ጆን ኔፐር
ጆን ኔፐር (1542– 1610) – ስኮትላንዳዊ ሓሳቢ (ሒሳብ ተማሪ)፣ የተፈጥሮ ህግጋት ጥናት ተመራማሪ፣ ሥነ ፈለክ አጥኚ እና ኮኮብ ቆጣሪ ነበር።
ከሁሉ ስራው በታሪክ ቀደምት ስሙ እሚነሳው ሎጋሪዝምን በመፈልስፉ ነበር። ይህን የሂሳብ መሳሪያ የፈለስፈበት ዋና ምክንያት ከኮምፒውተር እና ካልኩሌተር ርቆ በሚገኘው ዘመን ቁጥሮችን ማባዛት፣ ጊዜ የሚወስድ፣ ለስህተትም የተጋለጠ መሆኑ ነበር። ሎጋሪዝም ማባዛትን ወደ መደመር በመቀየር አስቸጋሪውንና አሰልቺውን የማባዛት ስራ ለማቃለል ይረዳል።
ክፍልፋይ ቁጥርን ለማሳየት የምትጠቅመው ነጥብ በአውሮጳ ታዋቂ እንድትሆን ያደረገ ኔፐር ነበር። ከዚህ በተረፈ ኔፐር በሥነ መለኮት፣ ሥነ አልኬሚ ይጠቀሳል። በዘመኑ ደግሞ በጥንቆላ ና በማሟረት ስራ ይታማ ነበር።
ኔፐር በጥንቆላ ስለመታማቱ
ለማስተካከልኔፐር በነበረበት ዘመን ጥቁር ሸረሪት በትንሽ ሳጥን ደብቆ ይዞር ነበር ይባላል፤ ደግሞም ለመኖሪያው ቤቱ አድባር እንዲሆነው ጥቁር አውራ ዶሮ ያረባ እንደነበር ይጠቀሳል።
የቤቱ ሰራተኞች ዕቃ ሲሰርቁ ይሄው አውራዶሮ የትኛው አገልጋዩ እንደሰረቀው ለማወቅ ይረዳው ነበር ይባላል። ለምሳሌ ዕቃ ከቤቱ ሲጠፋ፣ አገልጋዮቹን አንድ ባንድ ከዶሮው ጋር እቤቱ ውስጥ እየቆለፈ ዶሮውን እንዲነኩ ከውጭ ሆኖ ያዛቸው ነበር። ከዚያ በኋላ አውራ ዶሮው የትኛው አገልጋይ ጥፋተኛ እንደሆነ ይነግረው ነበር ይባላል። ይሁንና ይህን ተግባር ሲከውን በፈሊጥ ነበር። ጥቁር አውራዶሮውን ከተጠርጣሪዎቹ ጋር ከመቆለፉ በፊት ጥላሸት ይለቀልቀው ነበር። ጥፋተኛ የሆኑት አገልጋዮች ዶሮው ይናገርብናል ብለው ስለሚፈሩ ዶሮውን አይነኩም፣ ጥፋት የሌለባቸው ባንጻሩ ይነኩታል። በኋላ ላይ ኔፐር እጃቸውን አንድ ባንድ ሲመረምር፣ እጃቸው ንጹህ የሆኑት ጥፋተኛ እንደሆኑ ያውቃል ማለት ነው።
ኔፐር ጠንቋይ እንደሆነ በአገሩ የተማበት ሌላ ምክንያትም አለ። አንድ ቀን ኔፐር ያሰጣውን ጥራጥሬ የጎረቤቱ እርግቦች እየለቀሙበት ይደርሳል። በዚህ የተናደደው ኔፐር ጎረቤቱን ጠርቶ እርግቦቹ እኔፐር ግቢ ሁለተኛ ከመጡ የእርሱ ንብረት እንደሚያደርጋቸው ያስጠነቅቀዋል። በሚቀጥለው ቀን እርግቦቹ ኔፐር ግቢ ውስጥ ታዩ፣ ሆኖም ግን በሚያስፈራ መልኩ ከቆይታ በኋላ ሁሉም ተዝለፍልፈው ወድቀው በኔፐር እየተለቀሙ አዘጋጀላቸው አቅማዳ ውስጥ ሲታጨቁ ታዩ። ኔፐር ባለፈው ቀን ጥራጥሬውን የሚያሰክር ብራንዲ ውስጥ ከዘፈዘፈ በኋላ ነበር ለስጦሽ የዘረጋው። ጠዋት ላይ እርግቦቹ አተሩን ሲለቅሙ እ እየተሳከሩ መብረር አቅቷቸው መሬት ላይ እየተንደፋደፉ ተፈነገሉ።