አልጋ ወራሽ
አልጋ ወራሽ የአማርኛ ቅጽል ስም ሲሆን በዘውድ የመንግሥት ሥርዓት የአባቱን ዙፋን ለሚወርስ የንጉሥ ልጅ የሚሰጥ ማዕርግ ነው። ይህ ማዕርግ በግዕዝ 'ወራሴ-መንግሥት' ሲሆን በእንግሊዝኛ ደግሞ Crown-Prince በፈረንሳይኛ "Héritier du trône" የሚሉትን ቅጽል-ስሞች የሚተካ ነው።
በኢትዮጵያ ዘውዳዊ የመንግሥት ሥርዓት የቅርብ ታሪክ ከነበሩት አልጋ ወራሾች ለብዙ ዘመናት የማዕርጉ ባለቤት እና የመጨረሻው አልጋ ወራሽ የነበሩት መርድ አዝማች አስፋ ወሰን ነበሩ። እኚህ ሰው አባታቸው ተፈሪ መኮንን ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ተብለው ከነገሡበት ከጥቅምት ፳፫ ቀን ፲፱፻፳፫ ዓ/ም ጀምሮ ከዙፋን እስከወረዱበት እስከ መስከረም ፪ ቀን ፲፱፻፷፮ ዓ/ም ድረስ ለ፵፬ ዓመታት ዙፋኑን ለመውረስ ሲጠባበቁ ኖረዋል።
ከ መስከረም ፲፯ ቀን ፲፱፻፱ ዓ/ም እስከ መጋቢት ፳፬ ቀን ፲፱፻፳፪ ዓ/ም ድረስ የንግሥት ዘውዲቱ አልጋ ወራሽ የነበሩት ራስ ተፈሪ መኮንን (በኋላ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ) ሲሆኑ ከሳቸው በፊት የማዕርጉ ባለቤት የነበሩት የዳግማዊ ምኒልክ ዘውድና ዙፋን ተጠባባቂ የነበሩት ልጅ ኢያሱ ነበሩ።