ልጅ እያሱ እና ደጃች ተፈሪ መኮንን


ልጅ ኢያሱ ሚካኤል ከበርካታ ሙስሊም ባላባቶች ጋር የተነሳቸው ፎቶግራፎች አሉ፡፡ ለምሳሌ ሀረር ውስጥ ገራድ አብዱላሂ አሊ ሳዲቅ ከሚባል የሀረር ገዥ ቤተሰብ ጋር የተነሳው ፎቶግራፍ በብዙ ስፍራዎች ተለጥፎ አይቼዋለሁ፡፡ አንዳንድ ምንጮች ያ ፎቶግራፍ ልጅ እያሱን ለመወንጀል “montage” በሚባለው የፈጠራ ጥበብ የተሰራ ነው የሚል ታሪክ ያስነብባሉ። ለምሳሌ “የሃያኛው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያ” የተሰኘው መጽሐፍ ደራሲ “ፎቶውን የሰራው ዝነኛው እንግሊዛዊ ወታደር ቶማስ ለውሬንስ (በዓለም ታሪክ መጻሕፍት Lawerence of Arabia በሚል ቅጽል ስም የሚታወቅ) ነው” በማለት ጽፈዋል።

ሆኖም የልጅ እያሱ የልጅ ልጅ የሆኑት ፕሮፌሰር ግርማ ዮሐንስ እያሱ እንደዚህ ዓይነት ፎቶዎች እርግጠኛ ሊሆኑ እንደሚችሉ ከአስር ዓመታት በፊት “ጎህ” ለተሰኘ መጽሔት በሰጡት ቃለ-ምልልስ ገልጸዋል። ፕሮፌሰር ግርማ ስለዚህ ጉዳይ ሲናገሩ እንዲህ ነበር ያሉት።

“ከሼኮችና ከሌሎችም ጋር የተነሱአቸው ፎቶግራፎች ብዙዎች አሉ። ስለዚህ ከቄስ ጋር መነሳትም የተለመደ ነበርና ልጅ እያሱ ሁለቱንም እኩል አድርጎ ለማየት የነበራቸው ፖሊሲ አካል ነው”። (ጎህ መጽሔት፣ ቅጽ 1፣ ቁጥር 5፣ ጥቅምት 1993፣ ገጽ 13)

በቅርብ ጊዜ ስለልጅ እያሱና የአፋሮች ግንኙነት የጻፉት አራሚስ ሁመድ ሱሌ (Aramis Houmed Soulé) የተባሉ ምሁር ልጅ እያሱ ከአፋር ባላባቶችም ጋር እኝህን መሰል ፎቶግራፎች መነሳቱን አረጋግጠዋል። ስለዚህ ፎቶው “ፎርጅድ” አልነበረም ማለት ነው። ሁለቱ ምሁራን (ፕሮፌሰር ግርማ እና አራሚስ ሁመድ ሱሌ) በትክክል እንደገለጹት ልጅ እያሱ ፎቶግራፉን የተነሳበት ዓላማ ሙስሊም ኢትዮጵያዊያን ከክርስቲያን ወገኖቻቸው ጋር እኩል መሆናቸውን ለማሳየት በሚል ነው። ታዲያ ልጅ እያሱ በመናፍቅነት በተከሰሰበት ወቅት እንዲህ ዓይነት ፎቶዎች እየተለቀሙ እንደማስረጃ ቀርበውበት ነበር።

ይህ የልጅ እያሱ መስለም በዘመኑ ብዙ የተባለለት ቢሆንም እስከ አሁን ድረስ ከአፍ ታሪክ የበለጠ ማስረጃ ሊቀርብለት አልቻለም። የእርሱ የስልጣን ባለጋራ የሆኑት ራስ ተፈሪ መኮንን (አጼ ኃይለ ሥላሴ) በጻፉት “ህይወቴና የኢትዮጵያ እርምጃ” የተሰኘው ግለ-ታሪካቸው ውስጥ የእያሱ ወንጀሎች በማለት ከዘረዘሯቸው አስራ አንድ ነጥቦች መካከል አስሩ አቀራረባቸው ቢለያይም ይዘታቸው አንድ ነው። ይኸውም የልጅ እያሱ መስለም ነው። እነዚህ ነጥቦች የልጅ እያሱን አራት ሴቶች ማግባት፣ መስጊድ ገብቶ መስገድና ቁርአን ማንበብ፣ መስጊድ ማሰራት፣ በኢትዮጵያ ባንዲራ ላይ “ላኢላሃ ኢለላህ” የሚል ጽሁፍ ማስጠለፍ ወዘተ… የመሳሰሉት ናቸው።

ይሁንና የልጅ እያሱ የልጅ ልጅ የሆኑት ፕሮፌሰር ግርማ ዮሐንስ “እነዚህ ሁሉ የፈጠራ ክሶች ናቸው” ነው የሚሉት። በተለይ ከተፈሪ መኮንን ጋር ከተዋጉ በኋላ ተሸንፈው በሸሹበት የአፋር በረሃ ያስጠለሏቸው የዘመኑ የአፋር ሱልጣን አቡበከር የወንድም ልጅ የሆኑት ሀንፍሬ አሊሚራህ ስለልጅ እያሱ ፍጹም ክርስቲያን መሆን ምስክርነታቸውን እንደሰጡአቸው ይገልጻሉ። አራሚስ ሁመድ ሱሌ የተባሉት ምሁርም የፕሮፌሰር ግርማን አባባል የሚያጠናክር ምስክርነት ሰጥተዋል። እኝህ ምሁር እንደጻፉት ክርስቲያኑ ልጅ እያሱ በአፋር ምድር ሳለ በክርስትና እምነቱ ከመጽናቱም በላይ አገልጋዮቹ የሰሩለትን የማሽላ ጠላ ይጠጣ ነበር። ስለዚህ ልጅ እያሱ ሙስሊሙን ከክርስቲያኑ ጋር እኩል ለማድረግ ጥረት ከማድረጉ ውጪ ለራሱ ክርስቲያን ሆኖ ነው የኖረው ማለት ነው።

ሆነም ቀረ ግን የእያሱ መስለም እርሱን ከስልጣን ለማውረድ የተደረገው ትግል ማጠንጠኛ ሆኖ ነው ያረፈው። ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ክሱ በዚህ ስልት የተቀናበረው እያሱን በህዝቡና በጦር ሀይሉ ዘንድ ለማስጠላት አመቺ መሳሪያ ሆኖ በመገኘቱ ነው ይላሉ። እንደ ፕሮፌሰሩ ገለጻ ልጅ እያሱ ቀጨኔ መድኃኒዓለምን የመሳሰሉ ደብሮችን እንዳልተከለ ሁሉ ከፍ ብሎ የሚወራው መስጊዶችን ማሰራቱ ነው። ለክሱ ማስረጃ አምጡ በሚባልበት ጊዜ “ድሮውንስ ከሙሐመድ ዓሊ ልጅ ምን ይጠበቅ ኖሯል?!” የሚል ቃለ አጋኖ ይደሰኮር ነበር። “ይሁንና” ይላሉ ፕሮፌሰር ባህሩ “ለሸዋ መኳንንት የእያሱ አደገኛነት የፖለቲካ የበላይነታቸውን ከመፈታተኑ ላይ ነበር። ስለዚህ የመናፍቅነቱ ክስ የመነጨው ለሃይማኖት ከመጨነቅ ሳይሆን ለተፈጠረው የፖለቲካ ስጋት ርዕዮተ ዓለማዊ ሽፋን ሆኖ ለማገልገል ካለው አመቺነት ነው።” (ባህሩ ዘውዴ፣ የኢትዮጵያ ታሪክ ከ1847-1983፡ ገጽ 134-135)

በልጅ እያሱ ላይ የሚደረገው ዱለታ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰው ልጅ እያሱ አባቱን “ንጉሥ ሚካኤል” በማለት በወሎና በትግሬ ላይ ባነገሠበት ጊዜ ነው። የሸዋ መኳንንት ራስ ሚካኤል ሰሜን ኢትዮጵያን በቀጥታ ሌላኛውን የኢትዮጵያ ክልል በልጁ በኩል መቆጣጠሩን አሰመሩበት። በመሆኑም የሸዋ መኳንንት “ይህ ወጣት ከቤተ መንግሥቱ ጠራርጎ ሳያስወጣን እንቅደመው” በማለት መሯሯጥ ጀመሩ። የዚህ አድማ ዋነኛ መሪና አቀናባሪ የጦር ሚኒስትሩ ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ ስለመሆኑ ምሁራን የሚስማሙበት ሐቅ ነው።

          • ***** *****

ከዚህ በፊት እንዳጫወትኳችሁ ልጅ እያሱ የዕድሜ ልክ ባላንጣው ሊሆን የበቃውን ደጃች ተፈሪ መኮንንን በጋብቻ ጠልፎ ዝም ሊያሰኘው ሞክሮ ነበር። ይሁንና ተፈሪ የእያሱ እህት ልጅ የሆነችውን ወ/ሮ መነን አስፋውን ቢያገባም ሁለቱ ወጣቶች ፍጹም ሊጣጣሙ አልቻሉም። ተፈሪ የዘመኑ ሀብታም ክፍለ ሀገር የነበረው ሀረርጌ የዕድሜ ልክ ግዛቴ ነው ብሎ ያስብ ነበር። እያሱ ደግሞ ተፈሪ በሀረር ሀብት መበልጸጉን አልወደደውም። በተለይም ደጃች ተፈሪ ከባቡር መስመር መዘርጋት ጋር በአጭር ጊዜ ውስጥ የሀገሪቱ መንግሥት ግምጃ ቤት አለኝታ ሊሆን የበቃውን የድሬዳዋ ጉምሩክ ገቢ በቀጥታ ሊቆጣጠረው መቻሉ ለልጅ እያሱ አልተዋጠለትም።

ነገር ግን ከዚህ ክስተት በላይ እያሱን በተፈሪ ላይ ያነሳሳው የልጅ እያሱን ስም የሚያጠፋ ሚስጢራዊ ደብዳቤ ለእንግሊዝ መንግሥት ተጽፎ መገኘቱ ነው። ይህንን ደብዳቤ የጻፉት የደጃች ተፈሪ መኮንን ጸሓፊና አንድ ማንነቱ በውል ያልተገለጸ ሌላ ሰው ናቸው። ደብዳቤው በማን ትዕዛዝ እንደተጻፈ ግን የታሪክ ሰነዶች በይፋ የሚገልጹት ነገር የለም። ልጅ እያሱ “ትዕዛዙን ያስተላለፈው ተፈሪ መኮንን ነው” ባይ ነው። በዚህም ወደ አዲስ አበባ አስጠርቶት ስለጉዳዩ ቢጠይቀው ደጃች ተፈሪ ከነገሩ ንጹህ መሆኑን በመሀላ ገለጸለት። ቢሆንም እያሱ አላመነውም። በመሆኑም በሁለቱ መካከል የነበረው ቅራኔ በጣም ተባባሰ።

ነገሮች በዚህ ላይ እንዳሉ ልጅ እያሱ ተፈሪ መኮንንን ወደ አዲስ አበባ አስጠርቶት እርሱን ሳያነጋግር ወደ ሀረር ወረደ። ከሀገሬው ህዝብ ጋር ከተማከረ በኋላም ደጃች ተፈሪ መኮንንን ከሀረር ገዥነቱ ሻረው። በምትኩም የከፋ ገዥ አድርጎ ሾመውና በአስቸኳይ ወደ ተሾመበት ክልል እንዲሄድ ጥብቅ ትዕዛዝ ሰጠው። የድሬ ዳዋ ጉምሩክንም ወዳጁ በነበረው ሶሪያዊው ሀሲብ ይዲልቢ ስር እንዲሆን አደረገው።

የልጅ እያሱ እርምጃ ተፈሪን በጣም አስደነገጠው። “ይህ መስፍን ሊውጠኝ እያመቻቸኝ ነው” በማለት እንዲያስብም አደረገው። ስለዚህ ደጃች ተፈሪ ወደ ከፋ መሄዱን ተወና አዲስ አበባ ሆኖ የሚበጀውን መንገድ ማፈላለግ ጀመረ። ልጅ እያሱ በትዕዛዝ ላይ ትዕዛዝ ቢያዥጎደጉድለትም ደጃች ተፈሪ ልዩ ልዩ ሰበቦችን እያመካኘ በዋና ከተማይቱ ሰነበተ። የእያሱንም ልብ ለማቀዝቀዝ የስጋ ዘመዱ የሆነውን ቀኛዝማች እምሩ ኃይለ ሥላሴን (የኋለኛው ራስ እምሩ) የቃልና የጽሑፍ መልዕክት አስጨብጦ ልጅ እያሱ ወደሚገኝበት ድሬዳዋ ላከው። እያሱም የተፈሪን መልዕክት ከሰማ በኋላ እንዲህ አለ።

“ደጃች ተፈሪ አሳቡ ሁሉ ሌላ ነው። ያንዳንድ ወስላቶች ነገር እየሰማ ወዲያ ወዲህ ቢል ብርቱ ነገር ያገኘዋል። የአዲስ አበባ ወስላታ ሁሉ ፍሬ ያለው መስሎታል።” (ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ፣ “ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ”፣ በኢትኦጵ መጽሔት የቀረበ ጽሁፍ፣ ጥቅምት 1993፣ ገጽ 37) ይህ የልጅ እያሱ አነጋገር በሁለቱ ልዑላን መካከል የነበረው ውጥረት ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱን ያመላክታል። የእያሱ ንግግር ለደጃች ተፈሪ ጆሮ ከደረሰው በኋላ ተፈሪ በስውር ማድባቱን ትቶ እያሱን ከስልጣን ለመፈንገል የሚዶልቱትን መኳንንት በይፋ ተቀላቀለ። በአስገራሚ ፍጥነትም የዱለታውን መሪነት ከፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ እጅ ወሰደው።

          • ***** *****

የሁለቱ ወጣቶች መገፋፋት ይፋ ሆኗል። ቀጣዩ ነገር “ማን ቀድሞ አጥቅቶ የአሸናፊነቱን ዘውድ ይቀዳጃል” የሚለው ብቻ ነበር። የሸዋና የምዕራብ ኢትዮጵያ ባላባቶች በተፈሪ ዙሪያ ተሰልፈዋል። የወሎ፣ የአፋር፣ የኦጋዴንና የሀረርጌ ባላባቶች የእያሱን ጎራ ተቀላቅለዋል። ቢሆንም ሁለቱ ጎራዎች በራሳቸው ወኔ ፍልሚያውን መጀመር አልቻሉም። የመጨረሻውን ፍልሚያ ለማስጀመር ሌላ ስውር እጅ አስፈልጓል። የዘመኑ ታላላቅ ቅኝ ገዥዎች እጅ!

እንግሊዝ፣ ኢጣሊያና ፈረንሳይ ሁለቱ ልዑላን ሲጣሉ መጀመሪያ ላይ አይተው እንዳላዩ ሆነው ስራቸውን ማከናወኑን ነበር የመረጡት። ከቆይታ በኋላ ግን የልጅ እያሱ የእኩልነት ፖሊሲ (በሁሉም ኢትዮጵያዊያን መካከል እኩልነትን ለማስፈን በሚል የሚወስዳቸው እርምጃዎች) የነርሱን ጥቅም የሚጎዳ መሆኑን ተገነዘቡ። የጠረፍ አካባቢ ገዥዎች ከቅኝ ገዥዎች ጋር ለሚያደርጉት ውጊያ የሞራል ድጋፍ የሚሰጥ መሆኑ አስቀየማቸው። በተለይ እንግሊዝ ሶማሌላንድን ከብሪታኒያ አገዛዝ ነጻ ለማውጣት ለ30 ዓመታት ሲዋጋ ለኖረው ሰይድ አብዱሌ ሐሰን የተሰኘ የኦጋዴን ሶማሊዎች ብሔራዊ ጀግና የመሳሪያ ድጋፍ በገፍ ማቅረቡ ቅኝ ገዥዎቹን በጣም አስበረገጋቸው። “ይህ ወጣት ዝም ተብሎ ከተተወ ከዚህ አካባቢ ሊያስነቅለን ነው” እንዲሉም አደረጋቸው። አልፎ ተርፎም ልጅ እያሱ በዘመኑ ከነዚህ ቅኝ ገዥዎች ጋር በአንደኛው የዓለም ጦርነት የሚዋጉትን ጀርመንና ቱርክን የመደገፍ አዝማሚያ ማሳየቱ ሶስቱ ሀያላን እርሱን ከስልጣን ለመንቀል በሚደረገው ትግል በቀጥታ እንዲሳተፉ አነቃነቃቸው።

በመሆኑም ሀያላኑ ጳጉሜ 1908 የእያሱን የጠላትነት እርምጃ በማስመልከት በጻፉት የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ አድማውን መቀላቀላቸው ይፋ ሆነ። ከመጋረጃ ጀርባ ኩዴታ ጠንስሰው ወደ ተግባር መለወጥ ላቃታቸው የሸዋ መኳንንት ኩዴታው ወደ ተግባር የሚለወጥበትንም ስልት አስጨበጧቸው። በተለይ በእያሱ ላይ የቀረበው የመናፍቅነት ክስ ትክክል መሆኑን ለማስረገጥ የእያሱን መስለም የሚያሳዩ ፎቶግራፎችን እያባዙ በአዲስ አበባና በሌሎችም ከተሞች አሰራጩ።

          • ***** *****

ይህ ውጥረት በተፈጠረበት ወቅት ልጅ እያሱ ኦጋዴን ነበር። ከበረሃ ወደ አዲስ አበባ ተመልሶ በቤቱ ላይ የተለኮሰውን እሳት እንዲያጠፋ ወዳጆቹ መልዕክት ቢሰዱለት “የሸዋን መኳንንት በአፉ ላይ ብሸናበት የሚናገረኝ የለም” የሚል የንቀት መልስ መለሰላቸው። በዚህም የስልጣን ፍጻሜውን አቃረበው። ታዲያ እያሱ የጠላቶቹን አሰላለፍ በደንብ የተገነዘበው አይመስልም። በርሱ ሐሳብ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ለማመጣጠን የሚወስዳቸውን እርምጃዎች የሚቃወሙት የሸዋ መኳንንት ብቻ ነበሩ።

ነገሩ ግን እንዲያ አልነበረም። ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ እንደሚሉት ልጅ እያሱ ፖሊሲውን በግልጽ ባለማብራራቱ ተራው ህዝብ እንኳ ሀገሩን ለማስለም ሌት ተቀን የሚደክም አድርጎ ነው የወሰደው። በዚህ ላይ እነ ደጃች ተፈሪ በቆንስሎቹ ድጋፍ እያሱ የሚገለበጥበትን የሀሰት ክስ ቀምመው ሲያቀርቡለት ህዝቡም እንደ መኳንንቱ “ድሮስ ከሙሐመድ ዓሊ ልጅ” አለና አረፈው። በመሆኑም ሰፊው ህዝበ ክርስቲያን ለዱለታው ድጋፉን ሰጥቷል። የእያሱ እጣ አሳዛኝ የሚሆነው ድሮ የሚገብሩለት ሁሉ በዚህ ቀውጢ ጊዜ ሲከዱት ነው። በተለይ በስልጣን ዘመኑ መጀመሪያ ላይ በወሰዳቸው ተራማጅ እርምጃዎች ተደስተው በርሱ ዙሪያ የተሰለፉት ለውጥ ናፋቂ ምሁራን በዚህ የፈተና ወቅት የገቡበት ሳይታወቅ ከጎኑ ጠፍተዋል። አንዳንዶቹ ጭራሽ ከርሱ ጎራ ተነጥለው እርሱን ወደ መንቀፍ ገብተዋል። ለዚህም ምሳሌ የሚሆነው የነጋድራስ አፈወርቅ ገብረኢየሱስ ነገር ነው። ነጋድራስ አፈወርቅ ልጅ እያሱን በስልጣን ዘመኑ መጀመሪያ ላይ የኢትዮጵያ ተስፋና የለውጥ ሀዋሪያ አድርገው እንዳላንቆለጳጰሱት ሁሉ በዚህ የመከራ ወቅት እንዲህ የሚል ስንኝ መቋጠራቸውን ታሪክ አዋቂዎች በትውስታቸው መዝግበዋል። ሙሐመድ እያሱ ለገመ በራሱ እያሱ ሙሐመድ አልጋ ሲሉት አመድ። (ብርሃኑ ድንቄ፣ ቄሳርና አብዮት፣ 1986፣ ገጽ 30)

እንግዲህ የልጅ እያሱ ውድቀት እውን ሆነ። ለሶስት ዓመታት የነገሠበትን አልጋ ከውጪና ከውስጥ በተሸረበበት ሴራ አጣ። መስከረም 17/1909 ዓ.ል. ዘውዲቱ ምኒልክ ንግሥተ ነገሥታት ተብላ ዙፋኑ ላይ ስትቀመጥ ደጃች ተፈሪ መኮንን “ራስ” ተብሎ የኢትዮጵያ መንግሥት አልጋ ወራሽና ባለሙሉ ስልጣን እንደራሴ ሆነ። ይህ ሁሉ ሲከናወን ኢላማ የሌለው ተኩስ አልፎ አልፎ ከመሰማቱ በስተቀር አዲስ አበባ ሰላም ነበረች (አንዳንዶች 17 ሰዎች ሞተዋል በማለት ጽፈዋል)።

          • ***** *****

የልጅ እያሱ ከስልጣን መውረድ ዜና የተሰማው እያሱ ጅጅጋ እያለ ነው። የዜናውን መሰማት ተከትሎ የእያሱ ደጋፊዎች በሚበዙባቸው ሀረርና ድሬ ዳዋ ታላቅ ረብሻ ተነሳ። የደጃች ተፈሪ መኮንን ደጋፊዎች የተባሉት እየተሳደዱ ተፈጁ። እያሱ በከተሞቹ ደርሶ ሁኔታውን ካረጋጋ በኋላ በአሻጥር የተወሰደበትን ዙፋን ለማስመለስ ከከተሞቹ ነዋሪዎች ጋር ተማከረ። በዚህም የህዝቡን ድጋፍ ካገኝ በኋላ በሸዋ ላይ ለመዝመት መዘጋጀት ጀመረ። ይሁንና ዝግጅቱን ሳያጠናቅቅ እነ ራስ ተፈሪ የላኩት 15,000 ጦር ወደ ሀረርጌ እየመጣ መሆኑ ታወቀ። ልጅ እያሱም የሸዋውን ጦር ለመግጠም ወደ ምዕራብ አቅጣጫ ገሠገሠ። ሁለቱ ሀይሎች ሚኤሶ አጠገብ ተገናኙ። ትልቅ ውጊያም አደረጉ። በጦርነቱ የሸዋው ሀይል ድል ስለቀናው ልጅ እያሱ ወደ አፋር በረሃ ሸሸ። የልጅ እያሱ አባት (ራስ ሚካኤል) የልጁን ስልጣን ለማስመለስ 100,00 ጦር አስከትቶ ወደ ሸዋ ዘመተ። ነገር ግን እርሱም እንደ ልጁ ሰገሌ ላይ ተሸነፈ።

          • ***** *****

ልጅ እያሱ የሰገሌውን መርዶ ከሰማ በኋላ በሽሽት ነው የኖረው ለማለት ይቻላል። በመቅደላና በደሴ አነስተኛ ውጊያዎችን ቢያደርግም በለስ ሊቀናው አልቻለም። ከዚያም ወደ አውሳ በረሃ ሄዶ ከወዳጁ ከሱልጣን አቡበከር ጋር ለጥቂት ዓመታት ኖረ። ነገር ግን ጠላቶቹ እዚያም እንዲቆይ አልፈቀዱለትም። ከሀረርጌና ከወሎ ትልቅ ጦር ቢያዘምቱበት ወደ ትግራይ ሸሸ። በትግራይ ውስጥ ለጥቂት ወራት ከቆየ በኋላ በ1915 ተያዘና ፍቼ ታሰረ። እዚያ እያለ የጎጃሙ ራስ ሀይሉ ተክለሀይማኖት እስር ቤቱን ሰብሮ ሊያስወስደው መሆኑ ስለተወራ ሌላ ቦታ እንዲዛወር ተወሰነ። በመሆኑም ወደ ሀረርጌ ተወስዶ ጋራ ሙለታ አምባ ላይ በተሰራለት እስር ቤት እንዲታሰር ተደረገ። በዚህ አምባ ላይም ለአስር ዓመታት ያህል በእስር ከቆየ በኋላ ጥቅምት 1928 መሞቱ ይፋ ሆነ።

          • ***** *****

ልጅ እያሱ ሚካኤል የስልጣን ዘመኑ በእንቆቅልሽ የተመላ ነው። መንግሥቱን ያስተዳደረበት ዘይቤ፣ ከስልጣን የወረደበት ሁኔታ፣ በእስር ላይ ያሳለፈው ህይወትና የሞተበትም ሁኔታ እንቆቅልሽ ነው። ሌላው ይቅርና የተቀበረት ቦታ እንኳ እስከ አሁን ድረስ በትክክል አይታወቅም። እንቆቅልሽ በእንቆቅልሽ! ተሸዋረጋ የሚወለድ ልጅ እምብዛም አይከፋ እምብዛም አይበጅ ትንሽ ወደኋላ ይቀረዋል እንጅ። ባሽከሮቹ ክፋት ደግሞም ባጋፋሪ ዘውዱ ሲዞር አየን ወደ ልጅ ተፈሪ። እያሱ የሚባል አንድ ልጅ ተወልዶ የአባቶቹን መሬት አደረገው ባዶ። መች ባንተ ይሆናል ምኒልክ ንጉሡ አንተ አስበህ ነበር ልትሰጠው ለእያሱ እንኳን ሊነግሥና ይያዛል ለነፍሱ በራስ መኮንን ልጅ ትጠፋለች ነፍሱ ተጌታ ተፈርዷል ዘውዲቱ ሊነግሱ። የልጅ እያሱ ሰው የአባሻንቆ ሎሌ ተለቀለቀለት መወቂያው ሰገሌ። ሰገሌ ሜዳ ላይ የመጣብን መርዶ በቀኝ እጁ ካራ በግራው ብርንዶ። (የወሎው ሼኽ ሑሴን ጂብሪል ስለልጅ እያሱ ተናግረውታል ከተባለው ትንቢት: ምንጭ፣ ቦጋለ ተፈሪ በዙ፡ “ትንቢተ ሼኽ ሑሴን ጅብሪል”፣ አዲስ አበባ፣ 1985)

          • ***** *****
17/6/2018 AD

ከወሒድ ዑመር