ኪቲም (ዕብራይስጥ፦ כִּתִּים) በኦሪት ዘፍጥረት 10 መሠረት ከያዋን ልጆች አንዱ ነበር። እንዲሁም ከእርሱ የተወለደው ብሔርና አገራቸው «ኪቲም» ይባላሉ።

በመጽሐፍ ቅዱስ ለማስተካከል

  • ኦሪት ዘኊልቊ ፳፬፡፳፬ ፦ «ከኪቲም ዳርቻ መርከቦች ይመጣሉ፣ አሦርንም ያስጨንቃሉ፣ ዔቦርንም ያስጨንቃሉ፤ እርሱም ደግሞ ወደ ጥፋት ይመጣል።» (ይህ ጥቅስ የአረመኔ ነቢይ በለዓም የነበየ ነው።)
  • ትንቢተ ኢሳይያስ ፳፫፡፩ ፦ «የተርሴስ መርከቦች ሆይ፣ አልቅሱ፤ ፈርሶአልና ቤት የለም፣ መግባትም የለም፤ ከኪቲም አገር ጀምሮ ተገልጦላቸዋል።»... ፲፪ ፦ «አንቺ የተበደልሽ የሲዶና ድንግል ልጅ ሆይ፣ ከእንግዲህ ወዲህ ደስ አይበልሽ፤ ተነሥተሽ ወደ ኪቲም ተሻገሪ፣ በዚያም ደግሞ አታርፊም፡ (እግዚአብሔር) አለ።»
  • ትንቢተ ኤርምያስ ፪፡፲ ፦ «ወደ ኪቲም ደሴቶች እለፉና ተመልከቱ፣ ወደ ቄዳርም ላኩና እጅግ መርምሩ፣ እንደዚህም ያለ ነገር ሆኖ እንደ ሆነ እዩ።»
  • ትንቢተ ሕዝቅኤል ፳፯፡፮ ፦ «ከባሳን ኮምቦል መቅዘፊያሽን ሠርተዋል፣ በዝሆን ጥርስ ከታሻበ ከኪቲም ደሴቶች ዛፍ መቀመጫሽን (የጢሮስ ሠሪዎች) ሠርተዋል።»
  • ትንቢተ ዳንኤል ፲፩፡፴ ፦ «የኪቲም መርከቦች ይመጡበታልና ስለዚህ (የስሜን ንጉሥ) አዝኖ ይመለሳል፣ በቅዱስም ቃል ኪዳን ላይ ይቈጣል፣ ፈቃዱንም ያደርጋል፤ ተመልሶም ቅዱሱን ቃል ኪዳን የተዉትን ሰዎች ይመለከታል።» (በግሪኩ ግን በ«የኪቲም መርከቦች» ፋንታ «የሮማውያን መርከቦች» ይላል።)

መታወቂያዎች ለማስተካከል

በተለመደው ኪቲም የቆጵሮስ ከተማ ኪቲዮን መንስኤ ነው። ይህም ልማድ ጸሐፊው ፍላቪዩስ ዮሴፉስ (90 ዓ.ም. ግድም) እንደ ዘገበው ነው፦

«ከጢሞስ የከጢማን ደሴት ነበረው፤ አሁን ቆጵሮስ ይባላል፤ ከዚያም ነው ደሴቶች ሁሉና አብዛኞቹ የባሕር ዳርቻዎች በዕብራውያን ከጢም ይሰየማሉ፤ በቆጵሮስም ሥያሜውን የጠበቀ አንዱ ከተማ አለ፤ የግሪኮችን ቋንቋ በሚጠቀሙት ዘንድ «ኪቲዮስ» ተብሏልና በዚያ አነጋገር ከ«ከጢም» ስም አላመለጠም።»

በምዕራባውያን አብያተ ክርስቲያን ዘንድ በአዋልድ መጻሕፍት መካከል የሚቆጠረው መጽሐፈ መቃቢስ ፩ ፩፡፩ (ይህ የኢኦተቤ መጽሐፈ መቃብያን አይደለም) ታላቁ እስክንድር መቄዶናዊው ከ«ኪቲም አገር» እንደ መጣ ይላል።

ሙት ባሕር ብራና ጥቅሎች በአንዱ ብራና ጥቅል የብርሃን ልጆችና የጨለማ ልጆች ጦርነት ግን የ«ኪቲም» ሰዎች ከ«አሦር» እንደ ሆኑ ይጻፋል። ሊቁ ዪጋይል ያዲን እንደሚያስብ የዚህ ስውር ፍች «የሮሜ ሰዎች» ለማለት ነበር።

አይሁድ መጽሐፍ ዮሲፖን (10ኛው ክፍለ ዘመን ዓም.) እንዳለው፣ የ«ኪቲም» ወገን በጣልያ ሰፍሮ የሮማውያን ዘር ሆነ። የኪቲም ሰዎች ከቲቤር ወንዝ ደቡብ እያሉ የቶቤል ሕዝብ ደግሞ ከቲቤር ስሜን ነበሩ ይለናል። የኪቲም ሰዎች የቶቤል ሴት ልጆች በግድ ከወሰዷቸው በኋላ በወገኖቹ መካከል ጦርነት ተነሣ። ሆኖም የኪቲም ሰዎች ክልስ ልጆቻቸውን ለቶቤል ወገን ሲያሳዩ፣ ጦርነቱን ተዉ ስላምም ሆነ ይላል።

እንዲሁም አኒዩስ በ1490 ዓም. ባሳተመው ታሪክ ውስጥ «ኪቲም» በጥንት የእስፓንያና የጣልያን ንጉሥ አትላስ ኪቲም ፪ኛ ስም ነበር። ይህን «አትላስ» ወይም «ኢታሉስ» የኢጣልያን ሞክሼ ይለዋል።

የ19ኛው ክፍለ ዘመን ጀርመን አገር መምህር ማክስ ሚውለር እንደ መሰለው፣ የ«ኪቲም» መታወቂያ በአናቶሊያ ከነበረው ብሔር ከ«ሐቲ» ጋር አንድላይ ነበረ። አብዛኞቹ ሊቃውንት ግን የ«ሐቲ»ን ስም ከከነዓን ልጅ ከኬጢ ጋራ አገናኙት።