ጋውት
(ከጌጣር የተዛወረ)
ጋውት ወይም ጋውቲ፣ ጋውትር፣ ጌጣር፣ ጎጡስ በጥንታዊ ጀርመናውያን አፈ ታሪክ የጎታውያን ነገዶች አባት ነበር።
የጀርመን መምህር ዮሐንስ አቬንቲኑስ (1515 ዓ.ም. ግድም) እንዳለው በናምሩድ ዘመን ጎጡስ ወደ አውሮጳ ከቱዊስኮን ጋር ከሄዱት 20 መኳንንት መካከል አንዱ ነበር። በቱዊስኮን መንግሥት የራሱ ክፍል ጎጣላንድ (አሁን ደቡብ ስዊድን) ሆነ። በአቬንቲኑስ ዘመን ደግሞ የጻፈው ሊቅ ዮሐንስ ማግኑስ እንዳለው፣ ጌጣር ወይም «ጎጉስ» የማጎግም ልጅ ሲሆን የጎታውያን መጀመርያ ንጉሥ በጎጣላንድ ሆነ።
በጥንታዊ ኖርስኛ ልማዶች፣ ጋውቲ ወይም ጋውትር የአረመኔ አምላክ ኦዲን ልጅ ነበር። ብዙ ጊዜ ጋውት ወይም ጋውትር ደግሞ የኦዲን ስያሜ ሆኖ ይታያል።
በጥንታዊ እንግሊዝኛ የነገሥታት ዘር ሐረጎች ዘንድ፣ «ጌየት» የተባለ ወላጅ በአረመኔዎች በኩል እንደ አምላክ ይቆጠር ነበር። ይህ ጌየት የ«ታቷ» ልጅ ይባላል።
የጎታውያን ታሪክ የጻፈው መምህር ዮርዳኔስ እንደ መዘገበው፣ የአገር ውጭ ጎታውያን አባት «ጋፕት» ተባለ። ይህ በፊድሉ ለ«ጋውት» እንደ ተሳተ ይገመታል። ዳሩ ግን በዮሐንስ ማግኑስ ዝርዝር «ጋፕቱስ» የቤሪክ ልጅ ሲሆን የውጭ አገር ጎታውያን አባት ነው። የማጎግ ልጅ ጌጣር ግን የውስጣዊ ጎታውያን አባት ይባላል።