መርሻ ናሁሰናይ

የኢትዮጵያ ለውጥ አራማጅ (1850 - 1937)

አቶ መርሻ ናሁ ሰናይ (1850 ገደማ - 1937 ገደማ እ.ኤ.አ) ከዓጼ ምኒልክ ዘመነ ሥልጣን እስከ ዓጼ ኃይለሥላሴ ድረስ ለሀገራቸው ከፍተኛ ምሣሌያዊ አገልግሎት ያበረከቱ ኢትዮጵያዊ ነበሩ። ከ1890ዎቹ መጀመሪያ እስከ 1902 እ.ኤ.አሐረር የታሪካዊው ጄልዴሳ እና የአካባቢው አስተዳዳሪ ሆነው አገልግለዋል። የድሬዳዋ ከተማ እንዲቆረቆር ቁልፍ ሚና ከመጫወታቸውም በላይ ከ1902 እስከ 1906 እ.ኤ.አ የድሬዳዋና አካባቢዋ የመጀመሪያው አስተዳዳሪ ሆነው ሰርተዋል። የዓፄ ምኒልክና የራስ መኮንን አማካሪና የቅርብ ረዳት በመሆንም በወቅቱ ሀገራዊና ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች ላይ ተሳታፊ ለመሆን እድል አግኝተዋል። አቶ መርሻ ዘመናዊ ዕውቀትን የቀሰሙ፤ የፈረንሳይኛ ቋንቋን ያጠኑ፤ ስለአውሮጳ ታሪክና ባህል ሰፊ ዕውቀት የነበራቸውና በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭው ዓለም ለመታወቅ የበቁ አስተዋይ ሰው ነበሩ። የምድር ባቡር ወደ ኢትዮጵያ እንዲገባ ካደረጉት ልዩ አሰተዋጽኦ በተጨማሪ የባቡር ሀዲዱ የጥበቃ ሃይል ኃላፊ በመሆን ጡረታ እስከወጡበት ጊዜ ድረስ አገልግለዋል። በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻና በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ በተፈጠረው ሰላምና መረጋጋት ምክንያት የአውሮጳ ስልጣኔ ወደ ሀገር እንዲገባና ንግድ እንዲዳብር እንዲሁም ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ለውጥ እንዲመጣ ከደከሙት በርካታ ኢትዮጵያውያን መካከል እንዱ ነበሩ። ይህ አጭር የህይወት ታሪክ (የእንግሊዝኛውን ውክፔድያ ባዮግራፊ ጨምሮ [1] ) ለዛሬውና መጪው ትውልድ አርአያነታቸውን ለማሳየትና ትምህርትም እንዲሆን ታስቦ የተዘጋጀ ነው።

አቶ መርሻ ናሁሰናይ በ1900 እ.ኤ.አ. ገደማ

ትውልድና አስተዳደግ

ለማስተካከል

መርሻ ናሁሰናይ እንደ አውሮጳ አቆጣጠር በ1850 መጀመሪያ ገደማ በአንኮበር አካባቢ በሽዋ ተወለዱ። እድሜያቸው ለትምህርት እንደደረሰም በአቅራቢያቸው ከሚገኝው ወላጅ አባታቸው ከሚያገለግሉበት ቤተክርስቲያን ገብተው መሠረታዊ የሃይማኖትና ቀለም ትምህርትን እንደቀሰሙ ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፍ የቆየ የቤተሰብ አፈ ታሪክ ያመለክታል። የጎልማሳነት ጊዜያቸውን በአባታቸውን እርሻ ላይ በመርዳት እንዳሳለፉም ይነገራል።

ትዳር ከያዙ በሑዋላ ከቦታ ቦታም እየተዘዋወሩ ሰፊ ዕውቀትንና ልምድን አካብተዋል። አዳዲስ ነገሮችን ለማወቅና ለመሞከር ከፍተኛ ፍላጎት እንደነበራቸው በኋላ ካሳዩት ልዩ ችሎታና ብልህነት መገመት ይቻላል። በተለይም የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ቋንቋዎችን ገና በወጣትነት ሳሉ ለማወቅ መድከማቸው ወደፊት ለሰጡት ከፍተኛ ህዝባዊና መንግስታዊ አገልግሎት ትልቅ መሠረት እንደሆነ ከታሪክ እንረዳለን።

የአቶ መርሻን አስተዳደግ ለመረዳት ምናልባትም ፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት ተክለ ማርያም በኦቶባዮግራፊያቸው [2] ውስጥ የመርሻ ባልንጀራ ስለነበሩት ታላቅ ወንድማቸው ገብረ ጻዲቅ የፃፉትን ማስታወስ ይጠቅም ይሆናል--

"የመሬታችን ግብር እንዳይታጎል አብዩ (ገብረ ጻድቅ) በድቁና እየተለወጠ ይቀድሳል። ነገር ግን ለገብረ ጻድቅ የዕውቀት ዕድል በጣም ተሰጥቶት ነበርና፤ በሰሞነኝነት ታግዶ የሚቀር ሰው አልነበረም። ቅዳሴውን ለገብረ መድኅን (ሌላው ወንድማቸው) ተወለትና፤ እሱ ዕውቀቱን ለመኮትኮት ወደ ደብረ ብርሃን ሄደ። እዚያ ሲማር ቆይቶ፤ ቅኔና ዜማ ካወቀ በኋላ ወደ ደብረ ሊባኖስ ተዛውሮ የሠዓሊነትን ጥበብ ተማረ። እንደዚህ ከልጅነቱ ጀምሮ ብልኅነቱ ይደነቅለት ነበር። በሳያደብር ቤተክርስቲያን ውስጥ የነደፈውን ሐረግና ሥዕል እኔም ደርሼበት አይቼዋለሁ። ከፈረንጆች ጋር ለመተዋወቅና ጥበባቸውን ለመቅዳት ምንጊዜም አይቦዝንም ነበር። ስለዚህ፤ ወደ ዲልዲላ (እንጦጦ)፤ ወደ አንኮበር ይመላለሳል። ወደ አንኮበር እየሄደ ባሩድ እንዴት እንደሚቀምሙና እንደሚወቅጡ ይመለከታል፤ ባሩድ እያጠራቀመ፤ የቀለህ ጠመንጃ እያበጀ ይተኩስበታል።...ቀለሁ የታሰረበት ገመድ ወይም ጠፍር ይጎማምደውና ወደኋላው ይፈናጠራል። አንዳንድ ጊዜ ገብረ ጻድቅን እጁን ወይም ፊቱን ያቆስለዋል" (ገጽ ፯)

እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ1890ዎቹ መጀመሪያ ላይ እድሜያቸው አርባ ዓመት ሲሆን አቶ መርሻ ተወልደው ያደጉበትን ሽዋን ለቀው በሐረር አዲስ ኑሮን ጀመሩ። ወደ ሐረር ከመሄዳቸው በፊት ልጆችንም አፍርተው ነበር። ባለቤታቸው ወይዘሮ ትደነቅያለሽ የዓፄ ምኒልክ ታማኝ አገልጋይና አማካሪ የነበሩት የአቶ መክብብ ልጅ ነበሩ።

ሐረር ላይ ብዙም ሳይኖሩ ታላቁ የአድዋ ጦርነት ተጀመረ። አቶ መርሻ አድዋ ስለመዝመታቸው የሚታወቅ ነገር እስካሁን የለም። ነገር ግን በቅርብ የሚያውቋቸው ሰዎችና ጓደኞቻቸው እንደሞቱና እንደቆሰሉ ከታሪክ እንረዳለን። ለምሣሌ አስተዋዩ ባልንጀራቸው ገብረ ጻዲቅ በራስ መኮንን በተመራው ጦር ውስጥ ተመድበው ሲያገለግሉ ህይወታቸው አልፏል። በጦርነቱም ላይ ስላደረጉት ልዩ አስተዋጽኦ ወንድማቸው ፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት የሚከተለውን ጽፈዋል--

"የጦር ሠራዊት በሰፈር ላይ ስፍራውን እንዲያውቀው፤ መሳሳት እንዲቀር ፕላን ነድፎ ሰጠ። በፕላኑ ላይ፤ የአዝማቹ፤ የራሶቹ፤ የደጃዝማቾቹ፤ የፊታውራሪዎቹ እና የሌሎቹም የጦር አለቆች የወታደሮችም ድንኳኖች በተዋረድነት ተነድፈው፤ ማንም ሰው ፕላኑን እያየ የሰፈሩን ቦታ ለማወቅ እንዲቻለው አደረገ። በሰፈር ቦታ የሚጣሉ ሰዎች ቢኖሩም፤ አጋፋሪዎች ፕላኑን እያዩ ማስተካካል እንዲችሉ አደረገ። ይህንኑ በኋላ ንጉሡም ሰምተው በጣም አደነቁ። የጦርነቱንም ታሪክ እስከ መቀሌ ድረስ ጽፎት ነበር።" (ገጽ ፳፰)

የጄልዴሳና አካባቢው አስተዳዳሪ

ለማስተካከል

ዓጼ ምኒልክ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት እስከሆኑበት እስከ 1889 እ.ኤ.አ. ድረስ አቶ መርሻ መንግስትን በኃላፊነት ደረጃ እንዳገለገሉ እስካሁን የሚታወቅ ነገር የለም። በሐረር ከተማ ለጥቂት ዓመታት ከኖሩና በከተማዋ የፀጥታ (ፖሊስ) ሃይል ኃላፊ ሆነው ካገለገሉ በኋላ ጄልዴሳ የምትባለው ታሪካዊ ከተማና አካባባዋ አስተዳደሪ ሆነው ተሾሙ።

ጄልዴሳ ዛሬ በሱማሌ ክልል የምትገኝ መንደር ናት። በዚያን ጊዜ ግን ሽዋንና የተቀሩትን የኢትዮጵያ ክፍሎች ከቀይ ባሕርና ከገልፍ ኦፍ ኤደን (Gulf of Aden) ጋር ያገናኝ የነበረው የካራቫን (caravan) ንግድ መተላለፊያ በር ነበረች። የጉምሩክ መቀመጫም ነበረች። ስለሆነም አቶ መርሻ ስትራቴጂክ ቦታን የማስተዳደር ልዩ ኃላፊነት ተጥሎባቸው ነበር። አንዳንድ መረጃዎች የሚጠቁሙት ደግሞ ከኢትዮጵያ የድንበር ክልል እስከ አዋሽ ድረስ ያለውን አካባቢ በሙሉ ይቆጣጠሩ እንደነበር ነው። [3] ለማስታወስ ያህል ኢትዮጵያ በጊዜው ከብሪቲሽ ከፈረንሳይና ከጣልያን ሶማሌ ላንድ (British Somaliland, French Somaliland, and Italian Somaliland) ጋር ትዋሰን ነበር።

ከዓጼ ምኒልክ ቀዳሚ ዓላማዎች አንዱ የኢትዮጵያን ወሰን መካለልና ማስከበር ስለነበር አቶ መርሻ በተደረገው ጥረትና ድካም ተሳትፈዋል። በተለይም በድንበር እና አካባቢዎች ጥበቃ ረገድ ከፍተኛ ድርሻን አበርክተዋል። ከጄልዴሳ አስተዳዳሪነታቸው በፊት የሐረር ፖሊስ ኃላፊ ሆነው ማገልገላቸው [4] [5] ለፀጥታው ሥራ እንዳዘጋጃቸው ይታመናል።

ሌላው የዓጼ ምኒልክ ዐቢይ ዕቅድ ደግሞ ኢትዮጵያ ከውጭው አለም ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ እንዲሁም የንግድና ኢኮኖሚ ግንኙነት ማጠናከር ነበር። አቶ መርሻ በዚህም መስክ ልዩ አስተዋፅዖ አድርገዋል። በተለይም ከአድዋ ድል በኋላ የአውሮጳ የአሜሪካና የሌሎች ሀገሮች መንግስታት የኢትዮጵያን ነፃነትና ሉዓላዊነት ለመቀበል መወሰናቸው ለዘመናት ሲጠበቅ የነበረውን ስልጣኔ ለማስገባት አመቺ ሁኔታን በመፍጠሩ በርካታ ዲፕሎማቶች፤ ጋዜጠኞችና ሳይንቲስቶች፤ ፀሀፊዎችና ቱሪስቶች ኢትዮጵያን ጎበኙ። አብዛኛዎቹ የውጭ ሀገር ዜጎች ወደ አዲስ አበባ ሐረርና የተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ለመሄድ በወቅቱ ከሞላ ጎደል ሰላማዊ በነበረው የጄልዴሳ መንገድ ማለፍ ስለነበረባቸው አቶ መርሻ እንግዶቹን በክብር የመቀበልና ለቀጣዩ ጉዞአቸው የሚያስፈልገውን የማሟላት ከፍተኛ አደራ ተጥሎባቸው ነበር። ዓጼ ምኒልክና የሐረሩ ገዢ ራስ መኮንንም ጎብኚዎቹ ለሚያልፉባቸው ቦታዎች አስተዳዳሪዎች ሁሉ ዘመናዊ መስተንግዶ እንዲያደርጉ ጥብቅ ትዕዛዝ አስተላልፈው ነበር። በ1897 እ.ኤ.አ. ኢትዮጵያን ከጎበኙትና በእንግሊዝ መንግስት ስም የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ስምምነቱን ከፈረሙት ከንግስት ቪክቶሪያ ልዩ መልዕክተኛ ሰር ረኔል ሮድ (Sir Rennell Rodd) ጋር አብረው የመጡት ካውንት (ሎርድ) ኤድዋርድ ግሌይቸን (Count/Lord Edward Gleichen) በጻፉት መፅሐፍ ውስጥ የሚከተለውን አስፍረዋል--

"...የሚቀጥለው ቀን ጄልዴሳ አደረሰን፡ እዚያም በአስተዳዳሪው በአቶ መርሻ ከፍተኛ አቀባበል ተደረገልን። ከአቢሲንያ (ኢትዮጵያ) ክልል መድረሳችንንም ለማሳየት አስተዳዳሪው መሳሪያ በታጠቁና የሀገሪቷን ስንደቅ ዓላማ በያዙ ወታደሮች በመታጀብ ተቀበሉን። ሰንደቅ ዓላማው እምብዛም አልማረከንም በሰባራ እንጨት ላይ በሚስማር ከተመቱ ቢጫ ቀይአረንጓዴ ጨርቆች የተሰራ ስለነበር። የክብር ዘቡና አቀባበሉ ግን እጅግ የሚያስደስት ነበር።" [6]

 
አቶ መርሻ በጄልዴሳ ለእንግሊዙ ልዩ መልዕክተኛ ሰር ረኔል ሮድን ያደረጉትን የአቀባበል ስርዓት የሚያሳይ ስዕል (ከካውንት ግሌይቸን መጽሐፍ 1898 እ.ኤ.አ)

የጉምሩክ ኃላፊ

ለማስተካከል

አቶ መርሻ የጄልዴሳ ጉምሩክ ኃላፊ ስለነበሩ ወደ ሀገሪቱ የሚወጣውንና የሚገባውን ሁሉ በበላይነት ይቆጣጠሩ ነበር። ሸቀጦች ዘይላ በተባለው የብሪትሽ ሶማሌላንድ ወደብና በጅቡቲ (ፍሬንች ሶማሌላንድ) በኩል እንደልብ ይገቡና ይወጡ ስለነበር ከተማዋ በንግዱ ዓለም ታዋቂ ሆና ነበር። ለምሣሌ ኢትዮጵያና እንግሊዝ (ብሪታንያ) በ1897 እ.ኤ.አ. በፈረሙት ዲፕሎማሲያዊ ውል አንቀጽ ሦስት መሠረት ጄልዴሳ ለሁለቱም ሀገሮች ንግድ ክፍት እንድትሆን ስምምነት ላይ ተደርሶ ነበር።[7]

የካራቫን ነጋዴዎች እና መንገደኞች ጄልዴሳ ሲደርሱ ከሀገር ውጭ ያመጧቸውን ግመሎችና በቅሎዎች ወደመጡብት ሰደው ለቀጣዩ ሀገር ውስጥ ጉዟቸው የሚይስፈልጓቸውን እንሰሳት ከአካባቢው ነዋሪዎች እንዲከራዩ ይደረግ ነበር። ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባ ዕቃ ቀረጥ እንዲከፈልበት ስለተደረገም ለመንግስት ከፍተኛ የገቢ ምንጭም ሆኖ ነበር። ኢትዮጵያ በጊዜው እንደ ቡና፤ የእንሰሳት ቆዳ፤ ከብት፤ የዝሆን ጥርሶችና የመሳሳሉትን ሸቀጦች ወደተለያዩ የአፍሪቃ፤ እስያ፤ መካከለኛው ምሥራቅና አውሮጳ ሀገሮች በኤደን በኩል ትልክ ነበር። በተለይም የጅቡቲ ወደብ መከፈት ለጄልዴሳ ጉምሩክ መጠናከርና ለንግድ መስፋፋት ከፍተኛ እርዳታ አድርጓል፡ አቶ መርሻም ወደ ጁቡቲ ለሥራ ይሄዱ ነበር። [8] በ1902 እ.ኤ.አ ድሬዳዋ ስትቆረቆር የከተማውና አካባቢዋ አስተዳዳሪና የድሬዳዋ ጉምሩክ የመጀመሪያው ኃላፊ ሆኑ።

የዓጼ ምኒልክ አማካሪ

ለማስተካከል

አቶ መርሻ ዘመናዊ ሥልጣኔ ወደ ኢትዮጵያ እንዲገባና ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገት እንዲመጣ ይገፋፉ ከነበሩት ለውጥ ፈላጊ ስዎች እንዱና ቀዳሚ ነበሩ። ዓጼ ምኒልክና ራስ መኮንን ያዘዟቸውን ሥራዎች ሁሉ በትጋት በመፈፀምም ሆነ አዳዲሰ ሀሳቦችና የቴክኖሎጂ ውጤቶች ወደ ሀገር እንዲገቡ ጠቃሚ ምክሮችን በመለገስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አደርገዋል። ታዋቂው የታሪክ ተመራማሪና ፀሃፊ ተክለፃድቅ መኩሪያ አፄ ምኒልክና የኢትዮጵያ አንድነት በተባለው መጽሐሃፋቸው ላይ የሚከተለውን ብለዋል--

“ዐፄ ምኒልክ የነዚህንና የውጭ አገር ተወላጅ አማካሪዎች ምክር በመስማት እውጭ አገር ደርሰው መጠነኛ እውቀት እየቀሰሙ የተመለሱትን የነግራዝማች ዬሴፍን፤ የነነጋድራስ ዘውገን፤ የእነ አቶ አጥሜን፤ የነ አቶ መርሻ ናሁ ሠናይን፤ የነ ብላታ ገብረ እግዚአብሔርን፤ የነ ከንቲባ ገብሩን፤ የነአለቃ ታየን፤ የነነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይክዳኝን፤ የነአቶ ኃይለማርያም ስራብዮንን፤ አስተያየት በማዳመጥ በአገራቸው የአውሮፓን ሥልጣኔ ለማስገባት ታጥቀው ተነሡ።” [9]


የምድር ባቡር ግንባታ ሥራ ተቆጣጣሪ

ለማስተካከል

በ1894 እ.ኤ.አ ዓጼ ምኒልክ የምድር ባቡር ወደ ኢትዮጵያ እንዲገባ ከተስማሙ በኋላ የቅርብ አማካሪዎቻቸው የሆኑት የስዊሱ ተወላጅ አልፍሬድ ኢልግ (Alfred Ilg: 1854-1916) እና ፈረንሳዊው ሌዎን ሸፍነ (Leon Chefneux: 1853- 1927) ለሀዲዱ ግንባታ ሥራ የሚያስፈልገውን መሰናዶ ጀመሩ። [10] የምድር ባቡር ኩባንያም በአስቸኳይ ተቋቋመ። የባቡር ሃዲዱ ሥራ በ1897 እ.ኤ.አ ሲጀመር አቶ መርሻ ከኢትዮጵያ በኩል በበላይነት እንዲቆጣጠሩ በምኒልክ አደራ ተጣለባቸው።[11] ለዚህም ኃላፊነት የበቁት የባቡር ሀዲዱ የሚይልፍባቸው ቦታዎችና ህዝቦች አስተዳዳሪ በመሆናቸው ብቻ ሳይሆን የፈረንሳይኛ ቋንቋን ጠንቅቀው ስላጠኑና ሰለውጭው ዓለምም ሰፊ ዕውቀት ስለነበራቸውም ጭምር ነበር። በጁላይ 1900 እ.ኤ.አ. ሀዲዱ ከጅቡቲ ተነሥቶ ደወሌ ከተባለችው የኢትዮጵያ ድንበር ወረዳ ሲደርስ በተደረገው የምረቃ ስነሥርዓት ላይ ዓጼ ምኒልክን ወክለው ተገኝተዋል። [12] በሥነ ሥርዓቱ ላይ ከፈረንሳይ መንግሥት በኩል የፍሬንች ሶማሌላንድ (French Somaliland) ገዢ ጋብሪዬል ሉዊ አንጉልቮ (Gabriel Luis Angoulvant) የተገኙ ሲሆን የምድር ባቡር ኩባንያው ተጠሪዎችና ሰራተኞችም ተገኝተው ነበር። በጅቡቲ የኢትዮጵያ ቆንስል የነበሩት አቶ ዮሴፍ ዘገላንም በምረቃው ተካፋይ ከነበሩት የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት አንዱ ነበሩ።


 
ዓጼ ምኒልክ ታመው ለጠበል ደብረ ሊባኖስ በከረሙበት ጊዜ ለአቶ መርሻ የፃፉት ደብዳቤ (1909 እ.ኤ.አ.)


የሀዲድ ግንባታው ከተጀመረ ከአምስት ዓመት በኋላ በ1902 እ.ኤ.አ. ድሬዳዋ ወደፊት ከተመሠረትችበት ቦታ ደረሰ። ከዚያም በገንዘብና በዲፕሎማሲያዊ ችግር ሥራው ለሰባት ዓመት ተቋርጦ በ1909 እ.ኤ.አ. እንደገና ሲጀመር አቶ መርሻ በድጋሚ ግንባታውን እንዲቆጣጠሩ በዓፄ ምኒልክ ተጠየቁ። በታዘዙትም መሰረት እስከ አዋሽ ያለውን ሀዲድ በውሉ መሠረት እንዲጠናቀቅ አድርገዋል። ሀዲዱ አዲስ አበባ የደረሰው እ.ኤ.አ. በ1917 ራስ ተፈሪ መኮንን (በኋላ ዓፄ ኃይለሥላሴ) አልጋ ወራሽ በነበሩበት ጊዜ ነበር።

 
አንበሣ፡ የመጀመሪያው ባቡር

የምድር ባቡር ወደ ኢትዮጵያ መግባት በሀገሪቱ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ኢኮኖሚያና ማህበራዊ ለውጥን አስከትልዋል። በጅቡቲ በኩል ሸቀጥ ወደተለያዩ ሀገሮች ከድሮው በበለጠ ፍጥነት በባቡር ለማስወጣትና ለማስገባት በመቻሉ ንግድ እንዲጠናከር ረድቷል። [13] በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን የኑሮ ደረጃ በፊት ከነበረው በጣም አድጓል። በርካታ መንደሮችና ከተሞች በባቡር ሀዲዱ ምክንያት ተቋቁመዋል። የህዝብ ከቦታ ቦታ መዘዋወርም ጨምሯል። ከሁሉም በላይ ደግሞ የሀዲዱ መዘርጋት ከረጅም ጊዜ መጠራጠርና ቸልታ በኋላ አውሮጵውያኖች በኢትዮጵያ ላይ ኢንቨስትመንት መጀመራቸውን ያመለክታል። አንጋፋውና ታዋቂው የታሪክ ምሁር ዶ/ር ሪቻርድ ፓንክረስት የባቡር ሀዲዱን የዘመኑ ትልቅ የቴክኖሎጂ ውጤት ብለው ጠርተውታል።


የድሬዳዋ ቆርቋሪና የመጀመሪያ አስተዳዳሪ

ለማስተካከል

ከጅቡቲ የተነሳው የባቡር ሀዲድ እ.ኤ.አ. በ1902 ዛሬ ድሬዳዋ ካለችበት ቦታ ሲደርስ በአቶ መርሻና በፈረንሳዊው ሌዎን ሸፍነ መሪነት አዲስ ከተማ እንዲቆረቆር ትእዛዝ ተሰጠ። [14] የቦታውም ስም መጀመሪያ አዲስ ሐረር ተባለና ትንሽ ቆይቶ ግን ድሬዳዋ የሚል ስያሜ ተሰጠው። በዚያው ዓመት አቶ መርሻ የድሬዳዋና አካባቢው የመጀመሪያ አስተዳዳሪ ሆነው ተሾሙ። ብዙም ሳይቆይ በምድር ባቡር ኩባንያው ባልደረቦችና በበርካታ ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ድካም ድሬዳዋ ቶሎ ቶሎ መገንባት ጀመረች። በአጭር ጊዜ ውስጥም ዘመናዊ የሆነ ከተማ ተቋቋመ።

አቶ መርሻ በከተማውና አካባቢው አስተዳዳሪነት እስከ 1906 እ.ኤ.አ. ድረስ ካገለገሉ በኋላ ለሚቀጥሉት ሃያ ዓመታት ማለትም ጡረታ እስከወጡብት ጊዜ ድረስ የኢሳ ግዛቶች እና የባቡር ሀዲዱ ጥበቃ ሀይል ኃላፊ በመሆን ሰርተዋል። በልጅ ኢያሱ ዘመነ ስልጣን ለአጭር ጊዜ ተሽረው የነበረ ሲሆን ኢያሱ ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ ወደ ቦታቸው መመለሳቸውን የታሪክ መረጃዎች ይጠቁማሉ።


ጡረታና እረፍት

ለማስተካከል

አቶ መርሻ በ1920ኛዎቹ እ.ኤ.አ. አጋማሽ ገደማ በጡረታ ተገለሉ። እድሚያቸው ስለገፋና በበረሐም ረጅም ዘመን ስላሳለፉ ብዙ ሳይቆይ ጤንነታቸውን እያጡ መጡ። የአልጋ ቁራኛ እስከመሆንም ደርሰው ነበር። በጡረታ ላይ እያሉ አብዛኛውን ጊዜ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ያሳለፉ ሲሆን አልፎ አልፎ ግን ከጓደኞቻቸው ጋር ይገናኙ ነበር። ለምሳሌ የታወቁ የካቶሊክ ሃይማኖት ተከታይ ሰለነበሩ ከሚሲዮናውያን ወዳጆቻቸው ከነአባ እንድርያስ (Andre Jarosseau) ጋር በደብዳቤ ይገናኙ ነበር። [15] የካቶሊክ እምነት በሐርርና ዙሪያዋ እንዲጠናከር ከፍተኛ እገዛ አድርገዋል። በርካታ ለሆኑ ወጣት ካቶሊክ ኢትዮጵያዊያኖችም አርአያ ከመሆናቸውም [16] በተጨማሪ ዘመናዊ ትምህርት ካቶሊክ ለሆኑና ላልሆኑ ወጣቶች እንዲዳረስ ረድተዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንዲቋቋምና እንዲጠናከር ከፍተኛ ድርሻ ያበረከቱትና የመጀመሪያው ጥቁር አፍሪቃዊ የንግድ አውሮፕላን አብራሪ ካፕቴን አለማየሁ አበበ ባሳተሙት የህይወት ታሪካቸው ውስጥ የሚከተለውን ፅፈዋል--

“አቶ መርሻ ከነቤተሰቦቻቸው በሐረር ከተማ የታወቁና የተከበሩ የካቶሊክ ሃይማኖት ተከታይ ስለነበሩ ምንሴኘር አንድሬ ዣሩሶ በሚያስተዳድሩት የካቶሊክ ሚሲዮን ገብቼ በአዳሪነት እንድማር ተደረገ።” [17]

አቶ መርሻ ናሁሰናይ በ1937 እ.ኤ.አ. ገደማ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ። እድሚያቸው ሰማንያ አምስት ዓመት አካባቢ ነበር። የተቀበሩትም በሐረር ከተማ ነው። በጣሊያን ወረራ ዘመን ሰለነበር ይመስላል ስለሞታችው ምንም ዓይነት መረጃ እስካሁን አልተገኘም።


 
አቶ መርሻ በጡረታ ላይ ሳሉ (1920ዎቹ አጋማሽ እ.ኤ.አ.)


ቤተሰባቸው

ለማስተካከል

አቶ መርሻ ወይዘሮ ትደነቂያለሽ መክብብን አግብተው አሥራ አንድ ልጆችን ወልደዋል። እነርሱም በየነ፤ ንግሥት፤ ዘውዲቱ፤ አለሙ፤ ወርቄ፤ ደስታ፤ ዮሴፍ፤ ማርቆስ፤ ንጋቱ፤ ዘገየና መደምደሚያ ናቸው። የልጅ ልጆቻቸውና የልጅ ልጅ ልጆቻቸው ዛሬ በኢትዮጵያና ሌሎች ሀገሮች ይኖራሉ። ከነዚህም ውስጥ ብዙዎቹ በተለያዩ መንግስታዊና የግል ድርጅቶች ውስጥ በመስራት ለሀገራቸው አገልግሎትን ስጥተዋል። የአቶ መርሻ የበኩር ልጅ ባላምባራስ በየነ ወደ አውሮጳ በተደጋጋሚ ለልዩ ልዩ ጉዳዎች ከመጓዛቸውም በተጨማሪ ለድሬዳዋና ለሀገራቸው እድገት አስተዋጽኦ አድርገዋል። ለምሣሌ የእቴጌ መነን የሴቶች ትምህርት ቤት በአዲስ ኣአበባ ሲከፍት የመጀመሪያው አስተዳዳሪ ሆነው ያገለገሉ ሲሆን፣ ከደሴ ወደ አሰብ የሚወስደው መንገድ ሲሰራ በሃላፊነት መርተዋል:: ከዚያም ቀደም ብሎ በኢትዮጵያና ብሪትሽ ሶማሌላንድ የክልል ድርድር ሲጀመር ሀገራቸውን ወክለው በኮሚቴው ፀኃፊነት ተሳትፈዋል። ዛሬ በህይውት ካሉት መካከል ደግሞ አቶ አብነት ገብረመስቀል በአዲስ አበባ የሚኖሩ የታወቁ የንግድ ሰውና (businessman) በጎ አድራጊ ናቸው።

የአርአያነትና የአገልግሎት ውለታ

ለማስተካከል

አቶ መርሻ ናሁሰናይ ከሠላሣ ዓመታት በላይ ሀገራቸውን በተለያዩ መስኮች አገልግለዋል። አንደኛ በዓፄ ምኒልክና ራስ መኮንን መሪነት ሐረርና አካባቢዋ ወደ ኢትዮጵያ ከተቀላቀሉ በኋላ በአካባቢው ፀጥታና መረጋጋት እንዲኖር አግዘዋል። ሁለተኛ ከተሞችን በማስተዳደር ረገድ በተለይም የድሬዳዋ ከተማ እንድትቆረቆርና እንድታድግ ልዩ ድርሻ አበርክተዋል። በዚህም ምክንያት ደቻቱ የሚባለው ቦታ ለረጅም ጊዜ ገንደ መርሻ እየተባለ በአካባቢው ነዋሪዎች ይጠራ ነበር። [18] ሦስተኛ ዘመናዊ ስልጣኔ ማለትም ዘመናዊ ሀሣቦች፣ ዘመናዊ የአስተዳደር ዘዴዎች እና የቴክኖሎጂ ውጤቶች (የምድር ባቡርና የመሳሰሉትን) ወደ ሀገር እንዲገቡ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል። ዘመናዊነት ማለት ደግሞ አውሮፓዊ መሆን ሳይሆን ከውጭው ዓለም የሚገኘውን ዕውቀት ተሞክሮና ድጋፍ ለሀገር እድገትና ህዝባዊ ጥቅም የሚውሉባቸውን መንገዶች መፈለግና ተግባራዊ ማድረግ እንደሆነ ከተረዱት አንዱ ነበሩ። በመጨረሻም ኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ዕውቅናን አግኝታ የንግድና ኢንቨስትመንት ተጠቃሚ እንድትሆን እጅግ ደክመዋል። በተለይም ከዓድዋ ድል በኋላ በርካታ የውጭ መልዕክተኞችና እንግዶች ወደ ኢትዮጵያ በመጡበት ጊዜ በጄልዴሳና በድሬዳዋ አስተዳዳሪነታቸው የማስተናገድ እድል ስላገኙ ኢትዮጵያ በቀና መልክ እንድትታይ ልዩ ጥረት አድርገዋል። ለምሣሌ በሮበርት ፒት ስኪነር (Robert Peet Skinner) የተመራው የመጀመሪያው የአሜሪካ ልዑካን በኢትዮጵያ ጎብኝቱን ፈፅሞ ለመመለስ ሲዘጋጅ ድሬዳዋ ላይ በዓፄ ምኒልክ ስም አሸኛኘት ያደረጉትና ከምኒልክ የተላከውንም የስልክ ስንብት መልዕክት ያስተላለፉት አቶ መርሻ ነበሩ። [19] ለእዚህና ለመሳሳሉት ከፍተኛ የሃላፊነት ቦታዎች የበቁት በትዕዛዝ ፈፃሚነታቸው ብቻ ሳይሆን በቋንቋ አዋቂነታቸውና በአስተዋይነታቸውም ጭምር እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ። ሂዩስ ለሩ (Hughes Le Roux) የተባሉት የፈረንሳይ ጋዜጠኛ፤ ፀሃፊና በኋላም ሴኔተር (1860-1925) Le Figaro በተሰኘው ታዋቂ የፈረንሣይ ጋዜጣ ላይ ስለአቶ መርሻ የሚከተለውን ጽፈዋል--

"እኚህ ብልህ ሰው ... ንጉሰ ነገስቱ ለረጅም ዓመታት የሀገሪቱን መግቢያ በር ጠባቂ አድርገው ስለሾሟቸው ያላዩት የዜጋ ዓይነት የለም ።" [20]


 
መርሻ ናሁሰናይ መንገድ (ከዚራ ፤ድሬዳዋ)

የአቶ መርሻ አርአያነትና ሀገራዊ ውለታ በእርግጥ አልተረሳም። በድሬዳዋ ከተማ በዓፄ ኃይለሥላሴ በስማቸው መንገድ ተሰይሞላቸው እስካሁን ድረስ አለ። ድሬዳዋ የተመሠረትችበትን 105ኛ ዓመት በቅርቡ ስታከብር ስማቸው ተጠርቶ ተመስግነዋል። [21] ሆኖም ግን የአቶ መርሻ የህይወት ታሪካቸው ገና አልተፃፈም። በርካታ ኢትዮጵያውያን (የታሪክ ተማሪዎችንና ተመራማሪዎችን ጨምሮ) ማንነታቸውንም ሆነ ሥራቸውን አያውቁም። የመጣበትን የማያውቅ የሚሄድበት ይጠፋዋል እንደተባለው ባለፉት ዘመናት በተለያዩ መስኮች ምሣሌያዊ ተግባራትን የፈፀሙ እንደ አቶ መርሻ ያሉ ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆነ ኢትዮጵያዊያን አንደነበሩ ታሪክ ሰለሚይስተምረን የዛሬውም ሆነ መጪው ትውልድ ልብ ሊላቸው ይገባል። በተለይም ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴ እንደገና እየታየ ባለበት በአሁኑ ጊዜ (የአዳዲስ መንገዶችና ባቡር ሀዲዶችን ግንባታን ጨምሮ ማለት ነው) ለዘመናዊ ሥልጣኔ መግባትና መዳበር ልዩ አስተዋጽኦ አድርገው ያለፉ ኢትዮጵያውያንን የህይወት ታሪክና አርአያነት ጠንቅቆ ማወቁ ከፍተኛ ህብረተሰባዊ ጠቀሜታ እንዳለው ያደጉ ሀገሮች ተሞክሮ ያስገነዝባል።

ዋና የፅሁፍ መረጃዎች

ለማስተካከል
  1. ^ Tadewos Assebework (ታዴዎስ አሰበወርቅ) Mersha Nahusenay bio in English)
  2. ^ ፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት ተክለ ማርያም (፩፱፻፺፰). ኦቶባዮግራፊ (የሕይወት ታሪክ). አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬስ (1998 Eth calendar; 2005 Gregorian)
  3. ^ Rosanna Van Gelder de Pineda (1995). Le Chemin de fer de Djibouti a Addis-Abeba. L'Harmattan. p. 590.
  4. ^ Goedorp, V. With a camera in Somaliland. The World Wide Magazine, Vol. 5; 1900: 505
  5. ^ Martial de Salviac (1900). Un peuple antique, ou une colonie gauloise au pays de Menelik. F. Plantade.
  6. ^ Edward Gleichen (1898). With the Mission to Menelik. E. Arnold.
  7. ^ Augustus Blandy Wylde (1900). Modern Abyssinia. Methuen & Company. p. 476.
  8. ^ Bairu Tafla (2000). Ethiopian Records of the Menilek era: Selected Amharic documents from the Nachlass of Alfred Ilg, 1884-1900. Harrassowitz.
  9. ^ ተክለፃድቅ መኩሪያ (1983). አፄ ምኒልክና የኢትዮጵያ አንድነት. ኩራዝ አሳታሚ ድርጅት፤ አዲስ አበባ
  10. ^ Richard Pankhurst. "The Franco-Ethiopian Railway and its history". 2005.
  11. ^ Imbert-Vier, S. (2011). Tracer des frontières à Djibouti, des territoires et des hommes au XIXe et XXe siècles. Karthala Editions.
  12. ^ "Inauguration de la première section du chemin de fer". L'Année Coloniale: 231. 1900.
  13. ^ Richard Pankhurst. "The beginnings of Ethiopia’s modernisation". 2003.
  14. ^ "L’Abyssinie". Revue de Geographie: annuelle 54: 143–144. 1904.
  15. ^ Bahru Zewde (2005). Pioneers of Change in Ethiopia: The reformist intellectuals of the early twentieth century. Addis Abeba University Press.
  16. ^ Mickaël Bethe-Selassié (2009). La Jeune Ethiopie: Un haut-fonctionnaire éthiopien - Berhana-Marqos Walda-Tsadeq (1892-1943). Paris: L’Harmattan.
  17. ^ ካፕቴን አለማየሁ አበበ (1997). ህይወቴ በአየርና በምድር. አዲስ አበባ
  18. ^ Getahun Mesfin Haile (2003). "Dire Dawa: Random thoughts on a centenary". Addis Tribune.
  19. ^ Robert P. Skinner (1906). Abyssnia-of-today: An Account of the First Mission Sent by the American Government to the Court of the King of Kings, 1903-1904. New York: Longmans, Green & Co.
  20. ^ Hughes Le Roux (April 1901). Le Figaro.
  21. ^ ገዛህኝ ይልማ (ታህሳስ 2000 ዓ.ም.). "ድሬዳዋ የምዕተ ዓመት ጉዞ". ድሬ መጽሔት (ልዩ እትም).