ደጋ እስጢፋኖስ
ደጋ እስጢፋኖስ ጎጃም ጣና ሃይቅ ውስጥ በሚገኘው ደጋ ደሴት ውስጥ የሚገኝ ቤ/ክርስቲያን ሲሆን ወደ200 የሚጠጉ መነኮሳትን ያስተዳድራል። ቤ/ክርስቲያኑ የተቆረቆረው በ13ኛው ክፍለ ዘመን፣ በአጼ ይኩኖ አምላክ የወንድም ልጅ በሂሩተ አምላክ ነበር። ሂሩተ አምላክ ከአቡነ ተክለ ሃይማኖት ጋር በወሎ በሚገኘው ሃይቅ እስጢፋኖስ በአስተማሪያቸው እየሱስ ሞዓ የተማሩ የአንድ ክፍል ሰወች ናቸው።
ቀደምቱ ደጋ እስጢፋንኖስ በ19ኛው ክፍለ ዘመን በእሳት ሲቃጠል አሁን የቆመው ቤ/ክርስቲያን በምትኩ ተሰርቷል። በዚህ ምክንያት ከታሪክ አንጻር የቤ/ክርስቲያኑ ዋና መስዕብ ሆኖ የሚቀርበው ሳይቃጠል የተረፈው ቤተ-መዘክሩ ነው። በዚህ መዘክር የይኩኖ አምላክ፣ ቀዳማዊ ዳዊት፣ ዘርአ ያዕቆብ፣ ዘድንግል፣ ፋሲለደስና ባካፋ የደረቁ ቅሬቶች ይገኛሉ። አጼ ሃይለ ስላሴ በ1951 ደሴቲቱን ከጎበኙ በኋላ የነገስታቱ እሬሳ በመስታውት ሳጥን እንዲቀመጥ አደረጉ። የፋሲለደስ ቅሪት ከሌሎቹ ነገስታት በበለጠ መልኩ እስካሁን ብዙ ሳይበላሽ በመቆየቱ የፊቱን መልክ ከቅሪቱ መገንዘብ ይቻላል።