ብላታ አየለ ገብሬ (፲፰፻፹፯ ዓ/ም - ታኅሣሥ ፯ ቀን ፲፱፻፶፫ ዓ/ም) የውጭ ጉዳይ አደራዳሪ (diplomat)፤ የውጭ ዜጎች ልዩ ፍርድ-ቤት ሰብሳቢ፤ የፍርድ ሚኒስቴር፤ የንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት እንደራሴ፤ የዘውድ አማካሪ ሆነው የሠሩ ሲሆን የታኅሣሥ ግርግር ጊዜ ከሌሎች መሳፍንት እና መኳንንት ጋር ተይዘው ተገድለዋል። ብላታ አየለ ከአማርኛ በስተቀር፤ ፈረንሳይኛእንግሊዝኛጣልያንኛ እና አረብኛ ጠንቅቀው ያውቁ ነበር።

ወላጆቻቸው የጎንደር ተወላጆች ሲሆኑ፣ አባታቸው አቶ ገብሬ አንዳርጋቸው፣ እናታቸው ደግሞ ወይዘሮ ደብሪቱ ቢሰውር ይባሉ ነበር። ብላታ አየለ የተወለዱት በሐረርጌጠቅላይ ግዛት፣ ጋራ-ሙለታ አውራጃ፣ ግራዋ የተባለ ሥፍራ ላይ እንደነበረና የተወለዱትም በ፲፰፻፹፯ ወይም ፲፰፻፹፰ ዓመተ ምሕረት እንደነበር ተዘግቧል። መሠረተ ትምሕርታቸውንም የተከታተሉት እዚያው ሐረር ውስጥ በሚሲይናውያን ትምህርት ቤት ነበር።[1]

ከጠላት ወረራ በፊት ለማስተካከል

አበራ ጀምበሬ እና ሺፈራው በቀለ (፲፱፻፺፭ ዓ/ም) ባዘጋጁት አጭር የሕይወት ታሪክ ላይ እንደተዘገበው፣ ብላታ አየለ በሐረሩ የካቶሊክ ሚሲይናውያን ትምህርት ቤት ሳሉ በድሬዳዋ ፖስታ ቤት ተቀጥረው ለስድስት ዓመታት እንዳገለገሉና በ፲፱፻፲ ዓ/ም ከወይዘሮ ማርታ ንዋይ ጋር እንደተጋቡ እንረዳለን። ወዲያውም ወደ ድሬዳዋ የጉምሩክ መሥሪያ ቤት ሹም ሆነው ከተዘዋወሩ በኋላ የመሥሪያ ቤቱ ሥራ አስኪያጅነትን ተሹመው እስከ ፲፱፻፳ ዓ/ም አገለገሉ።

፲፱፻፳ ዓ/ም፣ በወቅቱ የአዲስ አበባ ጉምሩክ ኃላፊ የነበሩት አቶ ገብረ እግዚአብሔር ፍራንስዋ ወደ አውሮፓ በመላካቸው አየለ ገብሬ በጊዜያዊ አስተዳዳሪነት ተሹመው ወደ ርዕሰ-ከተማዋ አመሩ። አቶ ገብረ እግዚአብሔርም የሐረሩ ሚሲዮን ምሩቅ ሲሆኑ፤ ከዚሁ ከአውሮፓ ጉዟቸው ሲመለሱ ነጋድራስ (በኋላ ራስ ቢትወደድ) መኮንን እንዳልካቸውን ተክተው ጊዜያዊ የንግድ ሚኒስትር ሆነው ተሹመው ሳሉ በሙስና ተከሰው የገንዘብ እና የሦስት ዓመት እሥራት ተቀጥተዋል። [2] ብላታ አየለ ገብሬ ግን ለአንድ ዓመት በአዲስ አበባ የጉምሩክ ኃላፊነት ከሠሩ በኋላ በመጋቢት ወር ፲፱፻፳፩ ዓ/ም በከንቲባ ነሲቡ ዘአማኔል ሥር የአዲስ አበባ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ሥራ አስኪያጅ ሆነው ለሦስት ዓመታት ሠርተዋል።

፲፱፻፳፬ ዓ/ም የውጭ ዜጎች ልዩ ፍርድ-ቤት ሰብሳቢ ሆነው ተሾሙ። ይህ ፍርድ ቤት በኢትዮጵያውያን እና በውጭ ዜጎች መኻል ብቻ በሚከሰቱ ወንጀሎችና ቅራኔዎች ላይ ፍትህ ለመስጠት የተመሠረተ ልዩ ፍርድ ቤት ሲሆን ከዳኞቹ መኻል የውጭ ዜጋውን ቆንስላ ወይም ሌጋሲዮን የወከለ የአገሩ ዜጋ አብሮ ይመደብበት ነበር። ጉዳዩ የሚመለከታቸው፤ ከሳሽም ተከሳሽም የውጭ ዜጎች የሆኑ እንደሆነ ግን በፍርድ የሚቀመጡት ዳኞች ሙሉ በሙሉ የአገራቸው ወኪሎች ሲሆኑ የፍትሁም መሠረት በአገራቸው ሕግ እንጂ የኢትዮጵያን ሕግ አይመለከትም ነበር።

ኢጣልያ ወረራ ዘመናት ለማስተካከል

ግፈኛው የፋሺስት ኢጣልያ መንግሥት ኢትዮጵያን እንደወረረ ብላታ አየለ ገብሬ ታማኝነታቸውን ለዚሁ ወራሪ ኃይል መስክረው ከገቡለት የመጀመሪያዎቹ ኢትዮጵያውያን አንዱ ነበሩ። ከጣሊያኖቹም ጋር በመተባበር የፍርድ ሥራውን በማቀነባበር የሠሩ ሲሆን የካቲት ፲፪ ቀን ፲፱፻፳፱ ዓ/ም በግራዚያኒ ላይ የደረሰውን የቦምብ አደጋ ተከትሎ፣ ጥፋተኛ የተባሉትን ኢትዮጵያውያን በማደን ተባብረዋል።[3]

ከዚህም አልፎ፤ በማንኛውም አገር-ወዳድ እና የታሪኩን ዘገባ በተረዳ ኢትዮጵያዊ የበለጠ ዘላቂ ቁስልን ያሳደረው ድርጊታቸው በሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስ ላይ የሞት ፍርድ ቅጣት የመሐል ዳኛው ኢጣሊያዊው ኮንቴ ዴላ ፓርቶ ጋር ግራና ቀኝ ከተቀመጡት ሁለት የኢትዮጵያ ተወላጆች አንደኛው መሆናቸው ነው። የግራ ዳኛውን ወንበር የያዙት ሁለተኛው የኢትዮጵያ ተወላጅ እና የክፍሌ ወዳጆ አባት የነበሩት ነጋድራስ ወዳጆ ዓሊ ናቸው። [4]

ይህም ሆኖ ብላታ አየለ በኢጣልያ ሹማምንቶች ግንዛቤ ታማኝነታቸው ጥርጣሬ ውስጥ በመግባቱ እስከ፲፱፻፴፩ ዓ/ም ድረስ አዚናራ ደሴት በእሥራት ቆይተው ተመልሰዋል። በእሥር ቤቱ ውስጥ በተካሄደው ምርመራ ብላታ አየለ ለኢጣልያ አስተዳደር ታማኝነታቸውን ያስመሰከሩና በወገኖቻቸው ላይ በተደረጉ እርምጃዎች የተባበሩ እንጂ በእሥራት መቀጣት እንደሌለባቸው የተረጋገጠ ሲሆን፤ በዚሁ ዓይነት የተመሰከረላቸውን ሌሎችንም ኢትዮጵያውያን መኳንንትን ጣሊያኖቹ በአስቸኳይ ወደአገራቸው እንዲመልሷቸው ያበረታታቸው ጉዳይ ደግሞ ሰኔ ፮ ቀን ፲፱፻፴ ዓ/ም ዘርዓይ ድረስ የተባለው የእሥረኞቹ አስተርጓሚ የነበረ ኤርትራዊ በብዙ የሮማ ዜጎች ላይ ያደረሰው ጉዳት ነው። [5]

ከድል በኋላ እስከ ታኅሣሥ ግርግር ለማስተካከል

ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በድል አድራጊነት ሚያዝያ ፳፯ ቀን ፲፻፴፫ ዓ/ም አዲስ አበባ ከገቡ በኋላ፤ ብላታ አየለ ለጣሊያኖች በማደራቸውና ወገኖቻቸውን በመክዳት ስላደረሱባቸው ጉዳት በመቀጣት ፋንታ፣ ግንቦት ፫ ቀን ፲፱፻፴፫ ዓ/ም የፍርድ ሚኒስትር ሆነው ተሾሙ። [6]

ብላታ አየለ ገብሬ በሎንዶንኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት አምሥተኛው ዋና መላክተኛ ሆነው ከመስከረም ፯ ቀን ፲፱፻፴፭ ዓ/ም ጀምሮ የኤርትራው ተወላጅ ብላታ ኤፍሬም ተወልደ መድኅን እስከተኳቸው ጥቅምት ፳፱ ቀን ፲፱፻፴፰ ዓ/ም ድረስ አገልግለው ወደኢትዮጵያ ሲመለሱ በሐረርጌ ጠቅላይ ግዛት ምክትል ገዥነት፤ የጠቅላይ ግዛቱም ገዥ እንደራሴ ሆነው እስከ ፲፱፻፵፯ ዓ/ም ሠርተዋል። ከዚህ ሥራ በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ ያመሩት ወደ ፍርድ ሚኒስትርነት ሲሆን እስከ ፲፱፻፵፱ ዓ/ም ድረስ በቆዩበት ወቅት በነጋሪት ጋዜጣ ቁ ፩/፲፱፻፶፪ በተለይ የወጣውን “የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት የፍትሐ ብሔር ሕግ” ቅንብር መርተዋል።

ከፍርድ ሚኒስትርነት ክቡር ራስ ቢትወደድ መኰንን እንዳልካቸው ሊቀ መንበርነት በሚመራው የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት በአባልነት ተዘዋውረው በዘውድ አማካሪነትም ሲሠሩ እስከ ፲፱፻፶፫ ዓ/ም ቆዩ። [7]

የሕይወት ፍጻሜ ለማስተካከል

በወንድማማቾቹ ጄነራል መንግሥቱ እና ገርማሜ ንዋይ የተጠነሰሰው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ማክሰኞ ታኅሣሥ ፬ ቀን ሲጀመር በገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት ከታሠሩት ለትላልቅ መሳፍንት፣ መኳንንቶችና ዋና ሚኒስቴሮች መኻል አንዱ ብላታ አየለ ገብሬ ነበሩ። ዓርብ ታኅሣሥ ፯ ቀን የሙከራው ኃይል እየተዳከመ በአንጻሩ ደግሞ ተቃዋሚዎቻቸው እያደር እየጎለመሱ መሄዳቸውን የተገነዘቡት ሽብርተኞች በቁጥጥራቸው ላይ የነበሩትን ሃያ መሳፍንት፣ መኳንንት፣ ሚኒስትሮችንና መኮንኖችን ወደ አረንጓዴ ሳሎን ካዛወሩ በኋላ ከተያዙት ሃያ ሰዎች ውስጥ ከተረሸኑት አሥራ-አምስት መኳንንትና ባለ-ሥልጣናት መኻል ብላታ አየለ ገብሬ አንዱ ነበሩ።

ማጣቀሻዎች ለማስተካከል

  1. ^ Encyclopaedia Aethiopica: A-C (2003) p 411
  2. ^ P. R. O., F.O. 37/20940/0040, [J 2157/2157/1] (1937)
  3. ^ Sbacchi (1997), pp 131, 135
  4. ^ ፍትህ ቅፅ ፭ ቁጥር ፻፹፬ ፤ ገጽ ፲፬
  5. ^ Sbacchi (1997), p 135
  6. ^ ደጃዝማች ከበደ ተሰማ፤ (፲፱፻፷፪ ዓ/ም)፤ ገጽ ፬፻፳፰
  7. ^ ደጃዝማች ደምስ ወልደ ዐማኑኤል (፲፱፻፶፩ ዓ/ም፤ ገጽ ፻፷፫ - ፻፹፭

ዋቢ ምንጭች ለማስተካከል

  • ታዴዎስ ታንቱ (ዶክቶር)፤ “አውደ ታሪክ” ፍትህ ቅፅ ፭ ቁጥር ፻፹፬ (ሚያዝያ ፲፪ ቀን ፳፻፬ ዓ/ም)
  • ከበደ ተሰማ (ደጃዝማች)፤ “የታሪክ ማስታወሻ” ፤ (፲፱፻፷፪ ዓ/ም)
  • ደምስ ወልደ ዐማኑኤል (ደጃዝማች) ፤ 'ሕገ መንግሥትና ምክር ቤት'፤ኹለተኛ መጽሐፍ ፥ አዲስ አበባጥቅምት፲፱፻፶፩ ዓ/ም
  • P. R. O., F.O. 37/20940/0040, [J 2157/2157/1] “Record of Leading Personalities in Abyssinia”.- (as amended by Addis Ababa Despatch No. 54 of March 18, 1937), May 4, 1937
  • Sbacchi, Alberto; “Legacy of Bitterness: Ethiopia and Facist Italy, 1935-1941” The Red Sea Press Inc. (1997)
  • Uhlig, Siegbert; Encyclopaedia Aethiopica: A-C (2003); “Ayyälä Gäbrä” By Aberra Jembere, & Shiferaw Bekele