በለስ
በለስ (ሮማይስጥ፦ Ficus) ቅጠሉ ሰፋፊ፣ ነጭ ፈሳሽ ያለው፣ ፍሬው የሚበላ የእፅዋት አስተኔ ነው። ፍሬውም ደግሞ በለስ ወይም ዕጸ በለስ ይባላል።
በበለሱ ቤተሠብ ውስጥ ብዙ ልዩ ልዩ የዛፍ አይነቶች አሉ፤ ከነዚህም ውስጥ፦
- ተራ በለስ F. carica ከጥንት ጀምሮ ስለ ፍሬው በእርሻ ወይም በጓሮ ተተክሏል። ፍሬውም ለጤንነት እጅግ መልካም ነው።
- የቆላ በለስ F. palmata
- ሾላ F sycomorus -
- ዋርካ (ወይም ወርካ) F. vasta - በብዙ ቅርንጫፎች በጣም ትልቅ የሆነ የበለስ አይነት ነው። ፍሬው ከሾላ ፍሬ ያንሳል። ይህ ፍሬ ከበሰለና ከደረቀ በኋላ ይበላል።
- ባኒያን F. benghalensis
- ችባሓ F. thonningii
- የጎማ ዛፍ F. elastica
የበለስ 'ፍሬ' በዕውኑ ወደ ውስጥ ያበበ አበባ ነው። ይህ ክስተት ለሥነ ሕይወት ጥናት በጣም የሚያስገርም ድንቅ ነው። እነኚህ አበቦች ፅጌ ብናኝን (የአበባ ወንዴ ዘር) የሚያገኙበት ዘዴ በልዩ ብናኝ አርካቢ ጥቃቅን ተርብ አማካኝነት ነው። ይህች የበለስ ተርብ ወደ ፍሬው ውስጥ ገብታ በመኖር እንቁላሏን በዚያ ትጥላለች። አብዛኞቹ በለስ አይነቶች አለበለዚያ ብናኝ ዘርን ሊያገኙ አይችሉም። ተርቢቱ ዕንቁላሏን ጥላ በበለሱ ውስጥ ከሞተች በኋላ፣ በፍሬው ያለው ኤንዛይም በድኑን ፈጽሞ ይበላል። የዛፉ ጾታ አንስት ከሆነ፣ የተርቢቱ እንቁላል አይፈለፈለም፣ ፍሬውም በሰው ይበላል። የዛፉ ጾታ ግን ፍናፍንት ሲሆን፣ ዕንቁላሎቿ ይፈለፈላሉ፤ ፍሬው ለፍየል ሊሰጥ ይችላል እንጂ በሰዎች አይበላም። ተርቦች ከፍናፍንት ዛፍ ተወልደው ሴት ተርቦቹ የሴት ዛፍ እንዲያገኙ ገበሬው የፍናፍንት ዛፍ ቅጠል ከአንስት ዛፍ ቅርንጫፍ ይሰቅላል። አንዳንድ የበለስ አይነት ያለ ተርብ ያፈራል፤ ነገር ግን የነዚህ ፍሬዎች መካን ይሆናሉ። ዳሩ ግን በለሶች በእፃዊ ተዋልዶ ለማብዛት በተለይ ስለሚመቹ፣ ይህ ዘዴ የተለመደና ፈጣን የመራቦ ዘዴ ነው።
በእስልምና፣ በሕንዱ፣ በቡድሂስትና በጃይን እምነቶች፣ በለሶች የተቀደሱ ዛፎች ሆነው ይቆጠራሉ። በክርስትናም በአይሁድም በኩል በለስ ወይም ሾላ በብሉይ ኪዳን ብዙ ጊዜ ይጠቀሳል። ለምሳሌ በአንዳንድ ሥፍራ በትንቢት፣ በእግዚአብሔር መንግሥት ሰው ሁሉ በራሱ ወይንና በለስ ሥር እንደሚቀመጥ ይላል። በተጨማሪ በኦሪት ዘፍጥረት 3፡7 ዘንድ አዳምና ሕይዋን ከበለስ ቅጠል ልብስ ሠሩላቸው። ከዚህ የተነሣ በተለይ በተዋሕዶ ቤ.ክ. የበለስ ፍሬ ወይም እፀ-በለስ እግዚአብሔር እንዳትበሉት ብሎ ያዘዛቸው ፍሬ መሆኑን በመገመት ይታመናል። ሆኖም በሌላ አስተሳስብ የተከለከለው ፍሬ መታወቂያ ወይን ወይም ቱፋህ ነበር። መታወቂያው በመጽሐፉ እርግጠኛ ስላልሆነ፣ በእርግጥ በለስ ማለቱ ነበር ልንል አንችልም። በአዲስ ኪዳን ውስጥ ደግሞ በለስ በክርስቶስ ምሳሌዎች ብዙ ጊዜ ይጠቀሳል፤ በማርቆስ ወንጌል ምዕራፍ 11 መሠረት ኢየሱስም አንዲቱን በለስ ረግሞ ነበር።
-
ተራ በለስ
-
የተራ በለስ ፍሬ
-
የተረ በለስ ፍሬ ውስጥ
-
የበለስ ተርብ አይነት