ቲራስ
ቲራስ በኦሪት ዘፍጥረት 10 መሠረት (ወይም ቴራስ እንደ ዜና መዋዕል፤ ቴሬስ በመጽሐፈ ኩፋሌ) የያፌት ታናሽ ወንድ ልጅ ነበረ። በዕብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ቲራስ ምንም ተጨማሪ መረጃ ባይጠቀስም፣ በኩፋሌ ዘንድ ምድር በተከፋፈለበት ወቅት የቲራስ ርስት በውቅያኖስ ውስጥ 4 ታላላቅ ደሴቶች ሆነ።
የአይሁድ ታሪክ ጸሐፊ ዮሴፉስ (1ኛው ክፍለ ዘመን) በጻፈው ታሪክ ዘንድ፣ ቲራስ የ«ጢራስያውያን» አባት ሆነ። እነዚህ በኋላ ስማቸው ጥራክያውያን እንደ ተባለ ይነግረናል። ጥራክውያንም በጥንታዊ ዘመን «ነበልባል ቀለም» (ቀይ ወይም ወርቃማ ጸጉር) ያለው ብሔር መሆናችውን ግሪኩ ጸሐፊ ዜኖፋኔስ (6ኛው ክፍለ ዘመን ዓክልበ.) መሰክሯል። በጥንታዊ ዘመን «ቲራስ» የድኒስተር ወንዝ ስም ነበር። በዚህም ወንዝ አፍ የግሪክ ቅኝ አገር ቱራስ ይባል ነበር፤ በዙሪያውም ቲራጌታያውያን ይኖሩ ነበር። ከጥራክያውያንም ክፍሎች አንዱ ጌታያውያን ተብለው ይታወቁ ነበር (ሄሮዶቱስ 4.93፣ 5.3 እና ሌሎች ጸሐፍት)። በግሪኮች ዘንድ፣ የጥራክያውያን አባት ስም ጥራክስ ነበረ።
በአንዳንድ ሊቃውንት ዘንድ፣ ይህ «ቲራስ ያፌት» በዘሮቹ መካከል እንደ ጣኦቱ ስም ቶር (በጥንቱ ጀርመናውያን እምነት የነጐድጓድ አምላክ) ይታወስ ነበር። የግሪክ ባለቅኔ ሆሜር (9ኛው ክፍለ ዘመን ዓክልበ.) እንደ ጠቀሰው፣ Θουρος ጦውሮስ «የጥራክያውያን አሬስ (ማርስ)» ስም ነበር። በጥንታዊ ኖርስ መዝገቦች ዘንድ፣ ቶር የጥንት አለቃቸውና ወላጃቸው ሲሆን፣ ከጥራክያ እንደ ተነሣ ይላሉ።
በ1830 ዓ.ም. የጀርመን ሊቅ ዮሐን ክርስቲያን ፍሪድሪክ ቱክ እንደ ጻፈው[1] የቲራስ መታወቂያ በሮማውያን «ኤትሩስኪ» የተባለው ሕዝብ ይሆናል። በሄሮዶቱስ (1.94) እና በሌሎቹ ግሪክ ታሪኮች መሠረት፣ ይህ ሕዝብ በቀድሞ (ከ800 ዓክልበ. በፊት) «ቱርሴኖይ» ተብለው ከልድያ ወደ ጣልያን ፈለሱ። አንዳንድ ሊቃውንት እንደሚሉት፣ የ«ቲራስ»ና «ቱርሴኖይ» መታወቂያ በትሮአስ ከተማ ስም ይታያል፤ ይህም ጥንታዊ ሥፍራ በሆሜር ቅኔ ዝነኛ ሆኗል። በኬጢያውያን መንግሥት መዝገቦችም፣ ከተማው «ተሩዊሳ» በመባል ይታወቃል። በተጨማሪ፣ በምሥር ጥንታዊ መዝገቦች «የባሕር ሕዝቦች» ከተባሉት ነገዶች መካከል፣ አንዱ «ተረሽ» (1220 ዓክልበ.) ወይም «ቱርሻ» (1180 ዓክልበ.) ሲሆን፤ ይሄው መርከበኛ ብሔር ከቲራስ፣ ቱርሴኖይና ተሩዊሳ ጋ ግንኙነት እንዳለው የሚል አሳብ አለ።[2][3]
በአይሁድ ረቢዎች ተልሙድ ዘንድ ግን፣ ቲራስ የፋርስ አገር አባት ነው። በመካከለኛው ዘመን በተጻፉ የአይሁድ መጻሕፍት ዘንድ፣ ከቲራስ የተወለዱት የአንግሎ-ሳክሶን ሕዝቦች ናቸው። ሌሎች የአይሁድ መጻሕፍት ልዩ የሆኑ ትውልዶች ጨምረዋል። በሐሣዊ ፊሎ (67 ዓ.ም. ገደማ) ቅጂዎች፣ የቲራስ ልጆች «ማአክ፣ ታበል፣ ባላና ሳምፕላሜአክ እና ኤላዝ» ናቸው። በሠፈር ሃያሻር ግን፣ ልጆቹ «ቤኒብ፣ ጌራ፣ ሉፒርዮን እና ጊላክ» ይባላሉ።
የፋርስ ታሪክ ጸሐፊ አል-ታባሪ (910 ዓ.ም. ገደማ) እንደሚለው፣ የቲራስ ወንድ ልጅ ባታዊል ሲሆን፣ የባታዊልም ሴት ልጆች ቃርናቢል፣ ባኅትና አርሳል የየኩሽ፣ ፉጥና ከነዓን ሚስቶች ሆኑ።