ማጎግ
ማጎግ (ዕብራይስጥ፡- מגוג) በኦሪት ዘፍጥረት ምዕ. 10 መሠረት ከያፌት ሰባት ልጆች ሁለተኛው ነው።
ማጎግ ደግሞ በትንቢት ይጠቀሳል፤ በተለይ ትንቢተ ሕዝቅኤል 38፡2 ጎግ የሚባለው አለቃ ሲገልጽ የአገሩ ስም «ማጎግ» ይባላል፦ «በጎግ ላይና በማጎግ ምድር ላይ፣ በሞሳሕና በቶቤል ዋነኛ አለቃ ላይ» ይላል። በዮሐንስ ራዕይ 20፡8 «በአራቱም በምድር ማዕዘን ያሉትን አሕዛብ፥ ጎግንና ማጎግን፥ እንዲያስታቸው ለሰልፍም እንዲያስከትታቸው ይወጣል፤ ቍጥራቸውም እንደ ባሕር አሸዋ የሚያህል ነው» ሲል እዚህ ለመጀመርያው ጊዜ «ጎግና ማጎግ» አንድላይ ይሰየማሉ። «ጉግማንጉግ» የሚለው የአማርኛ ዘይቤ ከዚህ ጥቅስ (ራዕይ 20፡8) የተወረደ ነው።
የአይሁድ ታሪክ ጸሐፊ ዮሴፉስ (1ኛው ክፍለ ዘመን ዓ.ም.) እንዳለው የማጎግ ልጆች የእስኩቴስ ሰዎች ነበሩ፤ ይህም ብሔር በጥንት ከጥቁር ባሕር ስሜን የተገኘ ሰፊ ሕዝብ ነበር።[1][2] ግሪኮች እስኩቴስን «ማጎጊያ» ይሉት እንደ ነበር ጻፈ (Ant., bk. I, 6)።
ኢሲዶር ዘሰቪላ (600 ዓ.ም. ግድም) እንደ ጻፈው፣ ከዚህ በላይ አንዳንድ ሰዎች ማጎግ የጎታውያን አባት እንደ ነበር ይቆጥሩት ነበር በማለት ይጨምራል። ዳሩ ግን ይህ 'ስለ ስሞቹ ተመሳሳይነት ይሆናል' ብሎ መሰለው። (Etymologiae, IX, 89). በስዊደን ታሪክ ጸሐፊ ዮሐንስ ማግኑስ (1480-1536 ዓ.ም.) ዘንድ፣ ማጎግ ከማየ አይኅ 88 ዓመታት በኋላ በፊንላንድና በስዊድን አገር ሠፈረ። የማጎግ 5 ልጆች ስዌኖ (የስዊዶች አባት)፣ ጌጣር ወይም ጎግ (የጎታውያን አባት)፣ ኡቦ (ኡፕሳላ ከተማ የሠራው) ቶርና ገርማን ነበሩ።[3] የማግኑስ መጽሐፍ በስዊድን ግቢ ለረጅም ጊዜ ተቀባይነት አገኘ፤ ለምሳሌ የስዊደን ንግሥት ክሪስቲና እንደ ቈጠረችው፣ ከማጎግ ጀምሮ ከነበሩት ነገሥታት እርስዋ 249ኛዋ ነበረች። እንዲሁም የፊንላንድ ጸሐፊ ዳኔል ዩስሌኒዩስ (1668-1744 ዓ.ም.) እንዳለው፣ ማጎግ ቱርኩ ከተማ በፊንላንድ መሠረተ የፊንላንድም ሕዝብ ከማጎግ ተወልደው ነበር።
በአይርላንድ ዜና መዋዕሎች ዘንድ፣ የአይርላንድ ሕዝብ ከእስኩቴስ መስራች ከያፌት ልጅ ማጎግ ዘር የተከለሰ ሕዝብ ናቸው። በዚህ ልማድ የማጎግ 3 ልጆች በዓጥ፣ ዮባጥና ፋጦቅታ ናቸው። ደግሞ ፌኒየስ ፋርሳ፣ ፓርጦሎንና ኔሜድ እንዲሁም ፊር ቦልግና ቱአጣ ዴ ዳናን ከማጎግ ነገድ እንደ ተወለዱ ይታመን ነበር።
እንዲሁም ሁኖች የተባለው ብሔርና ማውጃር የተባለው (የሀንጋሪ ሕዝብ) ከመንታዎቹ ሁኖርና ማጎር እንደ ተወለዱ የሚል የሀንጋሪ ትውፊት አለ። እነዚህ ወንድማማች ከማየ አይኅ በኋላ በአዞቭ ባሕር አጠገብ ሲኖሩ ሚስቶች ከአላኖች እንደ ወሰዱ ይተረታል። በአንድ የ14ኛው ክፍለ ዘመን መጽሐፍ ክሮኒኮን ፒክቱም ዘንድ ይህም ማጎር መታወቂያ የያፌት ልጅ ማጎግ ነበረ።
መጣቀሻዎች
ለማስተካከል- ^ "Antiquities of the Jews, Book I, Chapter 6". Archived from the original on 2011-05-16. በ2011-01-23 የተወሰደ.
- ^ «መጽሐፍ ቅዱስ አዲሱ መደብኛ ትርጉም ከማጥኛ ጽሑፎች ጋር» እንዳለው፦ «ማጎግ የሲቲያን ሕዝቦች አባት ሊሆን ይችላል፤ ይኖሩ የነበሩትም ከጥቁር ባሕር በስተ ደቡብ ምሥራቅ ነበር።» «ሲቲያን» ከ«እስኩቴስ» አጠራር በእንግሊዝኛ ሲሆን፣ በጥቁር ባሕር ደቡብ ምስራቅ በታሪክ የተገኙ ምናልባት 700 ዓክልበ. ነበር።
- ^ Johannes Magnus, Historia de omnibus Gothorum Sveonumque regibus, 1554, I, Chapters 4–5, GMC., Cambridge Mass, oclc 27775895