ክሪስቶፎር ኮሎምበስ
ክሪስቶፎር ኮሎምበስ በሰሜን ምዕራብ ጣሊያን፣ ጀኖዋ ከተማ በ1451 እ.ኤ.አ. የተወለደ ነጋዴና አገር አሳሽ ነበር። የአረፈውም በ1506 እ.ኤ.አ. በቫላዶሊድ ስፔን ነበር። ኮሎምበስ በ14 አመቱ የባህር ጉዞ እንደጀመረ ዜና መዋዕሉ ያትታል። ይሁንና በአሁኑ ዘመን የሚታወቀው የአሜሪካን አህጉር በ1492 እ.ኤ.አ. ስለደረሰበት ነው።
የኮሎምበስ የጉዞ አላማ ቻይናንና ህንድን ከአውሮጳ ጋር የሚያገናኝ መስመር በአትላንቲክ ውቅያኖስ ላይ በማግኘት የቅመማ ቅመም እና ወርቅ ንግድ ለስፔን ነገስታት በሚያመች መልኩ እንዲካሄድ ማድርግ ነበር። በጊዜው ይህ ሃሳብ እንግዳ ነበር ምክንያቱም ቻይናና ህንድ ከአውሮጳ በስተምስራቅ እንጂ በስተ ምዕራብ አይገኙምና።
ኮሎምበስ፣ መሬት ድቡልቡል እንደሆነች ያውቅ ነበር፤ በተረፈም ከማርኮ ፖሎ መጻሕፍት እንደተረዳ ከቻይና ምስራቅ ውቅያኖስ እንዳለ ያውቅ ነበር። ይህ ውቅያኖስ የአትላንቲክ ውቅያኖስ ነው ብሎ ኮሎምበስ በስህተት በመደምደም ነበር ጉዞ የጀመረው። ስለሆነም በአትላንቲክ ላይ ከተጓዘ በኋላ ያገኘውን የመጀመሪያውን ደረቅ መሬት ምስራቃዊ ህንድ በማለት ሰይሞታል፣ ይሄውም ባሃማስ ደሴት ሲሆን የአሜሪካ ክፍል ነው። ኮሎምበስ፣ ከዚህ በኋላ ወደ ባሃማስ፣ አሜሪካ አራት ጊዜ ጉዞ አድርጓል። በነዚህ ሁሉ ጊዜ የኮሎምበስ እምነት አዲስ አህጉር እንዳገኘ ሳይሆን ህንድን ከምዕራብ በኩል እንደደርሰበት ነበር።