ኪዙዋትና በጥንት (በኬጥያውያን መንግሥት ዘመን) በደቡብ-ምሥራቅ አናቶሊያ የተገኘ አገር ነው። ከ1491 እስከ 1428 ዓክልበ. ድረስ ያህል ነጻ መንግሥት ነበር። በኋላ ይህ ኪልቅያ የተባለው አውራጃ ሆነ።

አናቶሊያ በኬጥያውያን ዘመን

በሐገሩ ስሜን፣ ብር የተገኙበት ታውሮስ ተራሮች እና ዋና ከተማ ኩማኒ ተገኙ። በደቡብም፣ በሜድትራኒያን ባሕር ዳር ባለው ሜዳ፣ ወደቡ ጠርሴስና ትልቁ ከተማ አዳኒያ ይገኙ ነበር። የአካድ ንጉሥ ታላቁ ሳርጎን በነዚህ ተራሮች እንደ ዘመተ ጽፏል። እንዲሁም በአፈ ታሪክ አገሩ በሚሪና፣ በሞፕሱስ ወዘተ. ተይዞ ነበር። አሦራውያን የ«ካሩም» ንግድ ማዕከሎች በሐቲ ከተሞች በመሠረቱት ዘመን፣ መንገዳቸው በኪዙዋትና በኩል እንዳለፈ ይመስላል።

ቢያንስ ከኬጥያውያን ንጉሥ 1 ላባርና ዘመን (1582-59 ዓክልበ ግ.) አዳኒያ (ኪዙዋትና) የኬጥያውያን ግዛት እንደ ሆነ ይመስላል። ሕዝቡም እንደ ምዕራቡ አገር አርዛዋ ሕዝብ የሉዊኛ ተናጋሪዎች ስለ ነበሩ፣ በኬጥያውያን ዘንድ ሁለቱ አገራት አብረው «ሉዊያ» ይባሉ ነበር። ሉዊኛ እንደ ኬጥኛ ተመሳሳይ ሕንዳዊ-አውሮፓዊ (አናቶላዊ ቋንቋዎች ቅርንጫፍ) አባል ነበረ።

በ1491 ዓክልበ. ኪዙዋትና ከኬጥያውያን መንግሥት ነጻ ወጣ። የኪዙዋትና ነገሥታት ከሐቲ ጋራ የወዳጅነት ስምምነቶች ይዋዋሉ ነበር። በ1465 ዓክልበ.ግ. ግን የኪዙዋትና ንጉሥ ፒሊያአላላኽም ንጉስ ኢድሪሚ ጋር ስምምነት ተዋዋለ፣ ኢድሪሚስም የሚታኒ ተገዥ ሆነ። ከዚያም በኋላ የሚታኒ እና ሑራውያን ተጽእኖ በኪዙዋትና ይበዛ፣ የሐቲም ይቀነስ ነበር። የኪዙዋትና መጨረሻ ንጉሥ ሹናሹራ ሲባል እንደ ሚታኒ ነገሥታት በመምሰል ከሕንዳዊ-ኢራናዊ (ከአናቶላዊ የተለየ) ቅርጫፍ የሆነ ስም እንዳለው ይታስባል። በመጨረሻ በ1428 ዓክልበ. ያሕል ሐቲና ሚታኒ ጦርነት ሲያደርጉ፣ የሐቲ ንጉሥ 1 ቱድሐሊያ ወርሮ እንደገና ኪዙዋትናን ተገዥ ክፍላገር አደረገው።

የኬጥያውያን መንግሥት በ1186 ዓክልበ. አካባቢ በወደቀበት ወቅት፣ ወራሪዎቹ በኪዙዋትና ሥፍራ አዳዲስ ነጻ መንግሥታት ፦ ታባልቁዌ፣ እና ሒላኩ - ይቋቁሙ ነበር። ከነዚህ «ሒላኩ» የተባለው ወደፊት የ«ኪልቅያ» መጠሪያ መነሻ ሆነ።

የኪዙዋትና ነገሥታት ለማስተካከል

  • ኢሽፑታሕሹ የፓሪያዋትሪ ልጅ - ከሐቲ ንጉሥ ተለፒኑ (1488-83 ዓክልበ.) ጋር ስምምነት ተዋወለ።
  • ኤሄያ - ከሐቲ ንጉሥ ታሑርዋይሊ (1483 ዓክልበ.) ጋር ስምምነት ተዋወለ።
  • ፓዳሽቲሹ - ከሐቲ ንጉሥ 2 ሐንቲሊ (1478-73 ዓክልበ.) ጋር ስምምነት ተዋወለ።
  • ፒሊያ - ከሐቲ ንጉሥ 2 ዚዳንታ ጋር በ1473 ዓክልበ.፣ በኋላ ከሙኪሽ ንጉሥ ኢድሪሚ ጋር በ1465 ዓክልበ. ስምምነት ተዋወለል፡
  • ታልዙ
  • ሹናሹራ - ለሐቲ ንጉሥ 1 ቱድሐሊያ በ1428 ዓክልበ. ተገዥ ሆነ።