ቢትወደድ አልፍሬድ ኢልግዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ኑሮውን ኢትዮጵያ ውስጥ የመሠረተ፤ የስዊትዘርላንድ ዜጋ ነበር። ኢልግ በምሕንድስና ሙያው ባቡር እና የቧንቧ ውሐ ለአገራችን ካስተዋወቃቸው ብዙ ዘመናዊ የሥልጣኔ መስመሮች ሁለቱ ሲሆኑ በንጉሠ ነገሥቱ ፊት ታላቅ ታማኝነትን በማፍራቱ የዘውድ አማካሪ እና የአገሪቱን የውጭ ጉዳይ እስከመምራትም የበቃ ሰው ነበር። ቢትወደድ ኢልግ በዘመናዊት ኢትዮጵያ ታሪክ ብዙ ሚና ከተጫወቱ አውሮፓውያን መሃል ባገሪቱ ባሳለፋቸው ሃያ ሰባት ዓመታት እና ባስቀመጣቸው የልማት አሻራዎቹ የታሪክ ሥፍራው በጣም የጎላ ሆኖ እናገኘዋለን።

ክቡር ቢትወደድ አልፍሬድ ኢልግ

ኢልግ በስዊትዘርላንድ፣ ፍራውንፌልድ በሚባል ከዙሪክ ከተማ በሰሜን-ምሥራቅ አቅጣጫ በሚገኝ ሥፍራ በ መጋቢት ወር ፲፰፻፵፮ ዓ/ም ተወልዶ በስድሳ ሁለት ዓመቱ የገና ዕለት (ታሕሣሥ ፳፱ ቀን) ፲፱፻፰ ዓ/ም ዙሪክ ላይ በልብ ምታት ምክንያት አረፈ።

ታዋቂው የታሪክ ምሁር ሪቻርድ ፓንክኸርስት ዳግማዊ ምኒልክ ገና በልጅነታቸው የዓፄ ተዎድሮስ እስረኛ በነበሩ ጊዜ ቴዎድሮስ አጠገባቸው የነበሩትን አውሮፓዊ ወንጌላያን መድፍና መሣሪያዎች እንዲሠሩላቸው ማግባባታቸውን ልብ አድርገው ነበርና የሸዋ ንጉሥ ሲሆኑ በ ኤደን ላይ የነበረ አንድ የስዊትዘርላንድ ዜጋ ነጋዴ ምሕንድስና የሚያውቁ አውሮፓውያን ባለሙያዎችን እንዲፈልግላቸው ጠይቀውት ነበር ይላል። [1]

ኢልግ እና ሁለት የአገሩ ሰዎች በ፲፰፻፸ ዓ/ም አካባቢ ጉዞዋቸውን ወደኢትዮጵያ አምርተው ሸዋ ሲገቡ ንጉሥ ምኒልክ መጫሚያ እንዲሠራላቸው ያዙትና ሠርቶ ባበረከተላቸውም መጫሚያ እጅግ እንደተደሰቱ ይነገራል። በሌላ ዘገባ ደግሞ ንጉሡ ኢልግን ጠመንጃ እንዲሠራላቸው አዘዙት። ኢልግ ጠመንጃ ለመሥራት ሙያ እንደሌለውና ከውጭ የሚመጣ መሣሪያ እሱ ከሚሠራው እጅግ የላቀ እንደሚሆን ቢያስረዳም፤ ምኒልክ ኃሳባቸውን የማይለውጡ ሆኑ። እሱም እንደተጠየቀው የሙከራውን ውጤት ሲያሳቸው ንጉሡ ተደስተው ይሄንኑ ጠመንጃ በግምጃ ቤታቸው የክብር ቦታ ሰጡት። ያም ሆነ ይህ ኢልግ በንጉሡ በኩል ዘለቄታ የነበረው የበጎ አስተያየትን እንዳተረፈ ግልጽ ነው።

ወዲያው በምሕንድስና ሥራ በደሞዘኝነት ቀጥረውት በየወሩ ሰባት ወይም ስምንት ፓውንድ በጠገራ ብር ይከፍሉት እንደነበር ፓንክኸርስት ዘግቧል።

ኢልግ ከሠራቸው አንዱ አዋሽ ወንዝ ላይ ያቆመው ድልድይ ነው። ስለዚህ ድልድይ ሥራ ኢልግ ሲጽፍ፤ የመጀመሪያው የድልድይ ሥራ እንደነበረና የድልድዩ ቋሚዎች በሰው ሸክም አሥራ አምስት ኪሎ ሜትር ተጉዘው እንደመጡ ይተርክና ሥራውን በሐሩር እና በዶፍ እንዲሁም በማታ የዱር አራዊትን በመቋቋም እራሱ ድንጋይ እየጠረበ፣ ምስማር፣ ችንካር እና ብሎን እያቀለጠ እየቀጠቀጠ እንደሠራው ይነግረናል።

ምኒልክ በሸዋ ንጉሥ ከሆኑ በኋላ ሐዲድ አዘርግተው ባቡር ለማስገባት አሰቡ። ይህም ሀሳባቸው እንዲፈቀድላቸው የበላያቸውን ንጉሠ ነገሥቱን አጤ ዮሐንስን ፈቃድ ጠየቁ። በአጤ ዮሐንስ አካባቢ የነበሩ መኳንንቶች መክረው ምኒልክ ከግዛታቸው ከሸዋ ውጭ ሐዲድ ለመዘርጋት እንደማይችሉ ተነገራቸው።

በሳቸው መቸኮልና መጓጓት ምክንያት አልፍሬድ ኢልግ በሥራና በሀሳብ ተጠምዶ እንደነበር ወዲያውም ለጃንሆይ ምኒልክ የሞዴል ባቡር ተጎታች ጋሪዎችን እየጎተተ በሐዲድ ላይ ሲሄድ የሚያሳይ ሠርቶ ሲያሳያቸው በጣም እንደተደሰቱ ጳውሎስ ኞኞ “አጤ ምኒልክ” በተባለው መጽሐፋቸው ዘግበዋል።

ዓፄ ዮሐንስ ሞት በኋላ ምኒልክ የንጉሠ ነግሥትነትን ዘውድ በጥቅምት ወር ጭነው ወዲያው በኅዳር ወር ላይ የምድር ባቡርን ሥራ አንቀሳቅሰዋል። ለዚህም ኢልግ ከማንኛውም ኩባንያ ጋር ተዋውሎ ሐዲዱን ለማሠራት የሚችልበትን ፈቃድና የሚዋዋልበትን የውል ዓይነት መጋቢት ፩ ቀን ፲፰፻፹፮ ዓ/ም አስጽፈው በማህተማቸው አትመው ሰጡት። ኢልግም ፓሪስ ከተማ ላይ ቢሮ ከፍቶ ለሥራው የሚያስፈልገውን መዋእለ ነዋይ፤ ሥራውን የሚኮናተሩ ድርጅቶችን እና ሌላም ጥናቶችን ማቀናበር ጀመረ።

የዚህ የምድር ባቡር መሥመር ከጂቡቲ ወደብ ተነስቶ አዲስ አበባ ድረስ ፯፻፹፬ ኪሎ ሜትር ሲሆን ሥራው በ፲፰፻፺ ዓ/ም ተጀምሮ ከሀያ ዓመታት በኋላ በ ፲፱፱፻፲ ዓ/ም ተገባደደ። መቸም የኃሳቡ ጸንሳሽ ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክም ሆኑ ሕልማቸውን ዕውን በማድረግ ብዙ አስተዋጽዖ ያስመዘገበው ኢልግም ፍጻሜውን ባያዩትም በኢትዮጵያ የምድር ባቡርን ስናስብ የነዚህ የሁለቱ ሰዎች ትዝታ በታሪክ ተመዝግቦ ይኖራል።

ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ መጋቢት 10 ቀን 1887 ዓ/ም ለስዊስ መንግሥት ሪፑብሊክ ፕሬዚዳንት ከጻፉት ደብዳቤ። [2]

“ሙሴ ኢልግን እጅግ ያገለገለኝ የኔ መሐንዲስ ለዚህ ለፖስታ ማኅበር ለመግባት የሚያስፈልገውን ጉዳይ ሁሉ ለመፈጸም ሙኡ ሥልጣን ሰጥቸዋለሁ።”

ዳግማዊ ምኒልክ በመንግሥታቸው ስርዓትን ለማስገባት፤ ኢትዮጵያአውሮፓ “ክርስቲያን ሕዝብ” ጋር እንዲለማመድ እና በዋናነት ግን በ[[፲፰፻፹፭ ዓ/ም ለአድዋ ጦርነት መንስዔ የሆነውን የውጫሌ ውል ካፈረሱ በኋላ እንደልባቸው ከውጭው ዓለም ጋር ያለኢጣልያ ጣልቃ ገብነት መገናኛ መንገድ አስበው የፖስታ ስርዓትን ሲመሠርቱ በጊዜው የፖስታ ማኅበር ዋና መሥሪያ ቤት በስዊስ ከተማ በርን ላይ ነበር።

ንጉሠ ነገሥቱ የፖስታ ድርጅት ከተቋቋመ በኋላ ወደአገር ውጭ ከጻፏቸው ደብዳቤዎች አንዱ ሐምሌ 13 ቀን 1887 ዓ/ም ኢልግ ወደአገሩ ሄዶ በነበረበት ጊዜ ለሱ የጻፉት ይጠቀሳል።

“ፖስታ ማበጀታችን እንኳን ያንተ የወዳጃችን ደብዳቤና የማንም ነጋዴ ደብዳቤ ሁሉ እንዲመላለስበት ነበር። ያንተ ደብዳቤ መጥፋቱ ፖስታ ለምን ተደላደለ ብለህ አኩርፈህ ይሆን ወይስ የምድር ባቡር እስከ አዲስ አበባ ድረስ እስቲበጅ መጠበቅህ ይሆን? ያለዚያ ያንተን ደብዳቤ የሚውጥ አውሬ ከመንገድ ላይ እንዳለ ቁርጡን አስታውቀኝ።….”

[3] ይላል። የኢልግ መልስ ምን እንደነበር ባናውቅም፣ ምኒልክ ግን የቱን ያህል ናፍቀውት እንደነበር እንገነዘባለን።

የቤተ መንግሥት እነጻ

ለማስተካከል
 
የእንጦጦ ቤተ መንግሥት

ሸዋው ንጉሥ ምኒልክ ዋና ከተማቸውን ከአንኮበር ወደ እንጦጦ ሲያዛውሩ መጀመሪያ የሠፈሩት በድንኳን ነበር። ወዲያ መሐንዲሳቸው አልፍሬድ ኢልግ አዲስ ቤተ መንግሥት እንዲያሠራላቸው በሰጡት ትዕዛዝ መሠረት፣ አሁን ድረስ ቆሞ በቤተ ቅርሳ ቅርስነት የሚያገለግለውን ሕንጻ አሠራላቸው።

ቤተ መንግሥቱ ከአንኮበሩ ቤተ መንግሥት ያነሰ እና በዚያ ጊዜ የነበሩትን ቤተ መንግሥቶች ያህል ስፋት የለውም በሚል በጊዜው ነቀፋ ተሰንዝሮበት ነበር። ሆኖም ምኒልክ የንጉሠ ነገሥትነቱን ሥልጣን እስከጨበጡ ጊዜ ድረስ ተገልግለውበታል። አንዳንዴም ወደሰሜን ሲጓዙ ወይም እንጦጦ ማርያምን ሊሳለሙ ሲሄዱ ያርፉበት እንደነበር ይታወቃል። እሳቸውም ከሞቱ በኋላ እቴጌ ጣይቱ እስከ ዕድሜያቸው መጨረሻ ድረስ በግዞት ኖረውበታል።

አዲስ አበባም የሚገኘው “ታላቁ” ወይም “የምኒልክ ቤተ መንግሥት” በ፲፰፻፺ ዓ/ም ላይ መታነጽ ሲጀምር ኢልግ በምሕንድስናው ሥራ ላይ ብዙ ተሳትፎ እንደነበረው ተጽፏል። በጊዜው ከተማዋን ትጎበኝ የነበረች፣ ወይዘሮ ፒስ የምትባል እንግሊዛዊት “(በቤተ መንግሥቱ) ብዙ (የስዊስ ባሕር ምስል እና የዊሊያም ቴል ጸሎት ቤት) ስዊሳዊ ተጽእኖዎች እንደተገነዘበች ጽፋለች ይላሉ ሪቻርድ ፓንክኸርስት [4] .


የቧንቧ ውሃ

ለማስተካከል
 
በዙሪክ በሚገኘው የኤንዘንቡህል መቃብር ላይ የኢልግ መቃብር

“አዲስ አበባ ከተማ ከተመሠረተችና የነዋሪዋ ብዛት እየጨመረ ከሄደ በኋላ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የውሃ እጥረት እያስጨገረ ሄደ።….ዓፄ ምኒልክም የውጭ አገር አማካሪዎቻቸው በፈረንጅ አገር ውሃ በቧንቧ እየተጠለፈ እንዴት አድርጎ ከቤት ድረስ እንደሚመጣ ካስረዷቸው በኋላ ያ ቧንቧ የተባለው ሥራ እንዲሠራ ዋና አማካሪያቸውንና መሐንዲሳቸውን ሙሴ ኢልግን አዘዙት።”

[5]

አቶ ጳውሎስ ስለዚህ ሥራ በሰፊው ሲያጫውቱን ሥራው በ፲፰፻፹፮ ዓ/ም እንደተጀመረና ለቧንቧ መግዣ ሰባት ሺ ማርያ ጠሬዛ ብር እንደሰጡ፤ ውሃው ከእንጦጦ ኪዳነ ምኅረት ቤተ ክርስቲያን አካባቢ ተጠልፎ ከቤተ መንግሥቱ እንደገባ ይነግሩናል። በዘመኑም

“እንዲህ ያለ ንጉሥ የንጉሥ ቂናጣ ውሃ በመዘውር ሰገነት አወጣ አሁን ከዚህ ወዲያ ምን ጥበብ ሊመጣ”

ተብሎ ተገጠመ ይባላል።

የቤተ መንግሥቱ የቧንቧ ውሃ ከተገጠመ በኋላ ምኒልክ አዲስ አበባ ከተማ በሙሉ እንዲዳረስ የውሃ ቧንቧ አስገዝተው ቧንቧው ከጂቡቲ እስከ ድሬ ዳዋ በምድር ባቡር፣ እስከ አዲስ አበባ ደግሞ በሰው ሸክም እንዲመጣ አዘዙ። ሆኖም እሳቸው ያሠሩት የቧንቧ ውሃ እምብዛም ሳይስፋፋ እስከ ጣልያን ወረራ ድረስ ቆየ። ሆኖም በዘመኑ የምኒልክ እንግዳ ሆኖ ኢትዮጵያን የጎበኘው አሜሪካዊው ዊሊያም ኤሊስ በምኒልክ አዳራሽ “ለኔ ክብር በተዘጋጀ ሰባት ሺ ሰዎች በተጋበዙበት ግብር ላይ፣ ጠጅ የሚባለውን መጠጥ በግብር ቤቱ ዙሪያውን በተገጠመ ቧንቧ የፈለገው ሰው እየተነሳ ከቧንቧው ይቀዳል።” ሲል ተቀድቷል።

የዘውድ አማካሪና የመንግሥት አደራዳሪ

ለማስተካከል
 
ዳግማዊ ምኒልክ በቢትወደድ ኢልግ የተነሡት ፎቶግራፍ

ዳግማዊ ምኒልክ ኢልግን የውጭ ዜጋም ቢሆን እንኳ ያከብሩትና ያምኑትም ነበር። ትውልድ አገሩ ስዊስ የቅኝ ግዛት ምኞት የሌላትና ትንሽ፣ የ ባሕር ወደብ የለሽ እና ከሌላ አውሮፓዊ ኃያል መንግሥታት ጋር ያልተሻረከች መሆኗም የኢልግን ታማኘት ሳያጠናክረው አይቀርም።

ኢልግም በበኩሉ “እንደአባቴ እወዳቸዋለሁ” ያላቸውን ምኒልክን ለሀያ ዓመታት በታማኝነት አገልግሏል።

ኢልግ ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር ወደ ትግራይ እና ዝዋይ የመሳሰሉ ቦታዎች ተጉዟል። እንዲሁም ወድጣልያን አገር ተጉዞ ከሚንስትሮቻቸው ጋር ከተወያየ በኋላ ሲመለስ ኢጣልያ ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ለመያዝ አሳብ እንዳላት ዳግማዊ ምኒልክን አስጠንቅቋቸዋል።

ከጦርነቱም በኋላ የአድዋ ድልም ያስከተለውን የድርድር (diplomacy) መስፋፋት እንዲያስተዳድር እና የአገሪቷን የውጭ ጉዳይ እንዲይስፋፋ ባለሙሉ ሥልጣን አደረጉት። ንጉሠ ነገሥቱ ኢልግን ሲሾሙት አብረውም የቢትወደድን ማዕርግ ሰጡት። በዚህ ሃላፊነት ሥራው ንጉሠ ነገሥቱን ወክሎ የውጭ አደራዳሪዎችን ያነጋግራል፣ ከኃያላን መንግሥታትም ጋር ይጻጻፋል። ሰውዬው ከአማርኛ ሌላ በጀርመንኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ ጣልያንኛና እንግሊዝኛ ቋንቋዎች የሠለጠነ ስለነበር ለዚህ ሥራ ብቃት የነበረው ሰው ነበር።

ከንጉሠ ነገሥቱም ሌላ ከብዙ ኢትዮጵያውያን መሳፍንት፣ መኳንንትና ሹማምንትም ጋር ይጻጻፍ እንደነበር ተዘግቧል። ከነኚህም መሃል እቴጌ ጣይቱ፣ የጎጃም ንጉሥ ተክለሃይማኖት፣ የሐረርጌው ገዥ ልዑል ራስ መኮንን፣ የጅማአባ ጅፋር እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ አቡነ ማቴዎስ ይገኙበታል።

አድዋ ድል በኋላ በኢጣልያ እና ኢትዮጵያ መሃል ጥቅምት ፲፮ ቀን ፲፰፻፹፱ የተፈረመውን የዕርቅ ውል፤ ከብሪታንያ እና ከፈረንሳይ መንግሥታት ጋር በመጋቢት ወር የተፈረሙትን ውሎች እንዲሁም ከጀርመን መንግሥት እና ከኦቶማን ንጉዛት መንግሥት ጋር የተፈረሙ ውሎችን በማዘጋጀትም ሆነ ማዋዋል ድረስ ኢልግ ሙሉ ተሳትፎ እንደነበረው ታሪክ ይዘግባል።

ወደመጨረሻው ጊዜ ንጉሠ ነገሥቱም ጤናቸው እየደከመ መጣ። በቤተ መንግሥቱም እሱን የሚመቀኙት ሰዎች በዙ። ከሁሉም ግን በየካቲት ወር ፲፰፻፺፯ ዓ/ም የጀርመን ልዑካንን የመራው ፍሬድሪክ ሮሰን የተባለው ጀርመናዊ በኢትዮጵያ መንግሥት እና በጀርመን መንግሥት መሃል ብዙ ውሎችን ከተፈራረመ በኋላ በቤተ መንግሥቱ የኢልግ ተሰሚነት እየመነመነ ሄዶ በ፲፱፻ ዓ/ም ሥራውን ለቆ ወደትውልድ አገሩ ተመለሰ።

ወደአገሩ ከተመለሰ በኋላ በእሪ በከንቱ ሠፈር ያለው መኖሪያ ቤቱ የመጀመሪያው ዘመናዊ ትምህርት ቤት (የአሁኑ ዳግማዊ ምኒልክ) በ፲፱፻፩ ዓ/ም ተከፈተበት። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን ትምህርት ቤቱ አሁን አራት ኪሎ ወዳለበት ሥፍራ ተዛወረ። አልፍሬድ ኢልግም በተወለደ በስድሳ ሁለት ዓመቱ የገና ዕለት (ታሕሣሥ ፳፱ ቀን) ፲፱፻፰ ዓ/ም ዙሪክ ላይ በልብ ምታት ምክንያት አረፈ።

ማመዛገቢያ

ለማስተካከል
  1. ^ (ፓንክኸርስት፣ 2008 እ.ኤ.አ)
  2. ^ (ጳውሎስ ኞኞ፤ ፲፱፻፹፬ ዓ/ም) ገጽ 267
  3. ^ (ጳውሎስ ኞኞ፤ ፲፱፻፹፬ ዓ/ም) ገጽ 268
  4. ^ (ፓንክኸርስት፣ 2008 እ.ኤ.አ)
  5. ^ (ጳውሎስ ኞኞ፤ ፲፱፻፹፬ ዓ/ም) ገጽ 297

ዋቢ ምንጮች

ለማስተካከል
  • (እንግሊዝኛ) Pankhurst, Richard: Foreign Involvement in Ethiopia’s Progress – Alfred Ilg , (February 5th, 2008)

http://lissanonline.com/blog/?p=126 Archived ጁን 10, 2008 at the Wayback Machine

  • (እንግሊዝኛ) Alfred Ilg’s Ethiopia around 1900” at the Ethnographic Museum

http://www.swissinfo.ch/eng/politics/Life_of_a_Swiss_who_engineered_change_in_Ethiopia.html?cid=3898064