2 ዚዳንታ ምናልባት ከ1473 እስከ 1458 ዓክልበ ድረስ ዓክልበ. አካባቢ ከአጎቱ 2 ሐንቲሊ በኋላ በሐቱሳሽ (በሐቲ አገር ወይም የኬጥያውያን መንግሥት) የገዛ ንጉሥ ነበር።

አባቱ ሐሹዊሊ የቀዳሚው የሐንቲሊ ወንድምና የንጉሣዊ ዘበኞች አለቃ እንደ ነበር ይታመናል። የዚዳንታ ንግሥት ያያ ተባለች። የዚዳንታም ኩኔይፎርም ማኅተም ይታወቃል።

በዚህ ዘመን እንደገና የወዳጅነትና ስምምነት ውል ከጎረቤቱ አገር ከኪዙዋትና ጋራ ከንጉሡም ፒሊያ ጋር ተዋዋለ። ይህ ፒሊያ ደግሞ ከጥቂት ዓመት በኋላ ከአላላኽ (ሙኪሽ አገር) ገዢ ከኢድሪሚ ጋራ ውልን እንደ ተዋወለ ይታወቃል። በዚያው ውል ኢድሪሚ የሚታኒ ገዥ ባራታርና ሊሆን ነበር፣ ኪዙዋትናም ያንጊዜ ከሐቲ ወዳጅነት ወደ ሚታኒ ወዳጅነት አለፈ። ስለ ሆነም ሐቲ ደግሞ ድካም ስለ ሆነች ይህ ኢድሪሚ ከዚያ በሐቲ ላይ ሊዘምት ቻለ። የኢድሪሚ ጽሑፍ እንዳለ፣

«ጭፍሮች ወስጄ በሐቲ አገር ላይ ተነሣሁ፣ ከአምባዎቻቸውም ሰባት አጠፋሁ፤ አምባዎቹም እነዚህ ናቸው፦ ፓሻሔ፣ ዳማሩት-ርዒ፣ ሑላሓን፣ ዚሴ፣ ዬ፣ ኡሉዚና፣ እና ዛሩና ናቸው። ሐቲ አገር በኔ ላይ አልገሠገሠም፤ እንደ ልበ ማድረግ ቻልኩ። ምርከኞች ወሰድኩባቸው፣ ሃብታቸውን ንብረታቸውን፣ ርስታቸውንም ዘረፍኩ፣ ለጭፍሮቼ፣ ለቀጥረኞቼ፣ ለወንድሞቼና ለጓደኞቼ አከፋፈልኩት። እኔም እንደነሱ ድርሻዬን ወሰድኩ። ከዚያ ወደ ሙኪሽ አገር ተመልሼ ወደ ከተማዬ አላላኽ በክብር ገባሁ።» (ANET 557f.)

ይኸው የሙኪሽ ወረራ በሐቲ አምባዎች ላይ የተከሠተው በ፪ ዚዳንታ ዘመን እንደ ሆነ ይታስባል።

ቀዳሚው
2 ሐንቲሊ
ሐቲ ንጉሥ
1473-1458 ዓክልበ. ግድም
ተከታይ
2 ሑዚያ