ከነዓን (የካም ልጅ)
ከነዓን በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት የካም ልጅና የኖህ ልጅ-ልጅ ነበረ። በዛሬው እስራኤልና ሊባኖስ ያለው አገር በጥንት ስለ ስሙ ከነዓን ይባል ነበር።
የከነዓን በኩር ልጅ ሲዶን ሲሆን ሲዶና ከተማ እንደ ተመሠረተና የፊንቄ አባት እንደ ሆነ ተብሏል። እንዲሁም ኬጢ ወይም ኬጢያውያን፣ አሞራዊው ወይም አሞራውያን የተባሉት ሕዝቦች ከከነዓን ተወለዱ። ከዚህ በላይ ኢያቡሳውያን፣ ጌርጌሳውያን፣ ኤዊያውያን፣ ዐሩኬዎን (ዐርካዊው)፣ ሲኒ፣ አራዴዎን፣ ሰማሪዎን፣ እና አማቲ የተባሉት ዘሮች ከከነዓን ወጡ።
በኦሪት ዘፍጥረት ኖህ በአራራት ተራራ ሰክሮ ስለ ካም ጥፋት ከነዓንን ረገመው። በመጽሐፈ ኩፋሌ ደግሞ ከነዓን ከወንድሞቹ ጋር በግዮን ማዶ ለመስፈር እምቢ ብሎ በአርፋክስድ ሴም ርስት ውስጥ በመቀመጡ ይረገማል።
በኢትዮጵያ ልማዳዊ ታሪክ፣ የከነዓን ልጅ አርዋዲ (አራዴዎን) እና ሚስቱ ኤንቴላ ከእስያ ወደ ኢትዮጵያ በ2108 ዓክልበ. ተሻገሩ። የቅማንት ብሔር ከልጃቸው አናየር እንደ ተወለዱ ይተረካል። ኢትዮጵያ በኩሽ ልጆች በተገዛችበት ዘመን 2 ሌሎች ከነዓናዊ ነገዶች የገቡ ከሲኒ ሻንጉል፣ ከሳምሪ (ሰማሪዎን) ወይጦ መሆናቸው የሚመስክር ልማድ አለ።
በአውሮፓ ልማዳዊ ታሪክ ደግሞ፣ የከነዓን ልጅ ዐርካዊው (አርካድ) መጀመርያ በአርካድያ (ግሪክ) ሠፈረ፣ ወንድሙም አማቲ በኤማጥያ (መቄዶን) ሠፈረ። ይህ ከተሞች በሊባኖስ (አርቃና ሐማት) ከሠሩ በኋላ ነበር ይባላል።
የፋርስ ሊቅ አል-ታባሪ (907 ዓ.ም. ግድም) የተረከው፣ የከነዓን ሚስት አርሳል ስትባል ይቺ የቲራስ ልጅ ባታዊል ሴት ልጅ እንደ ነበረች እርስዋም «ጥቁሮች፣ ኖባውያን፣ ፌዛን፣ ዘንጅ፣ ዛግሃዋህና የሱዳኑ ሕዝቦች ሁሉ» እንደ ወለደችለት ነበር።