1 ሐንቲሊ ክ1507-1491 ዓክልበ. አካባቢ ከንግሥቱ ሐራፕሺሊ ወንድም 1 ሙርሲሊ በኋላ በሐቱሳሽ (በሐቲ አገር ወይም የኬጥያውያን መንግሥት) የገዛ ንጉሥ ነበር።

የሐንቲሊና የባለቤቱ የሐራፕሺሊ ሴት ልጅ ደግሞ የዚዳንታ ሚስት ነበረች። ንጉሡ ሙርሲሊ የማርዱክን ጣዖት ይዞ ከባቢሎን ዘመቻው በተመለሰበት ጊዜ፣ «የዋንጫ ተሽካሚ» ሐንቲሊና የልጁ ባል ዚዳንታ በሤራ ገብተው ሙርሲሊን ገደሉና ሐንቲሊ ያንጊዜ የኬጥያውያን ንጉሥ ሆነ።

በኋላ ንጉሡ ቴሌፒኑ በጻፈው የቴሌፒኑ ዐዋጅ በተባለው ሰነድ የሐንቲሊ ዘመን ይተረካል፤ ሐንቲሊ ንጉሡን ሙርሲሊን በሤራ ስለ ገደለው አሁን እሱ ንጉሡ ለራሱ ሕይወት ፈራና ጸጸተ ይላል። ከዚያም፦

«የትም ቢሄድ፣ ሕዝቡ <...> ከአሽታታ፣ [ሹክዚ]ያ፣ ሑርፓና፣ ከርከሚሽ ከተሞች <...> ጭፍሮችን ያሠልፉ ጀመር <...>
ሐንቲሊም ቴጋራማ ከተማን በደረሰ ጊዜ፣ ምን አደረግኩ? ለምን የዚዳንታን ቃል ሰማሁት? ይል ነበር። ንጉሥም እንደ ሆነ አማልክት ስለ ሙርሲሊ ደም ቂም ፈለጉ ።
<...> የሑራውያንም ወታደሮች እንደ ዱር ቀበሮች አባረርዋቸው። ሑራውያን ጠላቶች ወደ ሐቲ መጥተው <...> በአገር ቤት ተዛወሩ <...>
<...> [አንድ መስመር በሙሉ ጠፍቷል]
<...> የሹክዚያ ከተማ ንግሥትም <...> ንግሥትዋ እያረፉ <...> ኢላሊዩማ በምስጢር ሎሌዎችን ልኮ <...> የሹክዚያ ንግሥት ትሙት! ብሎ ጮኸ። እንግዲህ ያዝዋትና ከልጆችዋ ጋራ ገደሉዋት።
ሐንቲሊ ስለ ሹክዚያ ንግሥትና ልጆቿ ጉዳይ ማን ገደላቸው? ብሎ ሲጠይቅ፣ የሎሌዎች አለቃ ቃሉን አመጣ። ቤተሠብዋን ሰብስበው ወደ ቴጋራማ ዱር አባረሩዋቸውና ሞቱ።
ሐንቲሊ ባረጀ ጊዜ እሱም አምላክ ሊሆን ሲል፣ ዚዳንታ የሐንቲሊን ልጅ ፒሼኒን ከነልጆቹም ከነሎሌዎቹም ገደላቸው።
ዚዳንታም ንጉሥ ሆነ። አማልክት ስለ ፒሼኒ ደም ቂም ፈለጉ። አማልክት የገዛ ልጁ አሙና እንደ ጠላቱ አድርገው እሱም አባቱን ዚዳንታን ገደለ።»

ከርከሚሽ በሶርያ ሲሆን ከዚያ ዙሪያ ሑራውያን ወይም ሚታኒ ጋር እንደ ታገለ ይመስላል። ኪዙዋትና (የበኋላ ኪልቅያ) የኬጥያውያን ክፍላገር ሆና እንደ ቀረች ይታመናል።

በኋላ በ4 ቱድሐሊያ (1249-1217 ዓክልበ.) ጽላት ዘንድ፣ የካስካውያን ብሔር በስሜኑ በጥቁር ባሕር ላይ መጀመርያ የታዩ በዚህ 1 ሐንቲሊ ዘመን የተቀደሠውን ከተማ ኔሪክን ሲያጥፉ ነበር። ይችም ከተማ እስከ 1275 ዓክልበ. ድረስ ዳግመኛ አልተሠራችም ይላል።

የሐንቲሊን ወራሾች ገድሎ ዚዳንታ በሐቲ ዙፋን ላይ ተከተለው። በአጭር ጊዜ ውስጥ ዚዳንታ በገዛ ልጁ አሙና ተገደለ፤ አሙናም የኬጥያውያን ንጉሥ ሆነ። የዚዳንታ ሚስት የሐንቲሊ ሴት ልጅ ስለ ሆነች ይህ አሙና የሐንቲሊ ልጅ ልጅ እንደ ነበር ይታስባል።

ቀዳሚው
1 ሙርሲሊ
ሐቲ ንጉሥ
1507-1491 ዓክልበ. ግድም
ተከታይ
1 ዚዳንታ