በር:ፍልስፍና/የተመረጠ ጽሑፍ/38
ሬኔ ደካርት (René Descartes) (መጋቢት 31፣ 1596 – ሐምሌ 1650;) [1] ፈረንሳዊ ሳይንቲስት፣ ሂሳብ ተመራማሪ እና ፈላስፋ የነበረ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ የዘመናዊ ፍልስፍና አባት በመባል ይታወቃል። ሶስት ምክንያቶች ይጠቀሳሉ። የመጀመሪያዊ፣ ከጥንት ዘመን ጀምሮ ይሰራበት የነበረውን ምሁራዊ አሪስጣጣሊያውነትን ለመጀመሪያ ጊዜ ከአስተሳሰብ ዘዴው ያሰዎገደ ፈላስፋ በመሆኑ። ሁለተኛው ምክንያት የአዕምሮ እና አካል ሁለት እና እማይቀላቀሉ ነገሮች መሆን አስተሳሰብን ለመጀመሪያ ጊዜ ስላስተዋወቀ። ሶስተኛው ምክንያት ደግሞ፣ በአስተዎሎት እና ሙከራ ላይ የተመሰረተ አዲስ ዓይነት ሳይንስ ስላስተዋወቀ ነበር።
የካርቴዢያን ሰንጠረዥ ተብሎ በሚታወቀው አዲስ የጂዎሜትሪ እና አልጀብራ መቀየጫ ዘዴ በዚህ ሰው የተፈጠረ ሲሆን፣ በሂሳብ ጥናት ላይ ስር ነቀል ለውጥ አምጥቷል። ስለሆነም የትንተና ጂዎሜትሪ አባት በመባል ይታወቃል። ዴካርት፣ ከሒሳብ በተረፈ በሳይንስ ጥናቶች ላይ በመሳተፍ በዘመኑ የሳይንስ አብዮት በአውሮጳ እንዲፈነዳ ጉልህ አስተዋጾ አድርጓል።
ዴካርት በ17ኛው ክፍለ ዘመን ግዙፍ ስም ያገኘ ፈላስፋ ሲሆን በተለይ በአውሮጳ አህጉር በምክኑያዊነት (rationalism) ፍልስፍና ታዋቂነትን ያተረፈና ከሱ ፍልስፍና ተነሰተው በማስፋፋት እነ ባሩክ ስፒኖዛ እና ሌብኒትዝ ለምክኑያዊ ፍልስፍና ጥበብ ታላላቅ ድርሻ ሊያበረክቱ ችለዋል። በዚህ ተቃራኒ ግን ዳሳሻዊነት (empiricism) ፍልስፍናን ያራመዱ ፈላስፎች፣ ለምሳሌ ሎክ፣ ሆብስ፣ በርክሊ፣ ሩሶና ሁም የምክኑያዊነት ፍልስፍናውን አጥብቀው ተቃውመዋል። ከፍልስፍና ጽሁፎቹ ውስጥ አትኩረተ ህሊና በፍልስፍና መሰረት ላይ (Meditations on First Philosophy) የተባለው ጽሁፉ እስካሁን ዘመን ድረስ በዩንቨርስቲወች ውስጥ እንደ ዋና የትህርት ክፍል ይሰጣል።ደካርት ብዙ ጽሁፍ ቢያቀርብም፣ ባሁኑም ሆነ ቀደምት ክፍለ ዘመናት ስሙ ገኖ የሚታወቀው በአንዲት ጥቅስ ነው፣ እሱዋም «ስለማስብ፣ አለሁ»፣ በላቲኑ «Cogito ergo sum» ተብሎ ይታወቃል።
- ^ Colie, Rosalie L. (1957). Light and Enlightenment. Cambridge University Press. p. 58.