ታሑርዋይሊ
ታሑርዋይሊ በ1483 ዓክልበ. አካባቢ ከተለፒኑ በኋላ በሐቱሳሽ (በሐቲ አገር ወይም የኬጥያውያን መንግሥት) የገዛ ንጉሥ እንደ ነበር ይታስባል። (ሆኖም ታሑርዋይሊ ከአሉዋምናና ከ2 ሐንቲሊ ቀጥሎ እንደ ነገሠ የሚል አስተሳሰብ ደግሞ ብዙ ይታያል።)
ተለፒኑ በጻፈው የተለፒኑ ዐዋጅ በተባለው ሰነድ እንደምንረዳ፣ በንጉሥ አሙና ጊዜ ታሑርዋይሊ «የወርቃማው ጦር ሰውዬ» ሲባል፣ አባቱም ዙሩ «የንጉሣዊ ዘበኞች አለቃ» ሲሆን፣ ሁለቱ በአሙና ሁለት ወራሽ ልጆች በቲቲያና ሐንቲሊ ላይ ሤራ ገብተው አስገድለዋቸው ነበር። ይህም ዙሩ የአሙና ወንድምና የ1 ዚዳንታ ልጅ፣ እናቱም የ1 ሐንቲሊ ልጅ እንደ ነበሩ ይታስባል።
ተለፒኑም ንጉሥ ከሆነ በኋላ፣ ሸንጎው ወይም ፓንኩሽ በዚህ ታሑርዋይሊ ላይ መሞት ቢፈርድም፣ ተለፒኑ ይቅር ብሎ ወደ ግብርና አስገደደው ይላል።
በተለፒኑም አዋጅ ዘንድ፣ ወንድ ልዑል አልጋ ወራሽ ባይኖር ኖሮ የትልቅዋ ሴት ልጅ ባለቤት ዘውዱን ወርሶ እሱ ንጉሥ ይሁን የሚል ነው። እንዲያውም የተለፒኑ ወንድ ልጅ ልዑል አሙና አርፎ ስለዚህ የሴት ልጁ የሐራፕሺሊ (ወይም ሐረፕሼኪ?) ባል አሉዋምና የተለፒኑ ሕጋዊ ወራሽ ይሆን ነበር። ሆኖም ከዚህ አዋጅ በኋላ አሉዋምናና ሐረፕሼኪ በአባትዋ በተለፒኑ መንግሥት ላይ አምጸው ወደ ማሊታሽኩር እንደ ተሳደዱ ይመስላል። ስለዚህ የታሑርዋይሊ ዘመን የቀደመው ይሆናል።
ታሑርዋይሊ ደግሞ እንደ ቀዳሚው ተለፒኑ ከኪዙዋትና ታላቅ ንጉሥ ኤሄያ ጋራ ስምምነት እንደ ተዋወለ ይታውቃል።
በኬጥኛ ኩኔይፎርም «ታሑርዋይሊ ታላቅ ንጉሥ የሐቲ ንጉሥ» የሚሉ ማኅተሞቹ ለሥነ ቅርስ ታውቀዋል። ስንት አመት እንደ ነገሠ በእርግጡ አይታወቅም፣ ብዙ ሳያልፉ ግን አሉዋምና ዙፋኑን እንዳገኘው ይሆናል።
ቀዳሚው ተለፒኑ |
የሐቲ ንጉሥ 1483 ዓክልበ. ግድም |
ተከታይ አሉዋምና |