ፍልስፍና ከግሪኩ φιλοσοφία (ፊሎዞፊያ) የመጣ ሲሆን ትርጉሙም የጥበብ ፍቅር ነው። ስለዚህ የፍልስፍና ዕውቀት ሁለት ነገሮችን መነሻ ያደረጋል። አንደኛው፣ «ጥበብ አለ» የሚል ሲሆን፣ ሁለተኛው «ይህ ጥበብ ሊደረስበት ይቻላል» የሚል ነው።
የየዘመኑ ሰዎች ጥበብ ላይ ለመድረስ ብዙ መንገዶችን ተጠቅመዋል። አንዳንዶች ሥነ ተረትን ሌሎች ሥነ ተማሎንና እንዲሁም ሥነ ዶግማን ሞክረዋል። ይሁንና እነዚህ አስተሳሰቦች ቁንጽል እውነታዎችን ከመያዝ ባለፈ ፍልስፍና ለመባል አልበቁም።
ፍልስፍናን ከላይ ከተገለጹት የዕውቀት ዘርፎች የሚለየው ዋናው ጉዳይ «አስተማማኝ እውቀትን» ለማግኘት መጣሩ ነው። ማናቸውም የፍልስፍና ዕውቀቶች ያለማቋረጥ ተጠርጥረው፣ ተመርምረውና ተተችተው ግን ፀንተው ሊቆሙ በቻሉ መሪ ሓሳቦች ይመሰረታሉ። ፍልስፍናን የመሪ ሓሳቦች ቁንጽል ስብስብ እንዳይሆን የሚያደርገው አመክንዮ ነው። መሰረታዊ ሃሳቦች በምክንየት ተያይዘው ሲዋቀሩ እና ሰፊ የዕውቀት ሥርዓት ሲገነባ ፍልስፍና ይባላል። በዚህ መንገድ ቁንጽል ሳይሆን ሰፊ፣ ተልካሻ ሳይሆን አስተማማኝ፣ የተነጣጠለ ሳይሆን ሥርዓታዊ ዕውቀት ይገኛል።
|