ሽፈራው
ሽፈራው (Moringa stenopetala) ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኝ ተክል ነው።
የሞሪንጋ/ሽፈራው ዛፍ ምንነትና ጠቀሜታው
ለማስተካከልየሞሪንጋ ዛፍ በኢትዮጵያ በተለምዶ ሽፈራው በሚል የሚታወቅ ሲሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ13 በላይ ዝርያዎች ያሉትና በሁለገብ ጠቀሜታቸው ከሚታወቁት ዛፎች መካከል አንዱ ነው። በአለም ላይ ካሉት የሞሪንጋ ዛፍ ዝርያዎች ውስጥ ሰባት የሚሆኑት በምስራቅ አፍሪካ በተለይ ደግሞ በኢትዮጵያ፣ በኬንያ፣ በጅቡቲና በሶማሊያ አካባቢዎች ይገኛሉ። ሽፈራው ከሚለው ስያሜ ባሻገር የጎመን ዛፍ ወይም የአፍሪካ ሞሪንጋ- Moringa stenopetala) ተብሎ የሚጠራው ዛፍ በኢትዮጵያ በአብዛኛው በዝቅተኛው የስምጥ ሸለቆ ሀይቅ በደረቃማ እና ከፊል-ደረቃማ በሆኑት የአየር ንብረት ክልሎች ማለትም በ ጌዴኦ፤ ሲዳማ፤ ኮንሶ፤ ኦሞ (ወላይታ) ፤ ምዕራብ ጋሞጎፋ፤ ጊዶሎ፣ ቡርጂ፣ ሴይሴና በመሌ ይገኛል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በወሎ፤ ሸዋ፤ ሀረርጌና ሲዳማ አካባቢዎች የግብርና ልማትን ከአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች ጋር በማቀናጀት ለሰርቶ ማሳያ እየተተከለ መሆኑን ዘገባዎች ይጠቁማሉ። ሞሪንጋ በፎንተኒና (ወሎ)፣ ዴራ (አርሲ) እንዲሁም በዝዋይ መስኖ እርሻ ለነፋስ መከላከያ አጥር በመሆን ጥቅም ላይ እየዋለ ነው። ከዚህ በተጨማሪ በኢትዮጵያ ደቡባዊው የስምጥ ሸለቆ ክፍል በተለይም በከፋ፣ ጋሞ ጎፋና ሲዳማ አካባቢዎች አንፃራዊ በሆነ መልኩ በተሻለ ስርጭት ይገኛል።
ሞሪንጋ በምድር ወገብ ፈጣን ዕድገት አለው። ይህ ዛፍ ከሚሰጣቸው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች መካከል ለምግብነት፣ ለመድሃኒትነት፣ ለውሃ ማጣሪያነት፣ ለእንስሳት መኖነትና ለንብ ቀሰምነት ዋና ዋናዎቹ ናቸው። በደቡብ ክልል የኮንሶ ብሔረሰቦች ለምግብ አገልግሎት ከመጠቀማቸው ባለፈ ከሌሎች ሰብሎች ጋር አሰባጥረው በመትከል ቀጣይነት ባለው የአመራረት ዘይቤ የመሬት ምርትና ምርታማነት እዲጨምር በማድረግ ለበርካታ ዓመታት ሲጠቀሙበት ቆይተዋል። ይህ ዛፍ ቅጠሉ በምግብ ንጥረ ነገር ይዘታቸው ከሚታወቁት ሰብሎች ማለትም ከካሮት (ቫይታሚን ኤ)፣ ከአተር (ፕሮቲን)፣ ከብርቱካን (ቫይታሚን ሲ)፣ ከወተት (ካልሽየም) እና ከቆስጣ (ብረት) ንጥረ ነገሮች ይዘት እንዳሚበልጥ ጥናቶች ያሳያሉ።
በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ዝናብ አጠር በሆኑት በዋግኽምራ ዞን (አበርገሌ) እና በሰሜን ሸዋ (እንሳሮ ወረዳ) በተሰሩ የምርምር ስራዎች ሞሪንጋ በአካባቢው መላመድ የሚችልና ውጤታማ ዛፍ መሆኑ ተረጋግጧል፤ በመሆኑም በተመሳሳይ ስነምህዳሮች (አካባቢዎች) እንዲስፋፋ ማድረግ ተገቢ ነው። የተገኘው የምርምር ሙከራ ውጤት እንደሚያመለክተው የሞሪንጋ ዛፍ በበጋ ወራት ቅጠሉን በመጠኑ የሚያረገፍ ነገር ግን ቅርንጫፉ ከተቆረጠ /ከተከረከመ/ ቅጠሉን ከማርገፍ የሚቆጠብና ብዙ ቅጠል የሚያቆጠቁጥ መሆኑ ታይቷል። ዛፉ ደረቃማና ከፊል ደረቃማ በሆኑ አካባቢዎች የሚበቅልና የሚያድግ በመሆኑ የአካባቢ ስነ-ምህዳርን ለመጠበቅና ለምግብነት አገልግሎት ስለሚውል የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ርብርብ አስተዋጽዖው የጎላ ነው። ስለዚህ ከባቢያዊ ችግር ባለባቸውና ድርቅ በሚያጠቃቸው አካባቢዎች ቢለማና መስፋፋት ቢችል ለምግብ ዋስትና ከሚያደርገው አስተዋፅዖ በተጨማሪ ለአካባቢ ጥበቃ ስራ ተመራጭ ዛፍ ያደርገዋል።
ተስማሚ አካባቢዎች
ለማስተካከልየሞሪንጋ ዛፍ ከደረቅ እስከ መጠነኛ እርጥበታማ ስነ-ምህዳሮችና የተለያዩ የማምረት አቅም ባላቸው የአፈር አይነቶች መብቅልና ማደግ ይችላል። ዛፉ ደረቃማ፣ ከፊል ደረቃማ እና ከፊል እርጥበታማ አካባቢዎች የሚያድግ በመሆኑ በቀላሉ መትከል ይቻላል። ይህ ዛፍ ከረግረጋማና ውሃ አዘል ቦታዎች በስተቀር የኮምጣጣነት መጠኑ ከ5-9 በሆነ በማንኛውም የአፈር አይነት እና ሁኔታ፤ ከባህር ወለል በላይ ከ500 - 2100ሜ በሆነ ከፍታ ፤ ከ500-1400 ሚ.ሜ የሆነ የዝናብ መጠንና ከ24-30 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ዓመታዊ አማካይ የሙቀት መጠን ይፈልጋል። በአጠቃላይ ተስማሚ የአየር ንብረት ካገኘ የተተከለው ችግኝ ምንም አይነት የመጠውለግ ሁኔታ የማይስተዋልበትና ለአካባቢ ጥበቃ ስራዎችም ከፍተኛ ፋይዳ አለው።
ጠቀሜታና አገልግሎት
ለማስተካከልበተለያዩ ክፍለ-ዓለማት የሞሪንጋ ዛፍ (ሽፈራው) የተለያዩ ጥቅሞች አሉት። የሽፈራው ቅጠል በውስጡ የተለያዩ ንጥረ ነገሮችን የያዘ በመሆኑ የምግብ ይዘት አትክልትን መተካት የሚችል ዛፍ እንደሆነ ጥናቶች ያሳያሉ። ስለዚህም የጎመን ዛፍ በመባል ይታወቃል። በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ፍጆታን ለማሟላት፣ የገቢ ምንጭን ለማሳደግ፣ የመሬትን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ እና ለተለያዩ የባህላዊ መድሃኒትነት አገልግሎት የሚውል ሁለገብ ጠቀሜታ ያለው የአግሮፎሬስትሪ ዛፍ ነው።
ለምግብነት
ለማስተካከልቅጠል
ለማስተካከልቅጠሉ በቪታሚን (ኤ፤ ቢ፤ ሲ)፣ በካልሲየምና በብረት የበለፀገ በመሆኑ ለምግብነት ተመራጭ ነው። በደቡብ ኢትዮጵያ የሚገኙ የኮንሶ ብሄረሰብ ዘንድ ተወዳጅ የሆነ የዕለት ተዕለት ምግብ ውስጥ እየተካተተ ለዘመናት የተጠቀሙበት ዛፍ ነው።
የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያሳዩት የሽፈራው ቅጠል ከተለያዩ የሰብል ዓይነቶች ጋር በንጥረ ነገር ተወዳዳሪነት አለው። ይህ የሚያሳየው የሽፈራው ዛፍ በሰዎች የእለት ተዕለት አመጋገብ ስርዓት ላይ ጉልህ ሚና መጫወት የሚችል መሆኑን ነው። የሚከተለው ሰንጠረዥ 2 እንደሚያመለክተው ሽፈራው በንጥረ ነገር ከተለያዩ ምግቦች ጋር ሲወዳደር ነው።
አዲስ የተቆረጠ ቅጠል ደርቆ የተፈጨ ቅጠል • ከካሮት ቫይታሚን ኤ በ4 እጥፍ ይበልጣል • በ10 እጥፍ ይበልጣል • ከብርቱካን ቫይታሚን ሲ በ7 እጥፍ ይበልጣል • 1/2ኛ ያህል ይዟል • ከወተት ካልሼም በ4 እጥፍ ይበልጣል • በ17 እጥፍ ይበልጣል • ከሙዝ ፖታሼም በ3 እጥፍ ይበልጣል • በ15 እጥፍ ይበልጣል • ከቆስጣ ብረት 3/4ኛ ያህል ይዟል • በ25 እጥፍ ይበልጣል ሰንጠረዥ ሽፈራው በምግብ ይዘት ከሌሎች ሰብሎች ጋር ሲነጻጸር
ቅጠሉን በተለያየ መልክ በማዘጋጀት መመገብ በውስጡ የሚገኙ በምግብነታቸው የታወቁ ጠቃሚ ንጥረ ነገሮችን በቀላሉ ማግኘት ይቻላል። ለአብነት ያህል እንደ ጎመን በመቀቀልና በመከሸን በእንጀራ ወይም በሳንዱዊች መልኩ በማዘጋጀት መመገብ ይቻላል። የሞሪንጋ ሳምቡሳና የሞሪንጋ ጭማቂ ማዘጋጀት ይቻላል። በተጨማሪም ከሾርባ ጋር ጨምሮ በማዘጋጀትም ሆነ ከእንቁላል ጋር አብሮ በመምታት መጥበስና መመገብ ይቻላል። ለተጠቃሚዎች በተለይም ለአርሶ አደሮችና የሽፈራው /ሞሪንጋ/ ምግብ በማዘጋጀት ለምግብነት እንደሚውል በሰርቶ ማሳያ በምርምር ማዕከላት ተረጋግጧል።
ሻይ
ለማስተካከልሞሪንጋ ከምግብነት አገልግሎት ባሻገር ለሻይ መጠቀም ይቻላል። የሞሪንጋን አዲስ የተቆረጠ ቅጠል ወይም ደርቆ የተፈጨውን ዱቄት ለሻይ ማዋል ይቻላል።
ፍሬ
ለማስተካከልዘር አቃፊ /ፖድ ወይም ቆባ/ በለጋነቱ እንደፎሶሊያ ተቀቅሎ መመገብ የሚቻል ሲሆን በአንድ ዛፍ በአማካይ በዓመት እስከ 70 ኪሎ ግራም ድረስ ምርት ይሰጣል።
ፍሬው ከደረቀ በኋላ ከዘሩ 40 በመቶ የምግብ ዘይት የሚሰጥ ሲሆን ተረፈ ምርቱ ወይም ፋጉሎ ለከብት መኖ ወይም ለውሃ ማጣሪያ ያገለግላል። ፍሬውን በቀጥታ መመገብ ፀረ-ትላትል፣ የጉበት ችግርን፣ የእንቅልፍ ችግርንና የመገጣጠሚያ ቁርጥማትን ማከም እንደሚቻል ጥናቶች ያሳያሉ። በተጨማሪም ከፍተኛ ፕሮቲንና የፋይበር ይዘት ስላለው የተመጣጠነ የምግብ እጥረትንና የተቅማጥ በሽታን ለመከላከል ያስችላል።
ውሃ ማጣራት
ለማስተካከልከወንዝ የተቀዳ ንፁህ ያልሆነ (የደፈረሰ) ውሃን ተፈጭቶ በላመ የሽፈራው ዘር ዱቄት በመጨመር በፍጥነትና ቀላል በሆነ ዘዴ ማከም ወይም ማጣራት ይቻላል። የሞሪንጋ ዘር ካታዮን (Cation) የተባሉ በውስጡ የያዘ በመሆኑ የደፈረሰ ውሃን ለማጥራት ይረዳል። ከዘሩ የተገኘ ዱቄት ከውሃው ውስጥ ካሉት ጠጣር ነገሮችኝ በማጣበቅ ወደ ታች እንዲዘቅጡ ያደርጋል። ይህ የማከም ዘዴ ከ90-99% በውሃው ውስጥ ባክቴሪዎችን ለማስዎገድ /ለመግደል/ ያስችላል። የተለያዩ ኬሚካሎችን ለምሳሌ አሉሚኒየም ሰለፌት /Aluminum Sulfate/ የተባሉ ለሰው ልጅ አደገኛና ጎጂ የሆኑ ንጥረ ነገሮች ለማጣራት ይረዳል።
ለከብት መኖ
ለማስተካከልቅድሚያ የሚሰጠው ለሰው ምግብነት ቢሆንም ፍሬው ከመድረቁ በፊት ለከብት መኖ በመሆን ያገለግላል። የዘይቱ ተረፈ ምርት (ፋጉሎ) ለውሃ ማጣሪያና በፕሮቲን የበለፀገ የከብት መኖ መሆን ይችላል። ቅጠሉም እንዲሁ ለከብት መኖ ያገለግላል።
ከዚህ ባሻገር ዛፉ ለንብ መኖ፣ ለአጥር (Live fence)፣ መድሃኒትነት፣ ለማዳበሪያነት ይውላል፡፡
የንብ መኖ
ለማስተካከልይህ ዛፍ አበባ ሰጪ ከሚባሉና መዓዛማ አበባ ከሚሰጡ የዛፍ ዝርያዎች ውስጥ አንዱ ነው። ንብ ማነብ ቀጣይና አዋጭ እንዲሆን ለማድረግ በቋሚ ተክል ልማት መመስረት ቢችል ተመራጭነት አለው። ይህ ተክል በተለያዩ የእንክብካቤና አያያዝ ስልቶች ዓመቱን በሙሉ አረንጓዴና ታዳጊ ማድረግ ስለሚቻል ከፍተኛ የሆነ የአበባ ምርት ይሰጣል። ይህ ደግሞ በንቦች የቀሰም ዕፀዋት እጥረት በሚኖርበት ወቅት ለንቦች ምግባቸውን በማሟላት ][ማር]] ዓመቱን ሙሉ እንዲመረት ይረዳል። ስለዚህም የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት በማሳደግ ተጨማሪ የገቢ ምንጭ እንዲፈጥር የሚያስችል ስለሆነ ሁለገብ ጠቀሜታ ካላቸው የጥምር ግብርና (አግሮፎሬስትሪ) ዛፎች እንዲመደብ ያደርገዋል።
አበባ
ለማስተካከልከአበቦቹ የተገኘ ጭማቂ ጡት የምትመግብን ሴት የወተት ጥራትና ፍሰት መጠን ያሻሽላል፤ ከሽንት ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮችን በመፍታት የሽንት መፈጠርን ያበረታታል።
እንጨት
ለማስተካከልገርና በቀላሉ ተሰባሪ በመሆኑ ለጣውላና ሌሎች የእንጨት ውጤቶች አገልግሎት የመዋል ውስንነት ይታይበታል።
ለአጥር (Live fence)
ለማስተካከልየሽፈራው ዛፍን በመትከል ህይወት ያለው አጥር በመጠቀም ለንፋስ መከላከያና ለጥላነት ያገለግላል። ይህም በዝዋይና ሌሎች ደረቃማ አካባቢዎች ልምዶች ያሉ በመሆኑ ለንፋስ መከላከያነት መጠቀም ይቻላል። ዛፉ በፍጥነት ስለሚያድግ በአጭር ጊዜ ለጥላ አገልግሎት ሊደርስ ይችላል።
መድኃኒትነት
ለማስተካከልእስካሁን ድረስ በዓለም ዙሪያ የሽፈራው እያንዳንዱ ክፍል ሙሉ በሙሉ በተለያየ መልኩ ለመድሃኒትነት ይውላል። ለምሳሌ የደም ማነስና የጉበት ችግርን ማከም ይችላል።
ለማዳበሪያ
ለማስተካከልዘሩ ለዘይት ከተጨመቀ በኋላ የሚቀረውን ተረፈ ምርት ለከብት መኖ ወይም ኮምፖስት በማዘጋጀት ለማደበሪያነት ሊውል ይችላል።