ንግሥት ዘውዲቱ
==
ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ | |
---|---|
ንግሥተ ነገሥታት ዘኢትዮጵያ | |
ግዛት | ከ፲፱፻፱ እስከ ፲፱፻፳፪ ዓ.ም. |
በዓለ ንግሥ | የካቲት ፬ ቀን ፲፱፻፱ ዓ.ም. |
ቀዳሚ | ልጅ ኢያሱ |
ተከታይ | ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ |
ባለቤት | አርአያ ሥላሴ ራስ ጉግሳ ወሌ |
ሥርወ-መንግሥት | ሰሎሞን |
አባት | ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ |
እናት | ወይዘሮ አብቺው |
የተወለዱት | ሚያዚያ ፳፪ ቀን ፲፰፻፷፰ ዓ.ም. |
የሞቱት | መጋቢት ፳፬ ቀን ፲፱፻፳፪ ዓ.ም. |
የተቀበሩት | ታዕካ ነገሥት በዓታ ቤተ ክርስቲያን |
ሀይማኖት | የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ክርስትና |
==
ግርማዊት ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ቅዳሜ ሚያዝያ ፳፪ ቀን ፲፰፻፷፰ ዓ.ም ከሸዋ ንጉሥ ምኒልክና ከወረኢሉ ተወላጅ ከወይዘሮ አብቺው በተጉለትና ቡልጋ አውራጃ በሞረትና ጅሩ ወረዳ እነዋሪ ከተማ አጠገብ በምትገኝ ሰገነት በምትባል መንደር ተወለዱ። ሐምሌ ፲፩ ቀን ሰኞ ሥርዓተ ጥምቀት ተፈጽሞላቸው፣ የክርስትና ስማቸው አስካለ ማርያም ተባለ። ግርማዊት ንግሥተ ነገሥት ዘውዲቱ ለዳግማዊ ምኒልክ ሦስተኛ ልጅ ሲሆኑ ከልጅ ኢያሱ ቀጥለው መኳንንትና ሕዝቡ መክሮና ዘክሮ በምርጫ በኢትዮጵያ ዙፋን ላይ የተቀመጡ ብቸኛዋ ንግሥት ናቸው።
አባታቸው የሸዋው ንጉሥ ምኒልክ (በኋላ ዳግማዊ ዐፄ) ዘውዲቱ የስድስት ዓመት ሕጻን እንደነበሩ ለአሥራ ሁለት ዓመቱ የዐፄ ዮሐንስ ልጅ ለአርአያ ሥላሴ ዳሩዋቸው። ጋብቻቸውም ጥቅምት ፲፫ ቀን ፲፰፻፸፭ ዓ.ም. በተክሊልና በቁርባን ተፈጸመ፡ የሠርጉም ማማርና የሽልማቱ ብዛት ሊነገር አይቻልም። ልጅ ኢያሱ መስከረም ፲፯ ቀን ፲፱፻፱ ዓ.ም ከስልጣን ሲወርዱ፤ መኳንንቱና ሕዝቡ መክሮና ዘክሮ በምርጫ ወይዘሮ ዘውዲቱን ግርማዊት ንግሥተ ነገሥት፤ ራስ ተፈሪ መኮንንን አልጋ ወራሽ እና ባለሙሉ ሥልጣን እንደራሴ እንዲሆኑ ወስነው መስከረም ፳፩ ቀን "ግርማዊት ዘውዲቱ፣ ንግሥተ ነገሥት ዘኢትዮጵያ" ተብለው ነገሡ። በመኳንንቱም ምክር መሠረት ጳጳሱና እጨጌ ወልደጊዮርጊስ "ኢያሱን የተከተልክ፣ ያነገሥናትን ዘውዲቱንና ራስ ተፈሪን የከዳህ፣ ውግዝ ከመአርዮስ" እያሉ በአዋጅ አወገዙ፡[1]
ከዚህ በኋላ በጥቅምት የሰገሌ ጦርነት ከተደረገ በኋላ የዘውድ በዓሉ የካቲት ፬ ቀን ፲፱፻፱ ዓ.ም እንዲሆን ታዞ፣ ለዘውዱ በዓል በኢትዮጵያ አዋሳኝ ያሉት የእንግሊዝ ሱዳንና የእንግሊዝ ሱማሌ ገዥዎች፤ የፈረንሳይ ሱማሌ ገዥ እና በኢትዮጵያም ታላላቅ ራሶች እንዲሁም የየአውራጃው ገዥዎች በተገኙበት በዕለተ እሑድ አባታቸው ባሠሩት በትልቁ ደብር በመናገሻ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በሊቀ ጳጳሱ በአቡነ ማቴዎስ እጅ ቅብዐ መንግስት ተቀብተው የንጉሠ ነገሥቱን ዘውድ ጫኑ። ከዚህም በኋላ እንደ ሥርዓተ ንግሡ ሕግ፤ ንግሥተ ነገሥት ዘውዲቱ በአባታቸው ዙፋን ተቀምጠው መንገሣቸውን፤ ደጃዝማች ተፈሪም ራስ ተብለው አልጋ ወራሽና ባለሙሉ ሥልጣን እንደራሴ መሆናቸውን በቤተ ክርስቲያኑ ቅጥር ግቢ በተሰበሰበው ሕዝብ ፊት አዋጅ ተነገረ።
የንግሥተ ነገሥታትን ሥልጣን ለማሳወቅ ሲባል ራስ ወልደ ጊዮርጊስ የካቲት ፲፩ ቀን ራስ ወልደ ጊዮርጊስን ንጉሠ ጎንደር ብለው አንግሠው ዘውድ ደፉላቸው። እንደዚሁም መስከረም ፳፯ ቀን 1921 ዓ.ም. ብዙ መኳንንትና መሣፍንት፤ ሊቃውንትና ጳጳሳት ባሉበት የኢትዮጵያ መንግሥት አልጋ ወራሽ ራስ ተፈሪ መኮንንን አዲስ አበባ መካነ ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን፣ ንጉሥ ተፈሪ ተብለው ዘውድ ተጫነላቸው።
ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ በነገሡ በአሥራ ሦሥት ዓመት ተኩል በ፶፬ ዓመት ዕድሜያቸው ረቡዕ መጋቢት ፳፬ ቀን ፲፱፻፳፪ ዓ.ም በ ፰ ሰዓት ዐረፉ። የሞታቸው ዜና እንደተሰማም በከተማው የሐዘን ጥላ አጠላበት። አባታቸው ዐፄ ምኒልክ በተቀበሩበት በታዕካ ነገሥት በዓታ ቤተ ክርስቲያን ተቀበሩ።
በግርማዊት ንግሥተ ነገሥት ዘውዲቱ ዘመን ከተፈጸሙ ተግባራት
ለማስተካከልየዓለም ማኅበር አባልነት
ለማስተካከልየዓለም መንግሥታት ማኅበር (ሊግ ኦፍ ኔሽንስ) ጠቅላላው ጉባዔ በ28 ሴፕቴምበር በ1923 እ.ኤ.አ. (መስከረም 17 1916 ዓ.ም.) ስብሰባውን ቀጠሉና የስድስተኛውን ኮሚሲዮን ማስታወቂያ ተደግፎ ኢትዮጵያ ማኅበርተኛ እንድትሆን ፈቃዱ መሆኑን አስታወቀ። በዚህ ጊዜ ዋናው መልእክተኛ ደጃዝማች ናደው የደስታ ስሜታቸውን ለመግለጥ ንግግር ማድረጊያው ስፍራ ላይ ቆመው የሚከተለውን ዲስኩር ተናገሩ፡፡
ክቡራን ሆይ፤
ጠቅላላው ጉባኤ በበጎ ፈቃደኝነትና በትክክለኛ ፈራጅነት፣ በጥልቅ አስተሳሰብ መርምሮ ወደ ማኅበሩ ስለመግባት ያቀረብነውን ጥያቄ ስለ ተቀበለው፣ የኢትዮጵያ መልእክተኞች በግርማዊት ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱና በልዑል ራስ ተፈሪ መኰንን የኢትዮጵያ መንግሥት አልጋ ወራሽና ባለ ሙሉ ሥልጣን እንደራሴ ስም፣ እንዲሁም በመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ስም ምስጋና ያቀርባሉ።
የሰውን ልጅ ወንድማማችነት የመመሥረት ዓላማ ባለው ውሳኔያችሁ የተሰማንንም ልባዊ ደስታ እንድገልጽላችሁ ይፈቀድልኝ ዘንድ እለምናለሁ። ኢትዮጵያ ባለፈው የጀግንነት ታሪክና በከፍተኛ ሥልጣኔዋ የምትኮራ አገር መሆንዋ፣ የዘመናዊ ድርጅቶች ከሚያስገኙላትም ፍሬ ተካፋይ ለመሆን ብርቱ ጥረትና ሙሉ ፈቃደኛነት እንዳላት የታወቀ ነው።
መንግሥታችንም ይህን ጥረት ወደ መልካም ግብ ለማድረስ የዓለም መንግሥታትን አንድነትና ኅብረት የሚያስፈልግ መሆኑን በጥብቅ ያምንበታል።
ስለ ባሮች የነፃነት ደንብ
ለማስተካከልልዑል አልጋ ወራሽ ራስ ተፈሪ መጋቢት ፲፮ ቀን ፲፱፻፲፮ ዓ.ም በግርማዊት ንግሥት ዘውዲቱ ፈቃድ ስለ ባሮች ነፃነት አንድ ደንብ አወጡ። ደንቡ «ስለ ባሮች አስተዳደርና ነፃነት የቆመ ደንብ» የሚል አርእስት ተሰጥቶትና እንደ መጽሐፍ ሆኖ በልዑል አልጋ ወራሽ ማተሚያ ቤት ታትሞ ወጣ። መጽሐፉ ባለ 10 ገጽ ሲሆን የደንቡ ቃል በ45 ቁጥሮች ተመድቧል፡፡
ይህ መጽሐፍ ለሕዝብ ይሸጥ ነበርና መጽሐፉን ገዝቶ ያነበበው አብዛኛው ሰው «የሥልጣኔ እርምጃ ነው» እያለ አልጋ ወራሽን አመሰገነ።
ባለብዙ ባሮች የሆኑት ሰዎች ግን በልባቸው ቅሬታ ገብቶ አዘኑ። ለምሳሌ የጦር ሚኒስትሩ ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ በዚያው ሰሞን የልባቸውን ቅርታ በጨዋታ ላይ ሲናገሩ «እንግዲህ ምን አለ አልታየ ወርቅ (ሚስታቸው) ወደ ወንዝ እየወረደች ውሀ መቅዳት ነው፣ እኔም እንጨት እየፈለጥሁ አቀርብላታለሁ» አሉ እየተባለ ሲወራላቸው ከረመ፡፡
የአፄ ቴዎድሮስ ዘውድ ስለ መመለሱ
ለማስተካከልከእንግሊዝ አገር የመጣው የአፄ ቴዎድሮስ ዘውድ ሐምሌ 4 ቀን 1917 ዓ.ም ቅዳሜ ለግርማዊት ንግሥት ዘውዲቱ ተመለሰ። በዚህም ጊዜ የተፈጸመው ሥነ ሥርዓት እንደሚከተለው ነበር፤
ከጧቱ በ4 ሰዓት የግቢ ሚኒስትር ደጃዝማች ወልደ ገብርኤል በሻህ በጦር ልብስ ያጌጡ ጭፍሮች አስከትለውና በአራት ፈረሶች የሚሳብ ሠረገላ አሲዘው ከአቶ ሣህሌ ፀዳሉ ጋር ወደ እንግሊዝ ሌጋሲዮን ሄዱ። የእንግሊዝ መንግሥት ሚኒስትር ሚስተር ቻርልስ ቤንቲንክም ዘውዱን በሠረገላው ላይ አስቀመጡትና ሁሉም ዘውዱን አጅበው ወደ ቤተ መንግሥት መጡ።
ግርማዊት ንግሥት ዘውዲቱና ልዑል አልጋ ወራሽ በቤተ መንግሥታቸው ውስጥ በተለይ በተሰናዳው ስፍራ ከመኳንንት ጋር ተቀምጠው ይጠብቁ ነበር። የግቢ ዘበኞችም በግቢው ውስጥ በቀኝና በግራ ተሰልፈው ነበርና ሠረገላው በሰልፉ መካከል አልፎ ከመንግሥት ፊት ደረሰ። እዚያም አንድ ጠረጴዛ ተዘጋጅቶ ነበርና ሚስተር ቤንቲንክ ዘውዱን ከሠረገላው አውርደው በጠረጴዛው ላይ አስቀመጡትና ከዚህ ቀጥሎ ያለውን ቃል ተናገሩ፤
ግርማዊት ሆይ በንግሥት ቪክቶሪያ መንግሥት በ1860 ዓ.ም ከመቅደላ የተወሰደውን የአፄ ቴዎድሮስን ዘውድ የታላቂቱ ብሪታንያና የአየርላንድ፣ ከባሕር ማዶ ያሉት ግዛቶች ንጉሥና የህንድ ንጉሠ ነገሥት በሆኑት በግርማዊ ጌታዬ በንጉሡ ትዕዛዝ ለግርማዊት ንግሥት በማክበር እመለስሁ።
(መርስዔ ኀዘን ወ/ቂርቆስ፣ የሐያኛ ክፍለ ዘመን መባቻ፣ 2000)
ዋቢ መጻሕፍት እና ማስታወሻ
ለማስተካከል- ሕይወቴና የኢትዮጵያ እርምጃ -ቀ.ኃ.ሥ 1929 ዓ.ም - ገጽ 37-38
- አጤ ምኒልክ - ከጳውሎስ ኞኞ1984 ዓ.ም -ገጽ 77
- የኢትዮጵያ ታሪክ ከንግሥተ ሳባ እስከ ታላቁ የአድዋ ድል በ ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ 1999 ዓ.ም. ገጽ 136
- http://www.ethiopianreporter.com/content/view/1161/54/ Wednesday, 02 April 2008