እንግሊዝኛ

የአንድ ኢንዶ-አውሮፓዊ ቤተሰብ የምዕራብ ጀርመን ቋንቋ
(ከእንግሊዘኛ የተዛወረ)

እንግሊዝኛ የምዕራብ-ጀርመናዊ ቋንቋዎች ቤተሠብ ቋንቋ ነው። በዓለም ላይ በብዙ አገራት ውስጥ ይነገራል። የመጀመሪያ ተናጋሪዎቹ ቁጥር 380 ሚሊዮን ያሕል ሲሆን በብዛት የምድር 3ኛው ቋንቋ ነው። ከዚህ በላይ እስከ 1 ቢሊዮን ሰዎች እንደ ሁለተኛ ቋንቋ ይችሉታል።

እንግሊዝኛ ወይም እንግሊዝኛ ክሪዎል መደበኛ የሆነባቸው አገሮች
EN

እንግሊዝኛ በእንግሊዝ አገር ጀመረ። አንግል እና ሴያክስ የተባሉ ጀርመናዊ ጐሣዎች መጀመርያ የተናገሩት ጥንታዊ እንግሊዝኛ ይባላል። ነገር ግን ይህ እንደ ዛሬው እንግሊዝኛ በጣም አልመሰለም። በ441 አ.ም. ጀምረው እነዚህ ጐሣዎች ከጀርመን ወጥተው በብሪታኒያ ደሴት ሰፈሩ። ቋንቋቸውም የተጻፈበት «ሩን» በተባለው ጽሕፈት ነበር። በ7ኛ መቶ ዘመን ክርስትና ከተቀበሉ በኋላ ግን ቋንቋው በላቲን ፊደል ሊጻፍ ጀመረ።

ከ9ኛ መቶ ዘመን ጀምሮ ብዙ ሠራዊት ከዴንማርክና ከኖርዌ ወደ እንግሊዝ ስለ መጡ ተመሳሳይ ቋንቋ ስለነበራቸው ያን ጊዜ እንግሊዝኛ ከጥንታዊ ኖርስ አያሌ ቃሎች ተበደረ።

1058 ዓ.ም. ዊሊያም 1 «አሸናፊ» ከነሠራዊቱ እንግሊዝ አገርን ወርሮ ንጉስ ከሆነ በኋላ አዲስ መንግሥት ለማቆም መኳንንቶቹን ከፈረንሳይ ከሱ ጋራ አመጣ። የእንግሊዝ መንግሥት ቋንቋ ፈረንሳይኛ ሲሆን ለረጅም ጊዜ (300 አመቶች) እንግሊዝኛ ከትምህርት ቤቶች ተከለክሎ ቋንቋው ለጽሑፍ ሳይሆን እንደ መነጋገርያ ብቻ ስለ ቀረ በዚያን ጊዜ ጠባዩ ብዙ ተለወጠ። እንግሊዝኛ በዚሁ ዘመን እጅግ ብዙ ቃላት ከፈረንሳይኛ ስለተበደረ በፍጹም ሌላ መልክ ይዞ አሁን መካከለኛ እንግሊዝኛ ይባላል። ቻውሰር የተባለው አንድ ስመ ጥሩ የመካከለኛ እንግሊዝኛ ጸሐፊ ነበር።

በ15ኛ መቶ ዘመን «ታላቅ የአናባቢ መፈራረቅ» በሚባለው ለውጥ ምክንያት፡ አናባቢዎቹ ተለውጠው የቋንቋው ድምጽ እንደገና ሌላ መልክ ያዘና ከዊሊያም ሼክስፒር ዘመን ጀምሮ «ዘመናዊ እንግሊዝኛ» ተብሏል።

እንግሊዝኛ ከሌሎቹ ልሣናት ለምሳሌ ከቻይንኛ፥ ከህንዲ፥ ከጃፓንኛ እና ከእስፓንኛ አንዳንድ አዲስ ቃላት ከመውሰድ አላቋረጠም። ከተለያዩ አገሮች የነበሩት ሊቃውንት እርስ በርስ ለመነጋገር የቻሉ የጋራ ካወቁት ልሳናት ከሮማይስጥና ከግሪክ የጥናቶቻቸውን ቃሎች በመምረጥ ነበር። እነዚያ የተክኖሎጂ ቃሎች ደግሞ ወደ እንግሊዝኛ ገቡ፤ ለምሳሌ፣ photograph (ፎቶግራፍ) ከግሪክ photo- ፎቶ (ብርሀን) እና -graph ግራፍ (ሰዕል)፤ ወይም telephone (ተለፎን) ስልክ። ስለዚህ እንግሊዝኛ ከብዙ ቋንቋዎች ይሠራል ሊባል ይችላል።

ሷዴሽ ዝርዝር 207 ዘመናዊ እንግሊዝኛ ቃላት፣ 161 ወይም 78% በቀጥታ ከጥንታዊ እንግሊዝኛ ቃላት ተደረጁ።

ከተረፉትም 46 ቃላት መኃል፤

  • 11 ወይም 5% ከፈረንሳይኛ መጡ (animal, forest, fruit, flower, turn, push, count, river, mountain, round, because።) እንዲያውም "because" ከጥንታዊ እንግሊዝኛ bi + ፈረንሳይኛ cause የሚገኝ ውሁድ ነው።
  • 10 ወይም 5% ከኖርስኛ መጡ (big, they, leg, wing, egg, stab, fog, sky, dirty, rotten)
  • 2 ቃላት ወይም 1% ከሮማይስጥ መጡ (vomit, correct)
  • 2 ቃላት ወይም 1% ከሆላንድኛ መጡ (split, rub)

የተረፉት 21 ቃላት ወይም 10% የመጡ ከጥንታዊ እንግሊዝና ሲሆን፣ ከጥንታዊ እንግሊዝኛ አዲስ ትርጉም ተሰጡ።

ደግሞ ይዩ

ለማስተካከል


 
Wikipedia