የአዲስ አበባ ከተማ ማዘጋጃ ቤት
ታሪክ
ለማስተካከልየአዲስ አበባ ከተማ የሕዝብ እድገት፣ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴና የከተማዋ የቆዳ ስፋት እየጨመረ በመምጣቱ፣ ለንጉሱ ግብር ለማስገባት ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ወደ አዲስ አበባ የሚመጡ የክልል አስተዳዳሪዎችም በመብዛታቸው እነዚህን እንቅስቃሴዎች በአግባቡ ለማስተናገድ ዘመናዊ የከተማ አስተዳደር መመስረት ያስፈልጋል ተብሎ የአዲስ አበባ ከተማ ማዘጋጃ ቤት በ1909 ዓ.ም መጨረሻ ላይ ተመሰረተ፡፡ የማዘጋጃ ቤት አስተዳደር ከተመሠረተ በኋላ ሊዮ ሸፍኑ በተባለ አንድ ፈረንሳዊ እና እድሊቢ በተባለ ሶሪያዊ ግፊት ማዘጋጃ ቤቱ አድዋ ሲኒማ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ እንዲመሠረት ተደረገ፡፡ ማዘጋጃ ቤቱም የከተማው ማሕበር ቤት ተብሎ ይጠራ ነበር፡፡ ይህ ሥያሜ የተሰጠውም ማዘጋጃ ቤቱ እንዲመሰረት ግፊት ሲያደርጉ በነበሩት በሶሪያዊው እድሊቢ ነው፡፡ ተቋሙ የከተማ ማሕበር ቤት ተብሎ ቢሰየምም አንድም የከተማዋ ነዋሪ በአባልነት አለመመዝገቡ፣ ይልቁንም የማዘጋጃ ቤቱን ሥራ የሚያከናውኑት የመንግሥት ተቀጣሪዎችና የተለያዩ የውጭ አማካሪዎች በመሆናቸው፣ ለተቋሙ የተሰጠው የከተማው ማሕበር ቤት የሚለው ስያሜም “Municipality” የሚለውን የእንግሊዝኛ አቻ ቃል አይወክልም በሚል በወቅቱ ከንቲባ የነበሩት ኅሩይ ወልደሥላሴ (ብላቴን ጌታ) በ1920 ዓ.ም ማዘጋጃ ቤት የሚል ስያሜ እንደተሰጠው በታሪክ ሰፍሯል፡፡
ማዘጋጃ ቤቱ በወቅቱ ማዘጋጃ ቤታዊ የታክስ ምንጮችን መመስረትና ታክስ መሰብሰብ፣ ለውጭ ሰዎችና በንጉሱ እውቅና ለተሰጣቸው ባለሥልጣናት መሬት ማደል፣ የንግድ ፈቃድ መስጠት፣ ማዘጋጃ ቤታዊ የሆነ የፍትህ አገልግሎት ማዳረስ የመሳሰሉትን ተግባራት ያከናውን ነበር፡፡
ይህ ለአዲስ አበባ ከተማ እድገትና ለከተማዋ ህዝብ ደህንነት የተቋቋመው ማዘጋጃ ቤት በ1926 ዓ.ም የሚያከናውናቸውን ተግባራት በ16 ዋና ዋና የሥራ ክፍሎች በመከፋፈል ከ250 ባልበለጡ ሠራተኞች ሥራውን ያከናውን ነበር፡፡ እነርሱም የከንቲባ ጽ/ቤት፣ የርስት ክፍል፣ የካርታ ማንሳትና የግምት ክፍል፣ የመንገድ ክፍል፣ የሂሳብ ክፍል፣ የግምጃ ቤት፣ የዳኝነት ክፍል፣ የአራዳ ዘበኛ፣ የተሽከርካሪና የመንጃ ፈቃድ/የቁማር ጨዋታ ቁጥጥርን ጨምሮ/ክፍል፣ የጽዳት ክፍል፣ የህክምና ክፍል፣ የገንዘብና የሥራ መቆጣጠሪያ ክፍል፣ የምሥጢር ክፍል /ልዩ ጓዳ/፣ የውል ክፍል፣ የእሳትና አደጋ መከላከያ ክፍልና የጋራዥ ክፍል የተባሉት ነበሩ፡፡ እነዚህ የሥራ ክፍሎች ዋና ዋናዎቹ ሲሆኑ እያንዳንዱ ክፍል ንዑስ ቅርንጫፎች ነበሩት፡፡ ማዘጋጃ ቤቱ ከላይ የተዘረዘሩት ዋና ዋና ክፍሎች ይኑሩት እንጂ ለከተማዋ እድገት ሲያደርግ የነበረው እንቅስቃሴ አመርቂ እንዳልነበረ የተለያዩ ጽሁፎች ያስረዳሉ፡፡ ለዚህም ምክንያቱ ማዘጋጃ ቤቱ በራሱ ከሚያገኘው ገቢ ውጪ በመንግሥት የሚመደብለት የመተዳደሪያ በጀት ስላልነበረው ነው፡፡ በዘመኑ ያገኝ የነበረው የአገልግሎት ዋጋ ወይም ግብር የሚሰበሰበው ከተወሰኑ ድርጅቶች ብቻ ሲሆን የሚያስከፍለው ግብር ደግሞ በጣም አነስተኛ ነበር፡፡ በዘመኑ ገቢ የሚገኘው ማዘጋጃ ቤቱ ከሚያከራያቸው ከራሱ ቤቶች፣ ከንግድ ፈቃድ፣ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ካላቸው ቦታዎችና ከውጭ አገር ዜጐች ጋር ተቀጥረው ከሚሰሩ ኢትዮጵያውያን ብቻ ነበር፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ የቦታ ካርታ መሰጠት የተጀመረው በ1903 ዓ.ም ሱሆን፣ በ1920ዎቹ በዚህ ዙሪያ በርከት ያለ ገቢ አይሰበሰብም ነበር፡፡ በዚህ ሂደት አገልግሎቱን ሲሰጥ የቆየው የአዲስ አበባ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ከከተማዋ እድገት ጋር ተያይዞ የመጣውን የህዝቡን የከተማ ኑሮ ለማሻሻልና የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል አደረጃጀትና ሕንጻ ያስፈልገዋል ተብሎ ዛሬ በማገልገል ላይ የሚገኘው የማዘጋጃ ቤት ሕንፃ እንዲገነባ ጥቅምት 23 ቀን 1942 ዓ.ም በዓፄ ኃይለ ሥላሴ የመሠረት ድንጋይ ተጣለ፡፡ በዚህ ጊዜ የማዘጋጃ ቤት አማካሪዎች የሚባል ምክር ቤት የነበረ ሲሆን የም/ቤቱ ምርጫም በየዓመቱ የሚካሄድ ነበር፡፡ በወቅቱ ማዘጋጃ ቤቱ ለህዝቡ የሚሰጠውን አገልግሎት እያሰፋ የሄደ ሲሆን ለአብነት ያህልም ለማዘጋጃ ቤት ጥያቄ በማቅረብ በግለሰብ ደረጃ በየቤቱ የውሃ ቧንቧ ካስገባው የከተማዋ ነዋሪ በተጨማሪ ህዝቡ በነፃ በየሰፈሩ ውሃ የሚቀዳባቸው 58 የውሃ ማደያዎች /ቦኖ/ ነበሩ፡፡
እንዲሁም የኤሌከትሪክ ብርሃንን በተመለከተ የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ለከተማው መንገዶች ለሚሰጠው የመብራት አገልግሎት ማዘጋጃ ቤቱ ዋጋ ይከፍል ነበር፡፡ በወቅቱ አዲስ አበባ ውስጥ የነበረው የመብራት ኃይል 45,000 ቮልት ነበር፡፡
በዚያን ጊዜ ማዘጋጃ ቤት ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች አንዱ ድሆችን መጦር ሲሆን፣ የድሆች ጡረታ ቤት የሚባል የሥራ ዘርፍ በማቋቋም በከተማዋ ውስጥ ጠዋሪ የሌላቸውን ደካሞች ይረዳ ነበር፡፡ ለዚህም አገልግሎት በጊዜው 15693.00 ብር ያወጣ ነበር፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ ማዘጋጃ ቤት በዚህ ሂደት የአገልግሎት አድማሱን እያሰፋና በጀቱንም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሳደገ በመምጣት በአሁኑ ወቅት ለከተማዋ ነዋሪ የሚያስፈልጉ የተለያዩ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶችን በስፋት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡