶስቡርግሆላንድ እንደ መሠረተ የሚል ልማድ አለ።

ቀዳሚው
የለም (መሥራች)
የቱዊስኮኔስ (ጀርመን) ንጉሥ ተከታይ
ማኑስ
  1. ^ Intra annum vicesimum foeminae noticiam habuisse, in turpissimis haberi iussit rebus, quo sera iuuenum aetas, eoque inexhausta pubertas foret: nec Virgines festinarentur, sed eadem iuuentus, similis proceritas, pares, validique miscerentur, ut robora parentum liberi referrent. የአቬንቲኑስ ጽሁፍ ገጽ. 14