መኪና የሚለው ቃል 'macchina' ከሚለው የጣሊያንኛ ቃል የተወረሰ ቃል ሲሆን፣ (ወይም አውቶሞቢልተሽከርካሪ) ከሥፍራ ወደ ሥፍራ በመንኮራኩር ላይ በሞቶር የሚነዳ ተንቀሳቃሽ አይነት ነው። ስዎችም ሆነ ዕቃ በመንገዶች ላይ ለማዛወር ይጠቀማል። በ1999 ዓ.ም.፣ በመላ ዓለም ውስጥ የመኪናዎች ቁጥር 800 ሚሊዮን ያህል ነበር። በተለምዶ «መኪና» የሚለው ስም የሚሰጠው ከዶቅዶቄ ትልቅ፣ ከካሚዎንም ወይም ከአውቶቡስ ትንሽ ለሆነ ባለሞቶር ተሽከርካሪ ነው፤ አንዳንዴ ግን ቀላል ካሚዎኖች ከመኪናዎች ጋር መመደብ ይቻላል። በአማካኝ ለመኪናዎች የተሳፋሪዎች ቁጥር ችሎታ 5 ሰዎች ቢሆን፣ በየአይነቱ ግን ከ1 እስከ 9 መቀመጫዎች ድረስ በመገኘት ይለያያል።

1953 ዓ.ም. ሲምካ አሮንድ P60 ኤሊዜ ረሽ
 
ፈቢስት በ1664 ያቀደው እንፋሎት ጨዋታ

ቤንዚን የሚሄድ ተግባራዊ መኪና መጀመርያ በጀርመን ሰዎች በ1877 ዓ.ም. ተፈጠረ። ከዚያ በፊት ግን በእንፋሎትም ሆነ በኤሌክትሪክ የሚነዱ መኪናዎች ይገኙ ነበር።

መጀመርያ በእንፋሎት የሚነዳ ተሽከርካሪ የታቀደው በኢየሱሳዊው ሚሲዮን ቄስ በቻይና፣ የቤልጅግ ኗሪ ፈርዲናንድ ፈርቢስት1664 ዓ.ም. ነበር። እሱ በጻፈው መግለጫ መሠረት፣ ይህ ተሽከርካሪ ለቻይና ንጉሥ ካንግሺ ለጨዋታ እንዲሆን ጥቃቅን ምሳሌ ብቻ ነበር፤ እቅዱም በተግባር ከተሠራ ኖሮ አይታወቅም።

 
የኩንዮ እንፋሎት ጋሪ፣ 1763 ዓ.ም.

ከዚያ በኋላ፣ በ1761 ዓ.ም. የፈረንሳይ ሠራዊት መድፎችን ለመሸክምና ለማዛወር የጠቀመ የንፋሎት ጋሪ በኒኮላ-ዦሴፍ ኩንዮ ተፈጠረ። በመጀመርያ የፈረንሳይ መንግሥት ትኩረት በዚህ ፍጥረት ተሳበና በ1763 ዓ.ም. ሁለተኛ እንፋሎት ጋሪ ተሠራ። ዳሩ ግን ለረጅም ጊዜ እንፋሎት ማስገኘት ስላልቻለ ተግባራዊው ዋጋ ጥቂት በመሆኑ፣ ወደ ማከመቻ ሥፍራ ተላከ። የመድፍ አለቃ ሙሴ ሮላንድ እንደገና በ1792 ዓ.ም. አገኘው፣ ነገር ግን ናፖሌዎን ለዚህ ጉድ ምንም ፍላጎት አልነበረውምና ሃሣቡ ለጊዜው ተረሳ።

 
የሙርዶክ እንፋሎት ሠረገላ፣ 1776 ዓ.ም.

በዚሁም መካከል፤ በ1776 ዓ.ም. የስኮትላንድ ሰው ዊሊያም ሙርዶክ ባለ ሦስት መንኮራኩር የእንፋሎት ሠረገላ ሠራ። ጊዜውን ባለማግኘቱ ግን ሥራው መቋረጥ ነበረበት።

 
የለንደን እንፋሎት ሠረገላ፣ 1795 ዓ.ም.

ከዚያ በ1793 ዓ.ም. የሙርዶክ ጎረቤት የነበረ ሌላው የብሪታንያ ኗሪ ሪቻርድ ትሬቪሲክ የራሱን እንፋሎት ሠረገላ ሠራ። በ1795 ዓ.ም. ደግሞ «የለንደን እንፋሎት ሠረገላ» ፈጠረ፤ ይህም መኪና ለ10 ማይል በለንደን መንገዶች ላይ ስምንት ሰዎችን ወሰደ፤ ጉዞውም ከሰዓት በላይ ፈጀ። ሆኖም በኋላ ጊዜ በአጋጣሚ ግጭት ተጋጠመና ፈጠራው ለጊዜው ጠፋ። ብዙ ጊዜ ሳያልፍ ሌሎች ሰዎች አዳዲስ አይነቶች የእንፋሎት ተሽከርካሪዎች ሠሩ።

1799 ዓ.ም. ደግሞ ውስጣዊ ፈነዳ ኤንጂንስዊስ አገር ተፈጠረ፤ በመጀመርያው ይህን ፈጠራ ያካሄደው ጋዝ ሃይድሮጅን ብቻ ነበረ። በ1818 ዓ.ም. ሱሙኤል ብራውን በዚህ አይነት መሣርያ አንዱን ጋሪ በለንደን ኮረብታ ላይ እንዲወጣ አደረገ፤ የሙከራው ከፍተኛ ዋጋ ግን ተግባራዊ ፈጠራ እንዳይሆን ከለከለ።


ከዚህ ትንሽ በኋላ፣ በ1820 ዓ.ም. የሀንጋሪ ሰው አንዮስ የድሊክ ለመጀመርያው ጊዜ በኤሌክትሪክ ሞቶር የሚሮጥ ትንሽ የተሽከርካሪ ምሳሌ ሠራ። እንዲሁም በአሜሪካ1826 ዓ.ም. እና በሆላንድ1827 ዓ.ም. ተመሳሳይ ባለ ኤሌክትሪክ ሞቶር ናሙናዎች ተሠሩ። በቅርብ ጊዜ ከዚያ ቀጥሎ፣ የስኮትላንድ ሰዎች መጀመርያው ሙሉ-መጠን ኤሌክትሪክ መኪና ለመሥራት ተከናወኑ። በሚከተሉት አሥርታት ላይ (1830ዎች-1840ዎች ዓ.ም.)፣ የእንፋሎት መኪና እና የኤሌክትሪክ መኪና ቀስ በቀስ በአውሮጳና በአሜሪካ መንገዶች ላይ ይታዩ ጀመር፤ እንደ ወትሮ ከቆየው ከባለ ፈረስ-ጋሪው ትራፊክ አጠገብ አነስተኛ ፈንታ ብቻ ወሰዱ እንጂ በዚያው ዘመን እኚህ አዳዲስ ፈጠራዎች እጅግ ብርቅ ዕይታ ሆነው ቀሩ። በተጨማሪ፣ በአገር ቤት መንገድ በሩቅ ጉዞ ለመሔድ ባለመቻላቸውና በጣም ውድ በመሆናቸው፣ ተግባራዊ ጥቅማቸው በከተማዎች ውስጥ ብቻ፣ በተለይም ለሀብታሞች ወይም እንደ ሕዝባዊ መጓጓዣ (እንደ ታክሲ) ነበር። ለፈረሶች አስደንጋጭ ሥራዎች እንደ ሆኑ መጠን፣ የእንግሊዝ መንግሥት መጀመርያ በ1853 ዓ.ም. የፍጥነት ወሰን በዚህ አይነት ትራፊክ ጣለ፤ ይህም ወሰን በከተማ 5 ማይል (8 ኪ/ሜ) በየሰአቱ ብቻ ነበረ። በ1857 ዓ.ም. የእንግሊዝ መንግሥት ባወጣ ሕግ ወሰኑን እንደገና ወደ 2 ማይል (3 ኪ/ሜ) በየሰአቱ ቀነሰው፤ ከዚህም በላይ ቀይ ባንዲራ የያዘ እግር መንገደኛ በጋሪው ፊት እንዲቀድመው ተገደደ። ስለዚህ «ፈረስ የለሽ ጋሪዎች» ከለንደን መንገዶች ለ30 ዓመታት ያህል ከማጥፋት ሁሉ ትንሽ ቀሩ። በመነጻጸር በፈረንሳይና በአሜሪካ አገራት በሕግ ቢታገሡም፣ ገና አልፎ አልፎ ብቻ የሚታዩ ድንቆች ይሆኑ ነበር።

 
ለኗር ሂፖሞቢል 1855 ዓ.ም.

በዚሁም መካከል፣ በ1855 ዓ.ም. የቤልጅግ ሰው ኤቲየን ለኗር በሃይድሮጅን ጋዝ ውስጣዊ ፈነዳ ኤንጂን የሚነዳ መኪና ወይም «ሂፖሞቢል» ፈጠረ። በሙከራው ጉዞ 11 ማይል በፓሪስ መንገዶች በ3 ሰአቶች ጨረሰ። ለኗር 350 ያህል ሂፖሞቢሎችን ሸጠ።

 
የማርኩስ መጀመርያ መኪና 1862 ዓ.ም.

1862 ዓ.ም. የኦስትሪያ ሰው ሲግፍሪድ ማርኩስ ትንሽ ጋሪ በቤንዚን ውስጣዊ ፈነዳ ኤንጂን ሠራ። እንዲያውም ይህ ድርጊት የቤንዚን መኪና ፈጣሪ ያደርገዋል፤ ዳሩ ግን በ2ኛው ዓለማዊ ጦርነት ጊዜ ናዚ ባለሥልጣናት ይህን ዒላማ ከጀርመን መዝገቦች አስወገዱ፤ ይህም አቶ ማርኩስ ከአይሁዳዊ ዘር ስለነበር ነው።

 
1877 ዓ.ም. ቤንዝ ሞቶር-ጋሪ

በማርኩስ ፈንታ በቤንዚን የሚሮጠውን ዘመናዊ መኪና የመፍጠር ክብር የሚሰጠው ለካርል ቤንዝ ሆነ። በ1877 ዓ.ም. በማንሃይም ጀርመን አገር መጀመርያ ቤንዝ ሞቶር-ጋሪ ሠራ። በ1880 ዓ.ም. ይህን ሞዴል በጀርመንና በፈረንሳይ በገበያው ላይ ይሸጥ ጀመር። በዚያም አመት የካርል ቤንዝ ሚስት ቤርጣ ቤንዝ ለመጀመርያው ጊዜ ለረጅም ጉዞ (106 ኪ/ሜ) በዚህ አይነት መኪና ሄደች። ከዚህ ትንሽ በኋላ በ1881 ዓ.ም. ሌላው ጀርመናዊ ጎትሊብ ዳይምለር የራሱን መጀመርያ ቤንዚን አውቶሞቢል ሠራ።

በዚሁ ወቅት፣ በርካታ ሰዎች በኤውሮጳም ሆነ በአሜሪካ የቤንዚን መኪና መሥራት ንግድ ሞከሩ። በ1881 ዓ.ም. በፈረንሳይ አንድ የመኪና መሥሪያ ድርጅት (ፓንሃርድና ሌቫሦር) ቆሞ ነበር፤ እንዲሁም በ1885 ዓ.ም. በአሜሪካ ነበር (ዱርዬ ሞቶር-ጋሪ ድርጅት)። ከ1892 ዓ.ም. ጀምሮ፣ አሜሪካና ፈረንሳይ አገራት ሁለቱ በጅምላ በገፍ ምርት መኪናን ለመስራት ዝግጁ ነበሩ። ሄንሪ ፎርድ በዚያው ዓመት የዲትሮይት አውቶሞቢል ድርጅት መሠረተ። በቶሎ ግን በ1894 ዓ.ም. ፋብሪካው የቆመው ኦልድስ የሞቶር ተሽከርካሪ ድርጅት አንደኛውን ሥፍራ ወሰደ። በዓመቱም ውስጥ አያሌ ሌሎች ተወዳዳሪዎች ድርጅቶች ለአሜሪካ መንገዶች ብዙ ሺህ መኪናዎች ሠሩ፤ እነርሱም ዊንቶን ሞቶር ጋሪዎችፎርድ ሞቶሮችካዲላክቶማስ ቢ ጄፍሪ ድርጅት ነበሩ። በ1895 ዓ.ም. መጨረሻ፣ 9000 ያህል የቤንዚን መኪናዎች በአሜሪካ ነበሩ። በዚሁ ሰአት በአሜሪካ ከተገኙት መኪናዎች መካከል 40 ከመቶ የእንፋሎት አይነት ሲሆኑ፣ 38 ከመቶ የኤሌክትሪክ አይነትና 22 ከመቶ ብቻ የቤንዚን አይነት ነበሩ። ከ10 አመታት በኋላ ግን የቤንዚን መኪና ከሌሎቹ አይነቶች ይልቅ የተወደደው ዘዴ ሆነው ነበር። ይህም የሆነባቸው ሳቢያዎች ሁለት ናቸው፤ አንደኛው የኤሌክትሪክ መኪና ባትሪ በዚያን ጊዜ ቻርጅ ሳይደረግለት ከ1 ሳአት በላይ ሊጠቀም ስላልቻለ ነው፤ ለአጭር ጉዞዎች ብቻ ተስማሚ ነበሩ። ሁለተኛው፤ በቂ የፔትሮሌዩም ዘይት ምንጮጭ በመገኘታቸው ቤንዚን ርካሽ የነዳጅ አይነት ሆነ። ከዚህ በላይ ከ1904 ዓ.ም. ጀምሮ የቤንዚን መኪና አጀማመር ዘዴ እጅግ ከለለ። ስለዚህ ጥቂት አመታት ስያልፍ የእንፋሎት መኪናና የኤሌክትሪክ መኪና ጥቅም ለጊዜው ተረሳ።