ኬጥኛ
ኬጥኛ (ኬጥኛ፦ 𒉈𒅆𒇷 /ነሺሊ/) በጥንታዊ አናቶሊያ ኬጥያውያን መንግሥት ከ1900-1200 ዓክልበ ግድም የተነገረ የሕንዳዊ-አውሮፓዊ ቤተሠብ አባል ነበረ።
እስከምናውቀው ድረስ ኬጥኛ ከሁሉ አስቀድሞ በጽሕፈት የተመዘገበው ሕንዳዊ-አውሮፓዊ አባል ነው። የተጻፈው ከአካድኛ በተወሰደው በኩኔይፎርም ጽሕፈት ዘዴ ነበር።
መጀመርያው የምናውቀው ናሙና የካነሽ ንጉሥ አኒታ አዋጅ (1650 ዓክልበ. ግ.) ነው። ሆኖም ከዚህ በፊት ከ1880 ዓክልበ. ጀምሮ በተጻፉት በአካድኛ ካሩም ካነሽ መዝገቦች መካከል ከተገኙት የነጋዴዎች ስሞች፣ በርካታ የኬጥኛ ስሞች ይመስላሉ።[1] ከዚያም በፊት በኤብላ ጽላቶች (2100 ዓክልበ. ግ.) ከተዘረዘሩት ከአርሚ ከተማ (ሐለብ?) ነጋደዎች ብዛት፣ ሃያ ያሕል የአርሚ ነጋዴዎች የኬጥኛ ስሞች እንዳሏቸው ይመስላል።[2]
ይህ ቋንቋ ከ1900 ዓክልበ. በፊት በሐቲ አገር የሠፈሩት የሓታውያን ቋንቋ ወይም ሐትኛ ምንም ዝምድና አልነበረውም፤ ነገር ግን እነዚህ ኬጥያውያን የተባሉት ከሐቲ ውጭ የወረሩ ነበር። አገሩም «ሐቲ» ከዕብራይስጥ ስም «ሔቲ» (ኬጢ ወይም ኬጥያውያን (መጽሐፍ ቅዱስ)) ጋር ተመሳሳይነት ስላለው፣ እነዚህ ሰዎች አሁን በእንግሊዝኛ «ሂታይት» (ኬጥያውያን) ይባላሉ፤ ቋንቋችውም «ኬጥኛ» ሲባል፣ እንዲያውም በመጀመርያው በካነሽ ከተማ ስለተገኘ በራሳቸው ዘንድ ስያሜው «ነሺሊ» (ማለት ካነሽኛ) ተባለ።