ጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድኢትዮጵያ ፖለቲካ ሰው ሲሆኑ በ ጣልያን ወረራ ጊዜ አምስቱን ዓመት ሙሉ በፓሪስኢትዮጵያ ጉዳይ ፈጻሚ፤ በዠኔቭዓለም መንግሥታት ማኅበርኢትዮጵያ ዋና ጸሐፊ ከድል በኋላም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርነት እና እስከ አብዮት ፍንዳታ ድረስም በዓፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስቴር ነበሩ። ከአብዮቱ ፍንዳታ በኋላ አቃቂ ታስረው ከቆዩ በኋላ ያለፍርድ ኅዳር ፲፬ ቀን ፲፱፻፷፯ ዓ/ም ከስልሳ ሰዎች ጋር በደርግ ተረሽነው ሞቱ።

ጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ

የተማሪነት ዘመናት ለማስተካከል

አክሊሉ መጋቢት ፭ ቀን ፲፱፻፬ ዓ/ም በሸዋ ጠቅላይ ግዛት ቡልጋ ከተወለዱት አለቃ ሀብተወልድ ካብትነህ እና ከወይዘሮ ያደግድጉ ፍልፈሉ ተወልደው የአማርኛ ትምህርታቸውን አዲስ አበባ በሚገኘው የራጉኤል ቤተ ክርስቲያን አጠናቀቁ። ከዚያም በዳግማዊ ምኒልክ ትምሕርት ቤት ለሦስት ዓመታት ዘመናዊ ትምሕርት ከተከታተሉ በኋላ በ፲፱፻፲፯ ዓ/ም ወደ እስክንድርያ ትምሕርታቸውን እዚያ በሚገኘው የፈረንሳይ “ሊሴ” ትምህርት ቤት እንዲቀጥሉ በአልጋ ወራሽ ራስ ተፈሪ መኮንን ተላኩ። እስክንድርያም እስከ ፲፱፻፳፫ ዓ/ም ከተማሩ በኋላ የሊሴ ትምሕርታቸውን አጠናቀው ለከፍተኛ ትምሕርት ወደ ፓሪስ እና ታዋቂው ሶርቦን ዩኒቨርሲቲ አምርተው የከፍተኛ የንግድ ሕግ እና ሽከታኪን (political science)[1] ትምሕርት ጀመሩ። ሶርቦን እስከ ፲፱፻፳፰ ዓ/ም ድረስ ተምረው የመጀመሪያ ሲማክቶ ጉላፕ (BA degree )[2] በሸከታኪን እንዲሁም የ ሲማሕግ ጉላፕ (bachelors degree in law)[3] ተመርቀው ወጡ። ወዲያው ፋሽሽት ኢጣልያ ሀገራችንን ይወርና ወጣቱ አክሊሉ ሀብተወልድ ለውድ አገራቸው ነጻነት የአርበኝነት ትግላቸውን በቶፍካ (diplomacy)[4] እና በገቢ ሰብሳቢነት እዚያው ፈረንሳይ አገር ተሰማሩ።

በዓለም መንግሥታት ማኅበር የኢትዮጵያ ዋና ፀሐፊ ለማስተካከል

በጦርነቱ ዋዜማ ኢትዮጵያ በዓለም መንግሥታት ማኅበር ሸንጎ ጣልያን በግፍ ልትወራት መነሳቷን እና በማኅበሩ ‘የጋራ ደህንነት’ ዋስትና (collective security principle) መሠረት አባላት አገሮች መሃል ገብተው ጣልያንን እንዲያስታግሱ በምትከረከርበት ጊዜ አክሊሉ በፈረንሳይ አገር ውስጥ ተማሪ ሆነው ሳሉ ለሀገራቸው የሚያደርጉትን ትግል በመመልከት ንጉሠ ነገሥቱ፤ በዠኔቭ የኢትዮጵያ ልዑካን መሪ ፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት ተክለ ማርያም ሥር ዋና ፀሐፊ አደረጓቸው። ፊታውራሪው ያንጊዜ በፈረንሳይ፣ በብሪታንያ እና በዠኔቭ የኢትዮጵያ ዋና ልዑክ ነበሩ። ጦርነቱ በይፋ ከመጀመሩ በፊት ወደዠኔቭ እየሄዱ በኢትዮጵያ ስም ከጣልያን ጋር በዓለም መንግሥታት ማኅበር ሸንጎ ይሟገቱ የነበሩት እነዚህ ሁለቱ ስዎች ነበሩ። ፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት ወደአገራቸው ሲመለሱና ብላቴንጌታ ወልደ ማርያም በፓሪስ የኢትዮጵያ አምባሳዶር ሲሆኑ አክሊሉ የ”ፕሬስ አታሼ” ሆነው እንዲሠሩ ንጉሠ ነገሥቱ ቢያዟቸውም አምባሳደሩ “እምቢ ብለው አላስገባም አሉኝ። ቢሆንም እውጭ ሆቴል ቁጭ ብዬ እንደፕሬስ አታሼ ሆኜ ሥሠራ ነበር።” ( መስከረም ፲ ቀን ፲፱፻፷፯ ዓ/ም ለደርግ የምርመራ ኮሚሽን ‘ዓለም በቃኝ’ እስር ቤት ሆነው በላኩት የታሪክ ማስተወሻተው) የሚሉን አክሊሉ ሀብተወልድ በዚሁ ሥራ አፈ ቀላጤ (spokesperson) ሆነው ለጋዜጠኞች ማብራሪያ እና ቃለ ምልልስ በመስጠት የኢትዮጵያን አቋም እና የተሰነዘረባትን ግፈኛ ድርጊት ማስተዋወቃቸውን ቀጠሉ።

ለመሆኑ ብላቴንጌታ ወልደ ማርያም ለምን ይሆን አክሊሉን አላስገባም ያሉት። ምናልባት ንጉሠ ነገሥቱ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ “ሕይወቴና የኢትዮጵያ እርምጃ - ሁለተኛ መጽሐፍ” በተባለው መጽሐፋቸው ላይ “በፓሪስ የኛ ሚኒስቴር የነበረው ብላቴንጌታ ወልደማርያም አየለ እኛን ከድቶ ለጣልያኖች በገባ ጊዜ በዓለም መንግሥታት ማኅበር የኢትዮጵያ ጸሐፊ አቶ አክሊሉ ሀብተወልድ በፓሪስ የኢትዮጵያ ጊዜያዊ ጉዳይ አስፈጻሚ ሆኖ አገልግሎናል።” ብለው ያሠፈሩት ምክንያቱን ይጠቁም ይሆናል።

በወቅቱ የፈረንሳይ ጠቅላይ ሚኒስቴር የነበረው ፒዬር ላቫል እና የብሪታንያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሳሙኤል ሆር በ ታኅሣሥ ወር ፲፱፻፳፯ ዓ/ም በምስጢር ዶልተው አዘጋጅተውት የነበረውን፤ ኢትዮጵያን የሚበልጠውን አገር (ሐረርን፣ ሲዳሞን፣ ባሌን) ለጣልያን ሰጥታ ጎጃምን፣ ጎንደርን እና ትግሬን አስቀርታ ተጣልያን ጋር እንድትታረቅ የሚደነግገውን የ”ሆር-ላቫል” ስምምነት የሚባለውን ለጃንሆይ መስጠታቸው ሲሰማ አክሊሉ ሀብተወልድ ማዳም ታቡዴስ ለምትባለው የ”ራዲካል ፓርቲ” ጋዜጣ ኃላፊ ለነበረችው ታዋቂ ጋዜጠኛ በምስጢር ይገልጹላትና እሷ ሎንዶን ላይ በጋዜጣና በራዲዮ ይፋ አደረገችው። ጉዳዩ በብሪታንያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትልቅ ውዝግብና ሙግት ተደርጎበት ሆርም ምክር ቤቱን ይቅርታ እንዲጠይቅና ስምምነቱም እንዲወድቅ አድርጎታል።

የጠላት ዘመን ለማስተካከል

ሚያዝያ ወር ፲፱፻፳፰ ዓ/ም መደምደሚያ የፈረንሳይ የሕግ አውጪዎች ምክር ቤት አባላት ምርጫ በሚካሄድበት ጊዜ ወጣቱ አክሊሉ ለሦስቱ ዋና ፓርቲዎች የወቅቱ የፈረንሳይ ጠቅላይ ሚንስቴር የነበሩት ፒዬር ላቫል ሙሶሊኒን ለማስደሰት ሲል ኢትዮጵያን በመሸጥ “የጋራ ደህንነት” (collective security) የተባለውን የዓለም ጸጥታው ምክር ቤትን ዓላማ ማድከሙን፤ የኢትዮጵያ አቤቱታ እንዳይታይ እያደረገ እንደነ ሙሶሊኒና ሂትለርን እንዳበራታ ፣ በዚህም የዓለም ጦርነትን እንዲፋጠን ማድረጉን በዝርዝር ማስረዳትና ለፓርቲዎቹም የላቫልን መንግሥት ለመገልበጥ መሣሪያ መስጠት ለኢትዮጵያ ታላቅ ጥቅም እንደሚሰጥ በመገንዘብ በነዚህ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ስብሰባ እየተገኙ የኢትዮጵያን እሮሮ ማሰማት ጀመሩ። የፈረንሳይም ጋዜጦች እነኚህን ስብሰባዎች በሚዘግቡ ጊዜ የአክሊሉ ሀብተወልድን ንግግርም ጨምረው ሲያትሙ ሀገራቸው የደረሰባትን የግፍ ወረራ ለመላው የፈረንሳይ ሕዝብ ሲያስተዋውቁ ቆዩ።

አዲስ የተመረጠውን የፈረንሳይ ጠቅላይ ሚኒስቴር ሊዮን ብሎምን አነጋግረው ፈረንሳይ የሙሶሊኒ ፋሽሽት ኢጣልያ መንግሥት በኢትዮጵያ ላይ ያላትን ይዞታ መቼም ቢሆን እንደማያውቅ አረጋግጦላቸዋል። ወዲያው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በስደት ወደብሪታንያ ሲመጡ አክሊሉም በዚያው በፓሪስ የኢትዮጵያ ጉዳይ ፈጻሚ ሆነው ሲያገለግሉ ቆዩ። መስከረም ፲ ቀን ፲፱፻፷፯ ዓ/ም ለደርግ የምርመራ ኮሚሽን ‘ዓለም በቃኝ’ እስር ቤት ሆነው በላኩት የታሪክ ማስተወሻተው እንደነገሩን፤ “በ፲፱፻፴ ዓ/ም የእንግሊዝ ንጉሥና ንግሥት በግብዣ ለጉብኝት ፓሪስ በመጡ ጊዜ ተሌሎች አምባሳደሮች ጋር እኔም ተጠርቼ ሄጄ ነበር። በፕሮቶኮሉ ደንብ የኢትዮጵያና የጣልያን ጉዳይ ፈጻሚዎች አቀማመጣቸው ጎን ለጎን ስለነበር አጠገቡ በምሆንበት ጊዜያት ጣልያኑ በጣም ሲቆጣ እኔም ኃይለኛ ቃል ስለተናገርኩት ጠቡን ሁሉም ሰምተው የፕሮቶኮሉ ሹም በመካከላችን የሌላ አገር ጉዳይ ፈጻሚ አስቀመጠ።”[5] ይላሉ

በወቅቱ ጣልያኖች በኢትዮጵያ ላይ “ኋላቀር፤ ባርያ ሻጭ፤ አውሬዎች…. የኛ ተልዕኮ ኢትዮጵያን ማሰልጠን ነው….” እያሉ ፕሮፓጋዳቸውን ያዛምቱ ስለነበር የፈረንሳይ ሕዝብ ስሜቱን ለኛ ስሞታውን ወደነሱ አዙሮ ነበር። ይሄንን በዘለቄታማና ስኬታማ መንገድ ለመከላከል አክሊሉ (ሀ) ከልዩ ልዩ ጋዜጮች ጋር በመገናኘት እውነቱን በማስረዳት (ለ) ተነ ሙሴ ጃንጉል (በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ በማስታወቂያ ሚኒስቴር ሥር የፈረንሳይኛ ጋዜጣ ያቋቋመ) እና ከሌሎች ፈረንሳዮች ጋር በመተባበር ኢትዮጵያን የሚረዱ ሁለት ኮሚቴዎች (comité d’action Ethiopie እና association du peuple Ethiopie) በማቋቋምና በነዚህ ኮሚቴዎች በኩል የኢትዮጵያን ጉዳይ በብዙ ሺህ ለሚቆጠሩ ፈረንሳዮች በማሰራጨት የሕዝብ ዕርዳታ ለማስገኘት ችለዋል። (ሐ) በነዚሁ ኮሚቴዎች ዕርዳታና መሥራችነት የኢትዮጵያን አቋምና የጣልያንን ግፍ በየጊዜው የሚያስረዳ “ኑቬል ደ ኤትዮፒ” (የኢትዮጵያ ዜና) የሚባል ጋዜጣ ተመሠርቶ እሳቸውም በየጊዜው በጋዜጣው ይጽፉ ነበር።

ከድል በኋላ ለማስተካከል

የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሲያከትም የተሸናፊዎቹን የጀርመንን እና የጣልያንን ይዞታ፤ የካሳ ጉዳይ እና በድል ጊዜ ከጣልያን ወደ እንግሊዝ አስተዳደር ተላልፈው የነበሩትን የኤርትራን እና የኦጋዴንን ጉዳይ ለመወሰን በየተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መሪነት “የሰላም ጉባዔ” በሚካሄድበት ጊዜ አቶ አክሊሉ ሀብተወልድ መጀመሪያ በፓሪሱ ጉባዔ በታዛቢነት በመጨረሻም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርነት አዲሱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በተመሠረተበት በሳን ፍራንሲስኮ ከተማ የኢትዮጵያን ልዑካን በመምራት ተሳትፈዋል።

አክሊሉ ሀብተወልድን ትልቅ የዲፕሎማሲ ሰው መሆናቸውንና በዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ መድረኮች ለኢትዮጵያ ብዙ መታገላቸውን የሚያስመሰክርላቸው ዘመን የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ካከተመበት ጊዜ ጀምሮ የኤርትራ እና የኢትዮጵያ በኅብረታዊ መንግሥት የመዋሐድ ጉዳይ እስከተፈረመበት ኅዳር ወር ፲፱፻፵፪ ዓ/ም ድረስ የነበረው ዘመን ነው። አክሊሉ በእንግሊዝና በኢጣሊያ ተሸንሽና የነበርቸውን አገራቸውን ረጅም ዓመት የፈጀ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት በማድረግ አንድ ያደረጉ ታላቅ ዲፕሎማት እንደነበሩ ስለሳቸው ብዙም የተጻፈ መረጃ ማግኘት ቢያስቸግርም በአምባሳደር ዘውዴ ረታ የተጻፈው ‘የኤርትራ ጉዳይ’ የተባለው መጽሐፍ ስለኚህ ሰው ታላቅ ተጋድሎ በሰፊው ተዘርዝሮ ይገኛል :: አምባሳዶር ዘውዴ የኤርትራን ጉዳይ በተመለከተው በዓለም መድረክ ላይ ይካሄድ ስለነበረው ትግል ሲጽፉ ፤ በዚያን ጊዜ በአካባቢ ቡድን ብዛት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኃይል የነበራቸው የላቲን አሜሪካ አገሮች የጣልያን ወገን በመሆን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩን አክሊሉ ሀብተወልድን እጅግ በጣም ቢያናድዷቸው የተከተለውን ትንቢታዊ ንግግር ከማኅበሩ መድረክ ላይ አደርጉ፦

«በዚህ አጋጣሚ ለባልደረቦቼ የላቲን አሜሪካ አገሮች ተወካዮች፣ በተለይም ለአርጀንቲናው ልዑክ እጅግ በጣም ከባድ ፋይዳ ስላለው ጉዳይ የማስተላልፈው መልዕክት አለኝ። ዛሬ አገሬ ከግብጽ እና ከላይቤሪያ ጋር ሆና እናንተ ከጣልያን ጋር በማደም የአፍሪቃን ሕዝቦች ለመጨቆን የምትጫወቱትን ሚና በጥንቃቄ እየተመለከትን ነው። በቅርብ ጊዜ ውስጥ ግን እዚህ ያለነው ሦስት አፍሪቃውያን አገሮች በአስር እጥፍ በዝተን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ ተገቢ መቀመጫችንን እንይዛለን። ያን ጊዜ እኛ እንደናንተ ሳይሆን፣ ለዓለም ሰላም ድጋፍ እና ፍትሐዊ ፍርድ ድምጻችንን እንደምናሰማ ጥርጣሬ የለኝም።»

ሲሉ ስሜታዊ ንግግራቸውን አሰምተዋል። እውነትም ይሄንን በተናገሩ በአሥር ዐመታት ውስጥ አፍሪቃውያን አገሮች በማኅበሩ ውስጥ ትልቁ አኅጉራዊ ቡድን ለመሆን በቁ።

ረዥሙ የስደት ዘመን ተጠናቀቀ ለማስተካከል

 
አክሊሉ ሀብተወልድ አስመራ ሲገቡ

፲፱፻፲፯ ዓ/ም መጀመሪያ ለትምሕርት ከአገራቸው፣ ከትምሕርታቸውም በኋላ በጣልያን የግፍ ወረራ ምክንያት አምስቱን ዓመታት አውሮፓ ቆይተው በተቻላቸውና በተሰጣቸውም መመሪያ ስለአገራቸው ሲታገሉ የኖሩት አክሊሉ፤ ከጠላትም ድል መደረግ በኋላ የሳቸው ዲፕሎማሲያዊ የትግል ሥራ እስከሚገባደድ ድረስ በድካም፤ በጭንቀት እና በህመምም ለብዙ ዓመታት በፓሪስ እና ኒው ዮርክ የኖሩት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከጥቂት የሥራ ጋደኞቻቸው ጋር በ፲፱፻፵፬ ዓ/ም ወደናፈቋት አገራቸው ተመለሱ።

የኤርትራን ጉዳይ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስፈጽመው የተመለሱትን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአገራቸው ሕዝብ በተለይም ኤርትራውያን በጣም ሞቅ ባለ ሁኔታ ተቀበሏቸው። ቀደም ብሎ ንጉሠ ነገሥቱ፣ እቴጌ መነን ፀሐፊ ትዕዛዝ ወልደ ጊዮርጊስ ወልደ ዮሐንስ፣ አቶ ይልማ ደሬሳ እና የወለጋ ጠቅላይ ግዛት አስተዳዳሪ የነበሩት ደጃዝማች መኮንን ደስታ የደስታ ቴሌግራም ተልኮላቸው ነበር። ሆኖም ንጉሠ ነገሥቱ መስከረም ፩ ቀን ፲፱፻፵፭ ዓ/ም የኤርትራን ከኢትዮጵያ ጋር በኅብረት መንግሥት መዋሐድ አስመልክተው ባደረጉት ንግግር አንዳንድ ኤርትራውያንን በስም ጠርተው ሲያመሰግኑ፤ ለዚህ ውጤት እጅግ ከፍ ያለ ትግል ያካሄዱትንና ታላቅ ዲፕሎማሲያዊ መስዋዕትነትን ላበረከቱት አክሊሉ ሀብተወልድ ግን በሕዝብ ፊት ምስጋና ያለማቅረባቸው ያሳዝናል።

ሚያዝያ ወር ፲፱፻፵፯ ዓ/ም የአክሊሉ ዋና ደጋፊ የነበሩት እና እስከዚያ ጊዜ ድረስ በንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት ትልቅ ሥልጣን እና በንጉሠ ነገሥቱም ታማኝነትና ተሰሚነት የነበራቸው ፀሐፊ ትዕዛዝ ወልደ ጊዮርጊስ ወልደ ዮሐንስ ፣ ትክክለኛ ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ከዚህ ቁልፍ ቦታ ተነስተው መጀመሪያ የአሩሲ ጠቅላይ ግዛት አስተዳዳሪ ቀጥሎም የጋሙ ጎፋ ጠቅላይ ግዛት አስተዳዳድሪ ተደርጉ።

አምባሳዶር ዘውዴ ረታ በመጽሐፋቸው ስለዚህ ጉዳይ ሲያወሱ፣ የኤርትራ ጉዳይ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሚካሄድበት ጊዜ አክሊሉ ሀብተወልድ የብሪታንያን የኤርትራ አቋም ነቅፈው በመዝለፋቸው የንጉሠ ነገሥቱ የግል ፀሐፊ የነበሩት እና የብሪታንያ ደጋፊ የሚባሉት አቶ ተፈራ ወርቅ (በኋላ ፀሐፊ ትዕዛዝ) ‘የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ አክሊሉ ለብሪታንያ ይቅርታ ይጠይቅ ሲሉ ፀሐፊ ትዕዛዝ ወልደጊዮርጊስ ግን ያደረገው አግባብ ነው ይቅርታ መጠየቅ የለበትም በሚል ጉዳይ ተከራክረዋል ሲሉን የፀሐፊ ትዕዛዝ ወልደጊዮርጊስ ከሥልጣን መወገድ ምክንያት ዕውን ይሄ ይሆን ወይ? ሊያስብለን ይችላል።

ባህሩ ዘውዴ ደግሞ (A History of Modern Ethiopia 1855-1991) በተባለው መጽሐፉ ላይ የፀሐፊ ትዕዛዝ ወልደ ጊዮርጊስ ከሥልጣን መወገድ ዋና ምክኛት የነበሩት የግል ምስጢራዊ የስለላ ድር የዳበሩት እና በዚህም የሚያገኙትን መረጃዎች ለንጉሠ ነገሥቱ በማካፈል ይወደዱ የነበሩት የአክሊሉ ታላቅ ወንድም መኮንን ሀብተወልድ ናቸው ይለናል። እንዴት የፀሐፊ ትዕዛዝ ወልደ ጊዮርጊስ የመውደቅ ምክንያት እንደሆኑ ባያብራራልንም ምናልባት በዚሁ የምስጢራዊ ስለላ ድራቸው ‘ትልቅ ምስጢር አግኝተውባቸው ይሆን? ለማለት ያበቃናል።

ትክክለኛ ምክንያቱ ይህም ይሁን ያ፣ የፀሐፌ ትዕዛዝ ወልደጊዮርጊስ መወገድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩን አቶ አክሊሉን ግን ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር የሚያቀራርበውን በፀሀፊ ትዕዛዝ ማዕረግ የፅህፈት ሚኒስቴርና እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴርነትን አፍርቶላቸዋል።

የታኅሣሥ ግርግር ለማስተካከል

ክብር ዘበኛ ሠራዊት አዛዥ ጄነራል መንግሥቱ ንዋይ እና በታናሽ ወንድማቸው አቶ ገርማሜ ንዋይ የተጸነሰሰውና ታኅሣሥ ፬ ቀን ፲፱፻፶፫ ዓ/ም ተጀምሮ ዓርብ ታኅሣሥ ፯ ቀን አሥራ አምስት መኳንንት፣ ሚኒስቴሮች እና የጦር መኮንኖች መረሸን ያከተመው የታኅሣሥ ግርግር የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ፣ ለፀሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ በታላቅ ወንድማቸው አቶ መኮንን ሀብተወልድ መገደል ትልቅ የግል ሀዘን ላይ ቢጥላቸውም፤ በጊዜያዊ ጠቅላይ ሚኒስቴርነት የንጉሠ ነገሥቱን መንግሥት ይመሩ የነበሩት የራስ አበበ አረጋይ በአመጸኞቹ እጅ መገደል ለሳቸው የጠላይ ሚኒስቴርነቱን ማዕርግ እና ሥልጣን አስገኝቶላቸዋል። በጠቅላይ ሚኒስቴርነት እና በፅሕፈት ሚኒስቴርነት በጥምር ሲያገለግሉ ዘመናዊውንና ጥንታዊውን ሥልጣናት በጃቸው በማግባት ለንጉሠ ነገሥቱ ቀርበው በተሰሚነት አብዮቱ እስከፈነዳ ድረስ ሠሩ።

አብዮት ፍንዳታ ለማስተካከል

፲፱፻፷፭ ዓ/ም የተቀጣጠለው አብዮታዊ ሽብር በተማሪዎች ሰልፍ፣ የወታደሮች እንቅስቃሴ እንዲሁም የዓለምን ዱኛ (economy)[6] ያናጋው የነዳጅ ማዕቀብ ሲለኮሱ የደርግ ሥልጣንም እየጎለመሰ መጣ። ወታደሮቹም መኮንኖችን ብቻ ሳይሆን የ መንግሥት ባለሥልጣናትንም ጭምር የማሠር ስልጣን እንደሚኖራቸው ንጉሠ ነገሥቱን አሳመኑ። በየካቲት ወር ጠቅላይ ሚኒስቴሩ አክሊሉ ሀብተወልድ ከነ ሚኒስቴሮቻቸው ሥልጣናቸውን ለቀቁ። ‘ተንፏቃቂው አብዮት’ ወዲያው ተተክተው የተሾሙትንም አዲስ ጠቅላይ ሚኒስቴር ልጅእንዳልካቸው መኮንንም ከሥልጣን አውርዶ ከነ አክሊሉ ሀብተወልድ ጋር ከርቸሌ ከከተተ በኋላ መስከረም ፪ ቀን ፲፱፻፷፮ ዓ/ም ባለቤቱን እራሳቸውን ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ከሥልጣን አወረደ። ፀሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ ከንጉሠ ነገሥቱ አዝማድ እና ቤተሰቦች፤ መሳፍንት እና መኳንንት፤ ባለሥልጣናትና ወታደራዊ መኮንኖች ጋር በእስራት ከቆዩ በኋላ ያለክስም ያለፍርድ በኅዳር ወር ፲፱፻፷፯ ዓ/ም በተወለዱ በ ስድሳ ሦስት ዓመታቸው ከስልሳ ሰዎች ጋር ተረሽነው ሞቱ።

የአክሊሉ ሀብተወልድ ጥቅሶች ለማስተካከል

 
አክሊሉ ከንጉሠ ነገሥቱና ከአቶ ከተማ ይፍሩ ጋር
  • "… "የደረሰው ይድረስ ደካማ ሆኜ መታየት አልፈልግም :: የሀገሬን ጥቅምና መብት የሚነካ መስሎ ከታየኝ መናገሬን አልተውም ::"


  • "…ሀገሬ ኢትዮጵያ በዓለም ሸንጎ ላይ ፍርድ ተነፍጓት ስታዝን የመጀመሪያ ጊዜ አይደለም።…..ኢትዮጵያ ያለፉት ታሪኮቿ በትክክል እንዳስረዱት፤ለነፃነቷና ለመንቷ፤በኮሎኒያሊስቶች ጣሊአን ጋር በየጊዜዉ ስተዋጋ፤ያሸነፈችዉ ብቻዋን ነዉ። የተጠቃቺዉም ብቻዋን ስለሆነ፤አገሬ መቸዉንም ለሚደርስባት አደጋ ከማንም እርዳታ አገኛለሁ ብላ አትጠብቅም።ዛሬም ሆነ ነፃነቷን ለመጠበቅ፤ታሪኳን ለማስከበር አስፈላጊዉን ዝግጅት ማድረግ ያለባት፤እሷ ራሷ ብቻ ነች።…"


  • “በዚህ አጋጣሚ ለባልደረቦቼ የላቲን አሜሪካ አገሮች ተወካዮች፣ በተለይም ለአርጀንቲናው ልዑክ እጅግ በጣም ከባድ ፋይዳ ስላለው ጉዳይ የማስተላልፈው መልዕክት አለኝ። ዛሬ አገሬ ከግብጽ እና ከላይቤሪያ ጋር ሆና እናንተ ከጣልያን ጋር በማደም የአፍሪቃን ሕዝቦች ለመጨቆን የምትጫወቱትን ሚና በጥንቃቄ እየተመለከትን ነው። በቅርብ ጊዜ ውስጥ ግን እዚህ ያለነው ሦስት አፍሪቃውያን አገሮች በአስር እጥፍ በዝተን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ ተገቢ መቀመጫችንን እንይዛለን። ያን ጊዜ እኛ እንደናንተ ሳይሆን፣ ለዓለም ሰላም ድጋፍ እና ፍትሐዊ ፍርድ ድምጻችንን እንደምናሰማ ጥርጣሬ የለኝም።”

ማመዛገቢያ ለማስተካከል

  1. ^ ሽከታ ወሸከተ (አወራ) ከሚለው ቃል የተገኘ ነው። “ሰገላዊ አማርኛ”፤ በዲባቶ (doctor ) መስፍን አረጋ (፳፻ ዓ/ም)
  2. ^ ሲማክቶ መሠረት የሚለውን የግዕዝ ቃል ከአቶ ጋር በማጣመር የተገኘ ሲሆን ጉላፕ ደግሞ ጎለመ (ከፈለ፣ ለየ) ከሚለው የአማርኛ ቃል የተገኘ ነው - “ሰገላዊ አማርኛ”፤ በዲባቶ (doctor ) መስፍን አረጋ (፳፻ ዓ/ም)፣ ገጽ ፵፰
  3. ^ “ሰገላዊ አማርኛ”፤ በዲባቶ (doctor ) መስፍን አረጋ (፳፻ ዓ/ም)
  4. ^ “ሰገላዊ አማርኛ”፤ በዲባቶ (doctor ) መስፍን አረጋ (፳፻ ዓ/ም)
  5. ^ “የታሪክ ማስታወሻ ከእስር ቤት፤ ጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ”፤ ጦብያ ፪ኛ ዓመት ቁጥር ፮ መስከረም ፲፱፻፹፮ ዓ/ም
  6. ^ ዱኛ የሚለው ፊተኛ ቅጽል (ፊልጡፍ) የተገኘው አዱኛ (ሐብት) ከሚለው ቃል ነው ። “ሰገላዊ አማርኛ”፤ በዲባቶ (doctor ) መስፍን አረጋ (፳፻ ዓ/ም)

ዋቢ ምንጮች ለማስተካከል

  • ጦብያ መጽሔት ፪ኛ ዓመት ቁጥር ፮ መስከረም ፲፱፻፹፮ ዓ/ም
  • (እንግሊዝኛ) Professor Negussay Ayele, In Search of the Historical DNA of the Eritrean Problem - Review Article on The Eritrean Affair (1941-1963) by Ambassador Zewde Retta
  • (እንግሊዝኛ) Bahru Zewde, “A History of Modern Ethiopia 1855-1991), 2nd edition (2001)