ዳግማዊ ምኒልክ

ዳግማዊ ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ
(ከአፄ ምኒልክ የተዛወረ)

ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ==

ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ
ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ
ሥርወ-መንግሥት ሰሎሞን
አባት ንጉሥ ኃይለ መለኮት ሣህለ ሥላሴ
እናት ወይዘሮ እጅጋየሁ ለማ አድያም
የተወለዱት ነሐሴ ፲፪ ቀን [1992 ዓ.ም.
የሞቱት ታኅሣሥ ፫ ቀን ፲፱፻፮ ዓ.ም.
የተቀበሩት ታዕካ ነገሥት በዓታ ቤተ ክርስቲያን
ሀይማኖት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ክርስትና

==

ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ (ነሐሴ ፲፪ ቀን ፲፰፻፴፮ እስከ ታኅሣሥ ፫ ቀን ፲፱፻፮ ዓ.ም.) ከ፲፰፻፶፯ እስከ ፲፰፻፹፪ ዓ/ም የሸዋ ንጉሥ ከዚያም ከ፲፰፻፹፪ እስከ ፲፱፻፮ ዓ/ም የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ነበሩ።

ምኒልክ
ምኒልክ

«....ማንም ሰው ለመማርና ለመሠልጠን መድከም አለበት።» [1]፲፰፻፺፰ ዓ.ም ስለትምሕርት ያስነገሩት አዋጅ


«እናንተ አንድ ልብ ከሆናችሁ በምቀኝነት እርስ በርሳችሁ ተዋግታችሁ ካላለቃችሁ በቀር ኢትዮጵያን አገራችንን ለሌላ ለባእድ አትሰጧትም፤ ክፉም ነገር አገራችንን አያገኛትም። ነፋስ እንዳይገባባችሁ አገራችሁን በያላችሁበት በርትታችሁ ጠብቁ፤ ወንድሜ ወንድሜ እየተባባላችሁ ተደጋገፉ፤ የኢትዮጵያን ጠላት ተጋግዛችሁ ተደንበር መልሱ። የኢትዮጵያ ጠላት ባንዱ ወገን ትቶ ባንድ ወገን ቢሄድና ደንበር ቢገፋ፤ በኔ ወገን ታልመጣ ምን ቸገረኝ ብላችሁ ዝም አትበሉ፤ ያ ጠላት በመጣበት በኩል ኁላችሁም ሄዳችሁ አንድነት ተጋግዛችሁ ጠላታችሁን መልሱ እስከ እየቤታችሁ እስኪመጣ ዝም ብላችሁ አትቆዩ»

[2]

ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ፤ ግንቦት ፲ ቀን ፲፱፻፩ ዓ.ም.

ትውልድና አስተዳደግ

ለማስተካከል

ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ ከአባታችው ከሸዋው ንጉሥ ኃይለ መለኮት ሣህለ ሥላሴና ከእናታቸው ወይዘሮ እጅጋየሁ ለማ አድያም ቅዳሜ ነሐሴ ፲፪ ቀን ፲፰፻፴፮ ዓ.ም. ደብረ ብርሃን አካባቢ አንጎለላ ከሚባል ሥፍራ ተወልደው፤ በአንጎለላ መቅደላ ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ክርስትና ተነሱ።

አያታቸው ንጉሥ ሣህለ ሥላሴ የልጁን መወለድ ሲሰሙ “ምን ይልህ ሸዋ” በሉት ብለው ስም አወጡ። እሳቸው “…ምኒልክ በሚል ስም የሚነግሥ ንጉሥ ኢትዮጵያን ታላቅ ያደርጋታል” የሚል ትንቢት ስለነበር ‘ምኒልክ’ የኔ ስም ነው ብለው ነበር። ሆኖም፣ በህልማቸው ከልጁ ጋር አብረው ቆመው ከሳቸው ጥላ የልጁ ጥላ በልጦ፤ በእግር የረገጡትን መሬት ሲያለካኩ እሳቸው ከረገጡት ልጁ የረገጠው ረዝሞ አዩ። ከዚህ በኋላ “ምኒልክ የኔ ስም አይደለም። የሱ ነው። ስሙን ምኒልክ በሉት” ብለው አዘዙ ይላል ጳውሎስ ኞኞ “አጤ ምኒልክ” በተባለው መጽሐፉ (ገጽ ፲፪)

ምኒልክ እስከ ሰባት ዓመታቸው ድረስ መንዝ ውስጥ ጠምቄ በሚባል አምባ ከእናታቸው ዘንድ አደጉ።አያታቸው ንጉሥ ሣህለ ሥላሴ ሲሞቱ የሸዋውን አልጋ የምኒልክ አባት ንጉሥ ኃይለ መለኮት ሣህለ ሥላሴ ወረሱ።

ዓፄ ተዎድሮስጥቅምት ወር ፲፰፻፵፰ ዓ/ም ትግራይንና ወሎን አስገብረው፣ አቤቶ ምኒልክ ገና የአሥራ ሁለት ዓመት ልጅ ሳሉ፤ የድፍን አማራንና የወሎን ጦር አስከትተው የሸዋውን ንጉሥ ኃይለ መለኮትን ለማስገበር ሸዋ ገቡ። ሁለቱ መሪዎች ጦርነት ለመግጠም ተዘጋችተው ሲጠባበቁ ንጉሥ ኃይለ መለኮት ባደረባቸው ሕመም ጥቅምት ፴ ቀን አረፉ። በዚህ ጊዜ የሸዋ መኳንንት ሕጻኑን ምኒልክን ከጠላት እጅ እንዳይወድቅባቸው ይዘው ሸሹ፤ ዳሩ ግን ዓፄ ቴዎድሮስ እንደሚከታተሏቸው ስላወቁ ኅዳር ፴ ቀን ፲፰፵፰ ዓ/ም የልጅ ምኒልክ ሠራዊትና የዓፄ ቴዎድሮስ ሠራዊት በረከት ላይ ገጥሞ የምኒልክ ሹማምንት እነአቶ በዛብህ፣ እነአቶ አንዳርጋቸው ሁሉ ተያዙ። ልጅ ምኒልክም ለቴዎድሮስ ገባ።[3]

የምርኮ እና ስደት ዘመናት

ለማስተካከል

ዓፄ ቴዎድሮስ ለሳቸው ያልገበሩ ብዙ የሸዋ መኳንንት ስለነበሩ ይወስዱብኛል በሚል ፍርሀት ምኒልክን በሰንሰለት አሳሰሯቸው። ንጉሠ ነገሥቱ ግን ምኒልክ በመታሠሩ ሲያለቅስ እንዳደር ሲሰሙ አዝነው ሰንሰለቱን እንዲፈቱላቸው አዘዙ። በጥር ወር ፲፰፻፵፱ ዓ/ም መቅደላ ገብተው በቁም እሥር ይቀመጡ እንጂ ከቴዎድሮስ ልጅ ከመሸሻ ጋር አብረው አደጉ። ወዲያውም የደጃዝማችነት ማዕረግ ተሹመው በጥር ወር ፲፰፻፶፮ ዓ.ም የዓፄ ቴዎድሮስን ልጅ ወይዘሮ አልጣሽን አገቡ። በዚህ ሁኔታ እድሜያቸው ፳፪ ዓመታቸው ድረስ ለ አሥር ዓመታት ዓፄ ቴዎድሮስ ግቢ ኖሩ።

ዓፄ ቴዎድሮስ ምኒልክን እንደልጃቸው ያዩዋቸው እንደነበረና በታላቅ ጥንቃቄም እንዳስተማሯቸው እንደ ኢጣልያዊው ጉሌልሞ ማሳያ፤ ዓለቃ ወልደ ማርያም እና ዓለቃ ገብረ ሥላሴ የመሳሰሉ መስክረዋል። ምኒልክም ቴዎድሮስን እንደአባት ይወዷቸው እንደነበር ይገለጻል። በኋለኛው ጊዜ ዓፄ ቴዎድሮስ መሞታቸውን ሲሰሙ ንጉሥ ምኒልክ በጣም ማዘናቸውንና የመንግሥት ሐዘንም ማወጃቸው ተዘግቧል።

ከመቅደላ ማምለጥና በሸዋ ዙፋን መቀመጥ

ለማስተካከል

ደጃዝማች ምኒልክ መቅደላ ላይ ከባድ ዝናብ ጥሎ ባደረበት ሰኔ ፳፬ ቀን ፲፰፻፶፯ ዓ/ም በ’ቆቂት በር’ ከሃያ ተከታዮቻቸው እና ከእናታቸው ከወይዘሮ እጅጋየሁ ጋር አምልጠው ወደአባታቸው ወዳጅ ወደ ወሎዋ ገዥ ወይዘሮ ወርቂት አመሩ። ሆኖም ወይዘሮ ወርቂት በቴዎድሮስ እጅ ወድቆ የነበረውን ልጃቸውን አመዴ አሊ ሊበንን ማስፈቻ ይሆነኛል በሚል ምኒልክን እና ተከታዮቻቸውን በእስር ይዘዋቸው ነበር።

ወይዘሮ ወርቂት ዓፄ ቴዎድሮስ ልጃቸውን አስደብድበው ገደል ከተቱት የሚል ወሬ ሲሰሙ ቦሩ ሜዳ ላይ ምኒልክን ተቀብለው፣ “የሸዋ ሰው አውራህ መጥቷልና ደስ ይበልህ፣ ተቀበል” ብለው አዋጅ አስነግረው፣ አጃቢ አድርገው በመለከትና እምቢልታ አሳጅበው ከሸዋ ድንበር ድረስ ላኳቸው።

ሸዋን ‘ንጉሥ ነኝ’ እያሉ ይገዙ የነበሩት አቶ በዛብህ የምኒልክን ወደመሀል ሸዋ መግፋት ሲሰሙ ለመውጋት ጋዲሎ ከተባለ ሥፍራ ተሠልፈው ሲጠባበቁ፣ አንዲት ሴት

«ማነው ብላችሁ ነው ጋሻው መወልወሉ፣
ማነው ብላችሁ ነው ጦራችሁ መሾሉ
ማነው ብላችሁ ነው ካራችሁ መሳሉ፣
የጌታችሁ ልጅ ነው ኧረ በስማም በሉ»

ብላ ገጠመች። [4]

ውጊያው ጋዲሎ ላይ ነሐሴ ፲፮ ቀን ተፋፍሞ ሳለ ከአቶ በዛብህ ጋር ተሠልፈው የነበሩት የሸዋ መኳንንት “በጌታችን በኃይለ መለኮት ልጅ ላይ አንተኩስም” ብለው ወደምኒልክ ዞሩ። አቶ በዛብህም ሸሽተው አፍቀራ ገቡ፤ ድሉም የምኒልክ ሆኖ ምሥራቅ ምስራቁን ተጉዘው በድል አድራጊነት አባቶቻቸው ከተማ አንኮበር ገቡ። ንጉሥ ምኒልክም በአንኮበር ጥቂት ወራት ከተቀመጡ በኋላ ወደ ደብረ ብርሃን ወርደው አዲሱን ከተማቸውን ልቼን እያሠሩ ተቀመጡ።

ምኒልክ፣ ንጉሠ ሸዋ

ለማስተካከል

ተቃራኒያቸውን አቶ በዛብህን ጋዲሎ ላይ ድል ካደረጉ በኋላ፣ ንጉሥ ምኒልክ ታማኞት የሸዋ መኳንንትን በሚሠበስቡበትና በሚያዳብሩበት ጊዜ ትኩረታቸውን ዓፄ ቴዎድሮስ አሲዘው በመርሐ ቤቴ አውራጃ በደጃዝማች ወልደ ሚካኤል ሥር ያስጠብቋቸው የነበሩትን አጎታቸውን መርዕድ አዝማች ኃይለ ሚካኤልን ነጻ ለማውጣት ግንቦት ፳፩ ቀን ፲፰፻፶፱ ዓ/ም ከልቼ ዘመቱ። ያላንዳች ተኩስ አጎታቸውን ካስለቀቁ በኋላ ወደ ልቼ ተመልሰው መርዕድ አዝማቹ የቡልጋን ግዛት ተሰጣቸው።

ሚያዝያ ፯ቀን ፲፰፻፷ ዓ/ም ዓፄ ቴዎድሮስእንግሊዝን ጦር መቅደላ ላይ ገጥመው መሞታቸው ሲሰማ ንጉሥ ምኒልክ ወደ ወሎ ዘምተው ባላባቶቹን አስገብረው፣ ወረይሉን ቆርቁረው ወደ ሸዋ ተመለሱ። በኋላም አንደኛው የወሎ ባላባት መሐመድ አሊ (በኋላ ንጉሥ ሚካኤል) ገቡላቸውና ይማሙ ብለው ወሎን በሙሉ ሰጧቸው። ለመተማመኛም የወይዘሮ ባፈናን ልጅ ወይዘሮ ማናለብሽን ልጅ ዳሩላቸው።

ትግራይ ደጃዝማች ካሳ (በኋላ ዓፄ ዮሐንስ ሐምሌ ፬ ቀን ፲፰፻፷፬ ዓ/ም የቴዎድሮስን ተከታይ ዓፄ ተክለ ጊዮርጊስን ተዋግተው ድል ስላደረጉ ዮሐንስ ፬ኛ ተብለው የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ሆኑ።

ንጉሡ እና ዓፄ ዮሐንስ

ለማስተካከል

ምኒልክ እና ዮሐንስ ከመጀመሪያው ጀምሮ ለንጉሠ ነገሥትነት ሥልጣን ተወዳዳሪዎች ሲሆኑ ጠባያቸው የተለያየ እና እርስ በርስ የማይተማመኑ ነበሩ። ዓፄ ዮሐንስ ሟቹን ንጉሠ ነገሥት ቴዎድሮስን ሊወጋ የመጣውን የእንግሊዝ ሠራዊት በመርዳት ከሸኚ እና ስንቅ ጋር በግዛታቸው እንዲያልፍ በማድረጋቸው ወሮታውን ከድሉ በኋላ በዘመናዊ መሣሪያ፤ መድፍ እና ጥይት አበልጽጓቸው ሲሄድ በጊዜው ከነበሩት መሪዎች ሁሉ የላቀ ኃይል ለማግኘትና ያስከተለውንም የንጉሠ ነገሥትነት ዘውድ እጃቸው ለማስገባት አመቸላቸው።

ንጉሥ ምኒልክ ደግሞ ጊዜያቸው እስኪደርስ፤ ኃይላቸውን በዘመናዊ መሣሪያዎች እስከሚያዳብሩና ለንጉሠ ነገሥትነቱ ሥልጣን እስከሚዘጋጁ ድረስ ግዛታቸውን በደቡብ እና በምዕራብ አቅጣጫ እያስፋፉ በዘዴ ለንጉሠ ነገሥት ዮሐንስ ታማኝና የበታች መስለው መኖርን ያዙ።

በሁለቱ መሀል ግንኙነታቸው መካረር የጀመረው ዓፄ ዮሐንስ የንጉሥ ምኒልክን ገባር የበጌ ምድሩን ገዥ ራስ ወልደ ማርያምን ለማሳመን ከዘመቱ በኋላ ጎጃምን አሳምነው ወደ ሸዋ ለመምጣት ዘቢጥ ላይ ሲደርሱ ከወደኋላ የቱርክ ጦር መጣ የሚባል ወሬ ስለሰሙ ወደትግራይ ተመለሱ። ይማም አባ ዋጠውም (ንጉሥ ሚካኤል) ምኒልክን ከድተው ወደ ዓፄ ዮሐንስ ሲገቡ ምኒልክ ገስግሰው የጁ ላይ ደርሰውባቸው እጃቸውን ይዘው አስረው ወደሸዋ ሰደዷቸው፡

ምኒልክ ወዲያው መልሳቸውን በጎጃም አድርገው በጌ ምድር ዘመቱና ደብረ ታቦር ላይ ሳሉ ዓፄ ዮሐንስ መምጣታቸውን ሲሰሙ እንደገና ወደ ጎጃም ተሻገሩ። ወዲያውም ወደሸዋ ተመለሱ። ይሄኔ ነው ወይዘሮ ባፈና ምኒልክን ከድተው ካማቻቸው ከይማሙ መሐመድ አሊ ጋር ተማምለው ወደዓፄ ዮሐንስ መላላክ ጀምረው ነበር።እንዲሁም አጎታቸው የቡልጋው ገዥ መርዕድ አዝማች ኃይለ ሚካኤልም ሸፍተው አንኮበርን ይዘው ነበር።

መርዕድ አዝማቹ ሚጣቅ አፋፍ ላይ ሲያዙ ወይዘሮ ባፈና ደግሞ መርሐ ቤቴ ላይ ኮላሽ አምባ እምቢላው ሥፍራ ላይ የተከተሏቸው ወታደሮች አሠሯቸው። ንጉሡ ይማሙ መሐመድ አሊን ለመያዝ በግስጋሴ ተከታትለው ሲደርሱበት አምልጦ በመሄዱ ተናደው ከተማውን ደሴን አቃጠሉት።

ዓፄ ዮሐንስ ደብረ ታቦር ላይ ሳሉ ከሸዋ ከሦስት ወገን መልእክት ይደርሳቸው ነበር።

በአንዱ ወገን አቤቶ መሸሻ ሰይፉ እርስዎ ከመጡ በሸዋ የኔ ወገን ነውና የሚበዛው ከንጉሥ ምኒልክ ምንም የሚሰጉበት ነገር የለም ብሎ ልኮላቸዋል።

በሁለተኛው ወገን ደግሞ የ’ሁለት ልደት’ ኃይማኖት ወገኖች እርስዎ መጥተው የማርቆስን ኃይማኖት ቢያቀኑልን ነው እንጂ ንጉሥ ምኒልክ በአዳል በኩል አባ ማትያስ የሚባሉ ጳጳስ አስመጥተው ከ’ሦስት ልደት’ ወገኖች ጋር ተፋቅረዋል እያሉ ይልኩባቸው ነበር።

በሦስተኛው ወገን ከወይዘሮ ባፈና እና ከመርዕድ አዝማች ኃይሌ ጋር የመከሩ ሰዎች ቶሎ ካልደረሱልን ንጉሥ ምኒልክ ያጠፉናል እያሉ ልከውባቸው ነበር።

ዓፄ ዮሐንስ እንግዲህ በነኝህ ተነሳስተው ወደሸዋ ለመዝመት ቆረጡ። ምኒልክም በጥቅምት ወር ፲፰፻፸ ዓ/ም ላይ ወደወሎ ሲሻገሩ መሐመድ አሊ ሸሽተው ወደ ዓፄ ዮሐንስ ገቡ። ይማሙ አባ ዋጠው ግን ከምኒልክ ጋር ታርቀው ስለገቡ የወሎን ግዛት መልሰው ሰጧቸው። ወዲያውም በምስጢር ወደ ዓፄ ዮሐንስ መኳንንቶች እየተላላኩ የንጉሠ ነገሥቱን አሳብ በርግጥ ደሩበት። እነኚሁም መኳንንት ዓፄ ዮሐንስን መክረው በረግም መንገድ እንዲጓዙ ሲያደርጓቸው ምኒልክ ወደ መርሐ ቤቴ ወርደው መሸሻ ሰይፉን መውጋት ጀመሩ። ዳሩ ግን እዚያ ከመሸሻ ሰይፉ ጋር ሲዋጉ ንጉሠ ነገሥቱ ደርሰው አገሬን የጠፉብኛል በሚል ዕርቅ ለማድረግ መነኮሳት ልከውበት እሱንም ወይዘሮ ባፈናንም አስታረቋቸውና ሁሉም ወደ ልቼ ገቡ።

የሁለቱ ነገሥታት አለመግባባት እየተገለጠና እየሰፋ ሲሄድ አንዳንድ መነኮሳት የክርስቲያን ወገን ለምን ይፈሳል በሚል ተነሳስተው ሁለቱን ለማስታረቅ ተነሡ። ሆኖም ዓፄ ዮሐንስ የዕርቅ ወዝ እያሳዩ ወደፊት እየገሰገሱ ያለፉበትን አገር ሁሉ እያጠፉ ቀኝና ግራ እየወረሩ ከብቱን እየማረኩ ስለነበር ንጉሥ ምኒልክም ተናደው በአንጎለላ ሠራዊታቸውን ሁሉ ሰብስበው ሰልፍና ግባት አሳዩ።

ሆኖም ምኒልክ ዕርቅን ይፈልጉ ስለነበር መነኮሳትና ሊቃውንቶችን ሰብስበው ወደ ንጉሠ ነገሥቱ ላኩ። ዕርቁንም በተመለከተ የተነደፈው ውል ሁለት ነገሮችን ብቻ የተመለከተ ሲሆን፣ እንኚህም፦

(ሀ) ንጉሥ ምኒልክ ወደ ዓፄ ዮሐንስ ሄደው ላይገቡና ላይገናኙ፤ በዓፄ ዮሐንስም ላይ ጠላት ቢነሳ ንጉሥ ምኒልክ የጦር አብጋዛቸውን እየላኩ ሊረዱ እንጂ ራሳቸው ወደ ዘመቻ ላይሄዱ

(ለ) በኃይማኖት አንድ ሊሆኑና አባ ማስያስ የሚባሉትን የካቶሊክ ጳጳስ ካገራቸው አስወጥተው ሊሰዱ ነው።

አስታራቂዎቹ ገና ወደ ንጉሥ ምኒልክ ተመልሰው የእርቁን ድርድር ሳይናገሩና ሳያስወድዱ የዓፄ ዮሐንስ ሠራዊት ‘ጭሬ ደን’ የተባለውን ወንዝ ተሻገረ። በዚህ ጊዜ የንጉሥ ምኒልክ ሠራዊት፣ በተልይም የፈረስ ዘበኛው ፈንድቶ ወጥቶ ጦርነት ተጋጠሙና ከሁለቱም ወገን ብዙ ሰው ሞተ። ከዚህ በኋላ ዓፄ ዮሐንስ “ከወንድሜ ከንጉሥ ምኒልክ ጋራ ታርቄያለሁና ከንግዲህ ወዲህ አገር ያጠፋህ ከብት የዘርፍክ ወታደር ትቀጣለህ”” የሚል አዋጅ አስነገሩ።

የኃይማኖት ክርክር

ለማስተካከል

ሁለቱ ነገሥታት ከታረቁ በኋላ በ’ሁለት ልደት’ እምነትና በ’ሦስት ልደት’ እምነት የኃይማኖት ጉባዔ እንዲደረግ ስለተስማሙበት በግንቦት ወር ፲፰፻፸ ዓ/ም ቦሩ ሜዳ ላይ ሁለቱም ነገሥታት ቀኝና ግራ በተዘረጋላቸው ዙፋን ተቀመጡ።

ከሁለት ልደት ወገን አፈ ጉባዔው መልአከ ብርሃን ወልደ ዮሐንስ፤ ከሦስት ልደት ወገን ደግሞ ዓለቃ ወልደ ሐና ሆነው ቆሙ። ሁለቱም ወገኖች በየተራቸው ጥያቄ እያመጡ ከተከራከሩ በኋላ ኢየሱስ ክርስቶስ ሦስተኛ ልደት አለው የሚል ከቅዱሳት መፃሕፍት ምስክር ስላልተገኘ ሁለት ልደት አለው የሚለው ወገን ረታ። በኢሁም በጉባዔው ያለው ሁሉ ኃይማኖቴ ሁለት ልደት ነው እያለ ከዚያው ሳይወጣ ተገዘተ። ከደብረ ሊባኖስ ተይዘው የመጡት ዋልድቤ እንግዳ እና ዘራምቤ እንግዳ ተክለ አልፋ የሚባሉት ሦስት ልደት አለው የሚለውን እምነታችንን አንተውም ስላሉ ሦስቱንም ምላሳቸውን በመቁረጥ ሲቀጧቸው ዋልድቤ እንግዳ ያን ጊዜውን ሞቱ። ዙራምቤ እንግዳና ተክለ አልፋ ግን ከቦሩ ሜዳ ጉባዔ በኋላ ብዙ ዘመን ኑረው ሞቱ።

ንጉሠ ነገሥቱ ወዲያው በዚያው ዓመተ ምሕረት እስላምና ያልተጠመቀ ሁሉ እንዲጠመቅ የሚያስገድድ አዋጅ አሳውጀው በኢትዮጵያ ያለ እስላም ሁሉ አስከፉ። ጉልበት ያለውና በኃይማኖቱ የጸናውም ወደ መተማ እየተሰደድ ከደርቡሾች ጋር ተቀላቀለ። ሌላው ወደሐረር ወደ ዋቤ እና ወደ ጅማ ተሰደደ።

የወሎውም ባላባት ይማሙ መሐመድ አሊ በዚሁ አዋጅ መሠረት በዓፄ ዮሐንስ ክርስትና ተነስተው ስማቸው ሚካኤል ተባለ። ንጉሥ ምኒልክም ክዚህ መልስ ወረይሉ ሲደርሱ ኡለተኛውን የወሎ ባላባት ይማሙ አባ ዋጠውን ክርስትና ናስተው ስማቸው ኃይለ ማርያም አስብለው የወሎን እስላም ለማስተማርና ወደ ክርስትና ለመመለስ መምሕር አካለ ወልድን ሾመው በሰኔ ወር መጨረሻ በ፲፰፻፸፪ ዓ/ም ወደ ሸዋ ተመለሱ።

በንዲህ ዓይነት ሁኔታ ንጉሥ ምኒልክ ጊዜያቸው እስኪደርስ፤ ኃይላቸውን በዘመናዊ መሣሪያዎች እስከሚያዳብሩና ለንጉሠ ነገሥትነቱ ሥልጣን እስከሚዘጋጁ ድረስ ግዛታቸውን በደቡብ እና በምዕራብ አቅጣጫ እያስፋፉ በዘዴ ለንጉሠ ነገሥት ዮሐንስ ታማኝና የበታች መስለው መኖርን ያዙ።

ዓፄ ዮሐንስም የምኒልክን ‘ሰሎሞናዊ’ ሥልጣን ለመበረዝና ኃይላቸውንም የሚቃረን ኃይል ለመመሥረት ባቀዱት ሤራ መሠረት ከዚያ በፊት በአገሪቱ ታሪክ ያልነበረውን “የጎጃም የንጉሥ ስርዓት በመፍጠር ገዚውን ራስ አዳልን ለማንገስ ወሰኑ። ስለዚህም ጉዳይ ወደምኒልክ የጻፉት ደብዳቤ የሁለቱን ሁኔታ ሲያሳይ ዮሐንስ ምኒልክን በአክብሮት የሚያይዋቸው ቢሆንም ንጉሠ ነገሥቱ የራስ በራስ መተማመን እንደሚያንሳቸውና የመጨረሻው አንቀጽ ደግሞ ምኒልክንም እንደማያምኗቸው ያሳያል።

«መልእክተ ዘሥዩመ እግዚአብሔር ዮሐንስ ንጉሠ ጽዮን፤ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ። ይድረስ ከንጉሥ ምኒልክ በአማን እሥራኤላዊ ዘአሎ ጽልሁት። ሰላም ለከ ወሰላመ እግዚአብሔር የሀሉ ምስሌከ። እኔ በእግዚአብሔር ቸርነት በምነ ጽዮን አማላጅነት አምላከ ቅዱሳን ይክበር ይመስገን ደህና ነኝ። ምህረቱ ለዘላለም ነውና።

ራስ አዳልን በጥምቀት ዕለት የምሾመው የማንግሠው ነኝ። ሲሆን ቢሰላ አብረን ሁነን መሾም ይገባነ ነበር። ቀኑ የሚያጥር የማያዳርስ እንደሆነ አንድ ደህና ሰው ሁኔታውን ሁሉ የሚያይ ገስግሶ ለጥምቀት እንዲገባ ይሁን። እኔ ይህን ማለቴ ንጉሠ ነገሥት ተብዬ እኮራለሁ ብዬ አይደለም። አንድ ጊዜ ስሙም ወጥቶልኛል። የ እግዚአብሔር ኃይማኖቴ እንዲጸናና እንዲሰፋ አሕዛቦች እንዲጠፉ ብዬ ነው። ደግሞ ይህን ጉዳይ ካደርግነ በኋላ ወደ አምናችን የምመጣ ነኝና መምጣቱ የሚቸግር እንደሆነ ከዚያው እንድንገናኝ ይሁን።

ኢጣልያ ንጉሥ አምና በረከት ሰዶልኝ ነበር። ዕቃውን አኑኦ ሰዎቹን መልሶ ወሰዳቸው። ፍቅር ጀምሮ ሰዎቹን መልሶ መውሰዱ ብልሃቱ ጠፍቶብኛል። የዚህ ነገር ወደእርስዎ ይገኛል ይሆንን? ተጽሕፈ በአምባጨራ ከተማ። አመ ሰሙኑ ለታሕሣሥ ወር በ፲ወ፰፻፸ወ፫ ዓ/ም»

ከንጉሥነት ወደ ንጉሠ ነገሥትነት

ለማስተካከል
 
ዳግማዊ ዓፄ ምኒሊክ

ዓፄ ዮሐንስ በተለያየ ጊዜ፣ ባንድ በኩል የምስር (ግብጽ) ሠራዊት በግዛታቸው በምጽዋ በኩል፤ ባንድ በኩል ደርቡሾች በሌላ በኩል ደግሞ የእንግሊዝን ድጋፍ የያዙት ኢጣልያኖች ከአሰብ በቶሎ አልፈው ቤይሉል የሚባለውን የባሕር ጠረፍ ያዙ። ከነኚህ የውጭ ቀማኞች ጋር ክፉኛ ፍልሚያ ይዘው አንዳንዴ ሲያሸንፉ አንዳንዴም ሲገፏቸው ኖሩ።

፲፰፻፹፩ ዓ/ም ደምቢያ ሣር ውሐ ላይ ደርቡሾች ከንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ጋር ገጥመው አሸንፈው የፈጁትን የኢትዮጵያን የክርስቲያን አጽም አይተው እጅግ አዘኑ። ከዚያም ወደመተማ ገሠገሡ። አሳባቸው መተማን አጥፍተው ወደ ትልቁ ከተማ ኦምዱርማን ለመሄድ ነበር። መጋቢት ፩ ቀን ፲፰፻፹፩ ዓ/ም ቅዳሜ ጦርነት ገጥመው የከተማውን ቅጥር ጥሰው ከገቡ በኋላ በጠመንጃ ጥይት ተመተው ቆሰሉ። ወሬውም ያንጊዜውን በየሠልፉ ውስጥ ሲሰማ መኳንንቱም ወታደሩም ከቅጥሩ ውስጥ እየወጡ መሸሽ ጀመሩ። በማግሥቱ እሑድ መጋቢት ፪ ቀን አረፉ። ደርቡሾቹም የንጉሠ ነገሥቱን ሬሳ ከማረኩ በኋላ ራሳቸውን ቆርጠው በእንጨት ላይ ሰክተው ገበያ ለገበያ መንደር ለመንደር እያዞሩ ሲያሳዩ ዋሉ።

ንጉሥ ምኒልክም ዓፄ ዮሐንስ ወደመተማ ሲዘምቱ ምናልባት ድል የሆኑ እንደሆነ ደርቡሽ ተከታትሎ ወጥቶ በጌ ምድርን እንዳያጠፋና ሕዝበ ክርስቲያኑንም እንዳይገድል በወሎና በበጌ ምድር ወሰን ሆነው ለመጠባበቅ ሲሉ ቀውት የሚባል ሥፍራ መጋቢት ፲፯ ቀን ሲገቡ የንጉሠ ነገሥቱን መሞት አረዷቸው። ለአራት ቀናትም በኀዘን ሰነበቱ።

ጳውሎስ ኞኞ “አጤ ምኒልክ” በተባለው መጽሐፉ የንግሡን ስራት ሲተነትን፤ ከዚያም መልስ የንግሥ በዓሉ ስርዓት እየተዘጋጀ ከርመው ጥቅምት ፳፭ ቀን ፲፰፻፹፪ ዓ/ም በእንጦጦ ርዕሰ አድባራት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን በተፈጸመው ስርዓት በጳጳሱ አቡነ ማቴዎስ እጅ የወርቅ ሰይፍ ታጥቀው፤ በወርቅ ሽቦ የታሸቡ ሁለት ጦሮች ጨብጠው፤ የወርቅ ዘንግ ከተሰጣቸው በኋላ ቅብዐ መንግሥቱን ተቀብተው፣ “ሞአ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ፤ ዳግማዊ ምኒልክ ሥዩመ እግዚአብሔር ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ” ተብለው የወርቅ ዘውድ ተደፋላቸው።

የቅዳሴውም ስርዓት ከተፈጸመ በኋላ ዓፄ ምኒልክ በውጭ አገር በአምስት ሺ ብር የተሠራ ካባቸውን ለብሰው፣ ባለወርቅ ጥላ ተይዞላቸው ዘውዳቸውን ደፍተው የወርቅ ዘንግ ይዘው የወርቅ ጫማ አድርገው ካህናቱ ከፊትና ከኋላ እያጠኑ በራሶችና ደጃዝማቾች ታጅበው ከቤተ ክርስቲያኑ ብቅ አሉ። እጅግ በጣም በዝቶ የተሰበሰበው ሕዝብም የዘንባባ ዝንጣፊ እየያዘ “ሺህ ዓመት ያንግሥዎ” እያለ ደስታውን በእልልታና በሁካታ ገለጠ።(ገጽ ፻) ይልና “ከቤተ መንግሥታቸው ውስጥ ከተዘጋጀው የግብር ማብሊያ ዳስ ገብተው ከተዘጋጀላቸው ዙፋን ላይ ሲቀመጡ ፻፩ ጊዜ መድፍ ተተኮሰ። ከመድፎቹ መተኮስ ጋርም ጠቅላላው ሠራዊት የያዘውን ጠመንጃ በተኮሰ ጊዜ የጭሱ ብዛት እንደ ደመና ሆነ።” ብሎ አስፍሮታል።

የዳግማዊ ምኒልክ ዘመን

ለማስተካከል
 
በአጼ ምኒልክ ዘመን የተቀናው (የተመለሰው) ግዛት

የአድዋ ጦርነት

ለማስተካከል

ታሪከ ዘመን ዘዳግማዊ ምኒልክ የተባለውን መፅሃፍ በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን፤ የኢትዮጵያ መንግሥት የጽሕፈት ሚኒስተር በነበሩት በፀሓፌ ትእዛዝ ገብረ ስላሴ ወልደ አረጋይ በአማርኛ የተፃፈ የዳግማዊ ምኒልክ ታሪክ ነው። መጽሐፉ በ288 ገፆች የተደጎሰና በተለያዩ ፎቶዎች የተደገፈ ሲሆን ፥ የተለያዩ ታሪካዊ ክስተቶችና ጸሓፊዉ የአይን እማኝ የነበሩበት ስለአድዋ ጦርነት ዝግጅትና ክናዋኔ በሰፊዉና በዝርዝር መረጃ የሚዳስስ ነዉ፡፡የአድዋ ጦርነት

==የ መኪና ስልክ ዘመናዊ ትምህርት ቤት እና ሌሎችም በጣም ብዙ ስራዎች ሰርተዋል።

የዕምዬ ምኒልክ ዘመን ፍጻሜ

ለማስተካከል

አቶ ተክለጻድቅ መኩርያ ስለ ዕምዬ ምኒልክ ዜና ዕረፍት፣ «ዐፄ ምኒልክና የኢትዮጵያ አንድነት» መጽሐፍ ላይ ካሠፈሩት ሀተታ የሚከተለው ይገኝበታል።

ንጉሠ ነገሥት በ፲፱፻ ዓ/ም የጀመራቸው በሽታ እየጸና ሔዶ በመጨረሻ ሰውነታቸው ዝሎ፣ አንደበታቸው ተዘግቶ እንደቆየ በታኅሣሥ ፫ ቀን ፲፱፻፮ ዓ/ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ። የሸዋ ንጉሥ (፲፰፻፶፯-፲፰፻፹፩) በኋላም፣ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት (፲፰፻፹፪-፲፱፻፮) በነበሩበት ዘመን ሁሉ ክፉውን በክፉ ሳይሆን፣ ክፉውን በደግነት እየመለሱ ጥፋትን ሁሉ በትዕግሥት እያሸነፉ፣ አገር የሚሰፋበትን ልማት የሚዳብርበትን፣ ሕዝብ ዕረፍትና ሰላም የሚያገኝበትን ከማሰብና ከመፈጸም አልተቆጠቡም። የአውሮፓን ኃያል መንግሥት በጦር ሜዳ በማሸነፍ ኢትዮጵያን በዓለም እንድትደነቅ አድርገዋል።

የዳግማዊ አፄ ምኒልክን ዜና ዕረፍት በወቅቱ ለመደበቅ ቢሞከርም ወሬው ካንዱ ወደሌላው እየተላለፈ ነገሩን የተረዳው ሁሉ፣ «እምዬ ጌታዬ፣ እምዬ አባቴ» እያለ በየቤቱ ያለቅስ ነበር። ከአልቃሾቹ አንዱ፣ «ፈረስ በቅሎ ስጠኝ ብዬ አለምንህም አምና ነበር እንጂ ዘንድሮ የለህም፤» አለ ይባላል። በንጉሠ ነገሥቱም ሞት ዋናዎቹ ሐዘንተኞች ባለቤታቸው እቴጌ ጣይቱ፣ ልጃቸው ወይዘሮ ዘውዲቱና ብዙ መኳንንት አሉ። በልቅሶውም ጊዜ እቴጌ ጣይቱ፣ ‹‹ነጋሪት ማስመታት፣ እምቢልታ ማስነፋት ነበረ ሥራችን፣ ሰው መሆን አይቀርም ደረሰ ተራችን›› ብለው ገጠሙ ይባላል።

ልጅ ኢያሱ ቀጥለው ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ወለቱ ለምኒልክ ተብለው የነገሡት ልጃቸው ወይዘሮ ዘውዲቱ የሚከተለውን ሙሾ አወረዱ። ሙሾውም በ«ዐፄ ምኒልክና የኢትዮጵያ አንድነት» መጽሐፍ ላይ እንዲህ ተከትቧል

«እልፍ ነፍጥ በኋላው፣ እልፍ ነፍጥ በፊት፣ ባለወርቅ መጣብር አያሌው ፈረስ፣
ይመስለኝ ነበረ ይኼ የማይፈርስ።
ሠላሳ ሦስት ዘመን የበላንበቱ የጠጣንበቱ፣
የትሣሥ ባታ ለት ተፈታ ወይ ቤቱ።
ብትታመም ልጅህ እጅግ ጨነቀኝ፣ ብትሞትስ አልሞትም እኔ ብልጥ ነኝ።
ወልደውኛል እንጂ እኔ አልወለድሁዎ፣ አንዠቴን ተብትበው ምነው መሔድዎ።
አሳዳጊ አላንተ አላውቅም እናት፣ ምነዋ ሞግዚቴ እንዲህ ያል ክዳት።
ቀድሞ የምናየው የለመድነው ቀርቶ፣ እንግዳ ሞት አየሁ ካባቴ ቤት ገብቶ።
እጅግ አዝኛለሁ አላቅሽኝ አገሬ፣ የሁሉ አባት ሞቶ ተጐዳችሁ ዛሬ።
ትንሽ ትልቅ አይል ለሁሉ መስጠት፣ ከጧት እስከ ማታ ያለመሰልቸት።
ድርቅ ሆኗል አሉ ዘንድሮ አገራችሁ፣ ዝናሙ ሲጠፋ ምነው ዝም አላችሁ።
አሻግሬ ሳየው እንዲያ በሰው ላይ
መከራም እንደሰው ይለመዳል ወይ።»[5]

ድምፅ ሰነድ

ለማስተካከል

ማመዛገቢያ

ለማስተካከል
  1. ^ "ተፈሪ መኮንን - ረዥሙ የሥልጣን ጉዞ"፣ ዘውዴ ረታ (፲፱፻፺፱ ዓ/ም) ገጽ ፬፻፸፯"፣
  2. ^ አፈወርቅ ገብረኢየሱስ፣ (፲፱፻፩ ዓ/ም) ገጽ ፻፲፬
  3. ^ የቴዎድሮስ ታሪክ፣ በብርሊን እንደሚገኝ አብነት አሳታሚው ዶክቶር እኖ ሊትመን። በ፲፱፻ ወ ፪ ዓመት፣ ገጽ ፳፬
  4. ^ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ (ብላቴን ጌታ)(፲፱፻፺፱ ዓ/ም) ገጽ ፺፰
  5. ^ Minilik Wuhibe Slassie facebook.com

ዋቢ መፃሕፍት

ለማስተካከል