ቃይንም
ቃይንም በኦሪት ዘፍጥረት 10፡24፣ 11፡13፤ በመጽሐፈ ዜና መዋዕል ቀዳማዊ 1፡18፣ እንዲሁም በሉቃስ ወንጌል 3፡36 መሠረት የአርፋክስድ ልጅና የሳላ አባት ነበረ። የአማርኛ (ኢኦተቤ) ትርጉም እንደ ግሪክ ትርጉም እንዲህ ይላል። ሆኖም በዕብራይስጥ ብሉይ ኪዳን ትርጉም የቃይንም ስም አይታይም፣ በርሱ ፈንታ አርፋክስድ በቀጥታ የሳላ አባት ያደርገዋል። አሁን በዓለም ዙሪያ ያሉት ትርጉሞች የተወሰዱ በተለይ ከዕብራይስጡ ስለሆነ፣ የቃይንም ስም የሚገኘው ብዙ ጊዜ በሉቃስ ወንጌል ብቻ ነው።
ዘፍጥረት 11፡12-13 ስለ ቃይንም እንደሚለው፣ የአርፋክስድ ዕድሜ 135 ዓመታት ሲሆን ቃይንምን ወለደ፣ ከዚያም አርፋክስድ 400 ዓመት ኖረ። የቃይንም ዕድሜ 130 ዓመት ሲሆን ሳላን ወለደ፣ ከዚያም ቃይንም 330 ዓመት ኖረ። እነዚህ ቁጥሮች ከግሪኩ ትርጉም ሲገኙ የዕብራይስጥና ሳምራዊው ትርጉም ቁጥሮች ግን ይለያያሉ።
በመጽሐፈ ኩፋሌ ውስጥ ስሙ ቃይናም ተጽፎ ከአባቱ አርፋክድና ከእናቱ ራሱአያ በ1375 አመተ አለም ተወለደ፤ አርፋክስድም ልጁን መጻሕፍት አስተማረው። አድጎ ቃይናም ለአምባው የሚመች ቦታ በመፈልግ ከጥፋት ውኃ አስቀድሞ የተቀረጸውን ጽሑፍ አገኘ፤ የትጉሃን (ደቂቀ ሴት) ሰማያት አቆጣጠር ነበር። በ1429 አ.አ. ሚስቱን ሜልካ አገባ፣ እርስዋም የያፌት ልጅ የአበዳይ (ወይም እንደ ድሮ ልሳናት የማዳይ) ሴት ልጅ ትባላለች። በ1432 አ.አ. ሜልካ ሳላን ወለደችለት ይላል።
ከመጽሐፍ ቅዱስም ውጭ በሌላ ታሪካዊ ሥነ ጽሑፍ ምንጮች ደግሞ ስለ ቃይንም ብዙ ልዩ ልዩ ልማዶች ይገኛሉ።