'ፍካሬ ዞራስተር: ወደ ሁሉምና ወደ ማንም' በፍሬድሪች ዊልሄልም ኒሺ የተደረሰ የፍልስፍና ልቦለድ* ነው። መጽሐፉ በ1883 እና 1885 (እ.ኤ.አ) መካከል በ4 ክፍል የተደርሰ ሲሆን በጊዜው ይሰራበት ከነበረው የአስተሳሰብ ዘዴ ለየት ባለ መልኩ የፍልስፍናን እና የግብረገብን ጥናቶች መርምሯል። የመጽሃፉ አትኩሮቶች፡ የዘላለማዊ ምልልስኃይልን መፍቀድ (*ፈቃድ እዚህ ላይ ጠንካራ ፍላጎት ማለት ነው)፣ የአዳዲስ ዋጋ ወይም ህግጋት አስፈላጊነት፣ የአምላክ በጊዜው በነበሩ አውሮጳውያን ልብ ውስጥ መሞት፣ የበላይ ሰው (*በኒሺ አስተሳሰብ የሰው ልጅ በጦጣወችና በበላይ ሰው መካከል ያለ ፍጡር ነው) መምጣት ትምቢቶች ነበሩ። [1] ጽሁፉ የመጽሐፍ ቅዱስ አጻጻፍ ስልት ይከተል እንጂ የውስጡ ፍሬ ነገር ግን የክርስትናአይሁድ ሃይማኖቶችን መሰረታዊ እምነቶች የሚጻረር ነበር። ኒሺ ይህን መጽሐፍ " ከሰወችና ከጊዜ 6000 ጫማ" እርቆ እንደጻፈ ይናገራል፣ ማለቱም የመጽሃፉን ሃሳቦች በተራራ ላይ እያለ እንዳገኛቸው ለማስገንዘብ ነበር።[2]

ፍካሬ ዞራስተር

ኒሺ ይህን "ፍካሬ ዞራስተር" ብሎ የሰየመውን መጽሃፍ "ስርዓት አልባ"(ጥራዝ ነጠቅ) ወይም ስርዓት ይለሽ በሆነ ዘዴ ስለጻፈው ለተመራማሪወች እጅግ አስቸጋሪ ሆነ። ይሁንና ተመራማሪወች አንድ አንድ ቋሚ የሆኑ የመጽሃፉን ይዘቶች ማስተዋላቸው አልቀረም፦

  • የበላይ ሰው፡ ለኒሺ የበላይ ሰው ማለት በራሱ ላይ ሙሉ ቁጥጥር ያለው ግለሰብ፣ እምቅ ኃይሉን ወደ ስራ የተርጎመ ሰው ማለት ነው። አሁን ያለው የሰው ልጅ (በኒሺ አሰተያየት) በእንስሳ እና በዚህ በበላይ ሰው መካከል ያለ ፍጡር ነው።
  • የዘላለም ምልልስ፡ ማናቸውም የተከሰቱ ነገሮች እንደገና ይከሰታሉ፣ አሁን የሚከሰቱ ነገሮች ድሮም ተከስተው ነበር ለወደፊቱም እልፍ አዕላፍ ጊዜ ይከሰታሉ! ይህ አለም ልክ እንደምናየው ሆኖ እንደገና ይከሰታል፣ ሰውም ይሞታል ግን ልክ በነበረበት መልኩ በነበረበት አለም ተመልሶ ይመጣል።
  • ኅይል መፍቀድ፡ የሰው ተፈጥሮ መሰረታዊ ባህርይ ነው። ማናቸውም የምንሰራቸው ነገሮች፣ እንደ ኒሺ አስተያየት፣ የዚህ መሪ ሃሳብ መገለጫ ናቸው። ከመራባት፣ ደስታ፣ ሐሴት ጋር ሲነጻጸር የኅይል መፍቀድ ሁሉም የሰው ልጅ ከከባቢው አለም ጋር የሚያደርገውን ትግል ጠቅልሎ የሚይዝ ጽንሰ ሃሳብ ነው።
  • ክፋትና ደግነት በተሰኙ ተቃራኒ የክርስትና ሃሳቦች ላይ ብዙ ትችት መመስረት። በኒሺ አስተያየት እኒህ ነገሮች የሰው ልጅ ፈጠራወች እንጂ በተፈጥሮ የሚገኙ አይደሉም። በሱ አስተያየት የሰው ልጅ ተግባር መለካት ያለበት አስቀድሞ በተቀመጡ የግብረ ገብ ዋጋወች/ህጎች (ጥሩና መጥፎ) ሳይሆን የተግባሩን መዘዝ በመለካት ነው።


መጽሐፉ ባጭሩ

ለማስተካከል

በመጽሃፉ መግቢያ ላይ ዞራስተር 30 አመት ሲሞላው ወደ ተራራ እንደወጣና በዚያ ከሰወች ተገሎ ብዙ ጥበቦችን እንደሰበሰብ እናነባለን። 40 አመት ሲሞላው ያከማቸውን ጥበብ ለማካፈል ከተራራው ወረደ። የመውረዱ ዋና አላማ "የበላይ ሰው"ን መምጣት ለመስበክ ነበር። የበላይ ሰው፣ በዞራስተር አስተሳሰብ፣ ከሰው በላይ የሆነ ፍጡር ማለት ነው፡ ልክ የሰው ልጅ ከጦጣወች በላይ የሆነ ፍጡር እንደሆነ።

በዞራስተር ግምት ዘመናዊው ሰው የሞራል ግሽበት፣ ባዶነትና አጠቃላይ የህይወት ውዥንብር ስለገጠመው አዲስ ትምህርት ያስፈልገዋል። በዞራስተር አስተሳሰብ የዘመናዊው ሰው መንፈሳዊ ግሽበት ምክንያት የአምላክ መሞት ነው። በርግጥ አምላክ ለመሞት አይቻለውም ሆኖም ግን በዞራስቶር አስተሳሰብ አምላክ ሞተ ማለት ዘመናዊው ሰው በአምላክ ላይ ያለው እምነት መሞት ማለት ነው። ስለሆነም የድሮወቹ ሰወች ብዙ አስደናቂ ስራወችን ለአምላክ ሲሉ ቢሰሩም የዘመናዊው ሰው ግን ይህን እመንቱን በማጣቱ አጠቃላይ ዘመናዊ ህብረተሰብ መሪ ሃሳብ የማጣት፣ የመበስበስና ተስፋ የማጣት ምልክቶች አሳየ። ህግን የሚሰጥ በሰው አምሳያ ያለ አምላክ ለአዲሱ ሳይንሳዊና ዘምናዊ ህብረተሰብ እጅግ ኋላ ቀር መስሎ ታየ። ስለሆነም በተማሩ ዘንድ የአለም የህይወት ትርጉምና የግብረገብ ስርዓት እጅግ ዝብርቅርቅ ያለ ሆነ። ዘመናዊ ሰው ባዶነት "ኒሂልዝም"( የህይወት ትርጉም ማጣት) የሚባል ችግር ተጋረጠው፣ የ"ዞራስተር ፍካሬ" ዋና አላማ ይህን ባዶነት ("ኒሂልዝም" -- የህይወት ትርጉም ማጣት) መታገል ነበር። በኒሺ አስተሳሰብ አዲሱ የ"በላይ ሰው" ትምህርት ለዚህ ዘመናዊ ባዶነት ፍቱን መድሃኒት መሆን ነበር።

ዞራስተር ከተራራው ወርዶ በሰወች መካከል እንዲህ ሲል ሰበከ፡ የሰው ልጅ በአሁኑ ሰዓት ያለበትን መናኛነት (ተራነት)ና የከሰረ ስልጣኔ በማሸነፍ የ"በላይ ሰው"ን መፍጠር አለበት፡ «የሰው ልጅ ሊሸነፍ የሚገባ ነው። ለማሸነፍ እያንዳንዳችሁ ምን አድርጋችኋል?» ሆኖም ግን ይህ ሰበካው ተቀባይነት አጣ። ህዝቡም መልሶ «የበላይ ሰውህን ለራስህ» ብለውም ተሳለቁበት። የተመቻቸና ጥሩ ኑሮ ከመፈለግ ውጭ የበላይ ሰውን እንደማይፈልጉ ነገሩት። ህይወት ከፍተኛ ትርጉም ከሌለው በርግጥም ከደስታ ውጭ ምንስ ያስፈልጋል? በዚህ ምክንያት የስልጣኔ ዋና ዓላማ "ከፍተኛ ደስታ ለከፍተኛ ቁጥር ላለው ሰው" ሆነ።

በዚህ ምክንያት ዞራስተር ለህዝቡ ያለው ጥላቻና ንቀት አደገ ( ምንም እንኳ ከጊዜ ወደጊዜ ሊያዝንላቸውና ሊረዳቸው ህሊናው ቢግደረደርም)። ተማሪውም ሆነ ያልተማረው፣ ፖለቲከኛውም ሆነ ፈላስፋው፣ ሰዓሊውም ሆነ ፕሮፌሰሩ፣ ሁሉም የተደላደለ ህይወት ከመሻት ውጭ ውስጣቸው ያለውን እምቅ ስብዕና ለማሳደግ የማይጥሩ ሆኖ አገኛቸው። ዞራስተር ብዙ ተከታይ ከማፍራት ይልቅ ሊግባባቸው የሚችሉ ጥቂት ፈርጥ የሆኑ ሰወችን ፍለጋ ጀመረ፡ ተራ(መናኛ) ነገሮችን ከህይወት ለማግኘት የሚሞክሩን ሳይሆን፣ ከፍተኛ ነገርን ለማግኘት የሚሞክሩትን። ፍለጋው ጥቂት ሰወችን ስላስገኘለት በዚህ ወቅት ለተመረጡት "ማስተማር" በጥብቅ ጀመረ።

በዚህ የመጽሃፉ ክፍል የዞራስተር ዋና ነጥቦች በስድስት ዋና ዋና ሃሳቦች ይጠቃላል።

  • የመጀመሪያው የዞራስተር ነጥብ አጠቃላይ ሜታፊዝክን መካድ ነው። ሜታፊዚክ ማለት በተጨባጩ አለም ጀርባ የማናየው፣ የማንዳሰሰው፣ የማናሸተው እውነተኛ አለም አለ በማለት ይህን አለም ለማግኘት የሚጥር የፍልስፍና ዘርፍ ነው። በዞራስተር አስተያየት አንድ አለም ብቻ አለ፡ እርሱም ተጨባጩ አለም ነው።
  • ሁለተኛው የዞራስተር ነጥብ የአይምሮአካል ክፍፍልን መካድ ነበረ። በተለምዶ ሰው አካል አለው ብንልም በዞራስተር አስተያየት ሰው እራሱ አካል ነው። የሰው ልጅ ከማይጨበጥ ምናባዊ ነገር (አዕምሮ) እና ከተጨባጭ ነገር (አካል) የተሰራ ሳይሆን ሙሉ በሙሉ ከአካል የተሰራ ነው። በነደካርት የተነሳው ቀልበኛ ፍልስፍና የስውን ልጅ ከሁለት (አዕምሮና ሰወነት) ከከፈለ ወዲህ የስው ልጅ የስራ ውጤቶች ብዙ አመርቂ አልሆኑ፣ ይልቁኑ የጥንቶቹ ከያኒያን በ"ደማቸው የጻፉዋቸው መጽሃፎች" (በአይምሮ ከተጻፉ ዘመናዊ መጽሃፎች) በተለየ መልኩ ስሜት የሚነኩ እንደነበሩ አስተማረ። የሰው ልጅ "አዕምሮ" ከሆነ ወዲህ ስራው ሁሉ በቀመር የተወጠረና ምንም ስሜት የማይቀስቀስ ሆነ።
  • ዞራስተር ሙሉ በሙሉ የግለሰብ ነጻነትን ይደግፋል። ግብረገብ፣ የጋራ ሰላምና፣ ይሉኝታ ለዞራስተር ደንታው አይደሉም። የህይወት ኃይሎች በምንም አይነት መታፈን የለባቸውም። የተመረጡ ነፍሶች የመንጋወችን ግብረ ገብና ስርዓቶች ወደጎን ትተው የራሳቸውን ዋጋ/ህግ አውጥተው የራሳቸውን አላማ ለማስፈጸም ይታገላሉ። ትክክለኛው የህይወት ጣዕም በህግጋትና ግብረገብ የተጋረደ ሳይሆን ከኃጢያትጽድቅ ወዲያ ርቆ የሚገኝ ነው።
  • ሙሉው የግለሰብ ነጻነት "ሁሉ በሁሉ ላይ" ጦር እንዲያነሳ ሊያደርግ ይችላል። ይህ ግን በዞራስተር አይን ምንም አይደለም ምክንያቱም ሁሉም ህይወት ያለው ነገር "ኃይልን ይፈቅዳል"፡ ሁሉም ህይወት ያለው ነገር እራሱን ያረጋግጣል፣ ለመኖሩም ምልክት ትግል ያካሂዳል። ሄራክሊተስ እንደጻፈ "ጦርነት የሁሉ ነገር አባት ነው"፣ በዞራስቱራ አስተያየት ያለፍልሚያ ምንም ጥቅም ያለው ነገር አይመጣም። ዞራስተር ለጓደኞቹ የሚመክረውም "በአደጋ ኑር!" እያለ ነበር። ፍቅረኛሞች እንኳ ሳይቀሩ ችግር ሊገጥም እንዲችል መረዳት አለባቸው፣ በፍቅር መጎዳት የሚፈራ ወይም ቂም የሚያሲይዝ ሳይሆን እራስን ለማሳደግና አዳዲስ ነገሮችን ለመረዳት የሚያገልግል ዕድል ነው። ጦርነት ተቀባይነት ያለው መሳሪያ ብቻ ሳይሆን ተቀባይነት ያለው ግብም ነው።
  • እራስን መወሰን ለዞራስተር ፍልስፍና ዋና ቁልፍ ነው። ይህ አለም ከላይም ሆነ ከታች ከጎንም ሳይቀር የተሰጠው ትርጉምም ሆነ ህግጋት የሉትም። ሁሉም ሰው የራሱን ትርጉምና ህግጋት በመፍጠር እራሱን ይወስናል። ሁሉም ሰው ልክ እንደሙሴ የራሱን ጽላት እንዲቀርጽ እንጂ ለሁሉም የሚሰራ ከላይ የተላለፈ ህግ የለም። ከዚህ አንጻር እራስን መወሰን ባንድ በተስተካከል የአለም ስርዓት ውስጥ ራስን መቻል ሳይሆን ከትርምስ ውስጥ የራስን አለምን እንደመፍጠር ነው።
  • ህይወት ሂደት እንጂ ሁኔታ አይደለም። አንድ የሰው ልጅ በሂደት ላይ ያለ እንጂ፣ ቆሞ ያለ የሆነ ነገር አይደለም። እራስን እንደ አንድ ቋሚ ነገር ማሰብ በዞራስተር ስህተት ነው። በመጠበቅ፣ እውቀትንና ሃብትን ዝም ብሎ በማከማቸት ህይወት አይኖርም፣ ይልቁኑ እራስን በየጊዜው በማሸነፍና እራስን በመቀየር ህይወት ይኖራል።

ሶስቱ ሽግግሮች

ለማስተካከል
  • ሌላው የዚህ ክፍል ዋና ሃሳብ ሶስቱ ሽግግሮች ናቸው፡፡የሰው መንፈስ እውነቱንና እራሱን ለማወቅ 3 ከባድ ለውጦች እንደሚያካሂድ ዞራስትራ በዚህ ክፍል ሲያስረዳ፦
" እነሆ ነፍሳችሁ ሶስት ጊዜ ይሻገራል፡ እንኪያስ ግመል ነበራችሁ፣ ግመሉ አምበሳ፣ በመጨረሻ አምበሳው ህጻን ልጅ!"

ትርጉሙም የመጀመሪያው የመንፈስ ለውጥ ወደ ግመል ሲሆን ይህም "ትሁት መንፈስ"ን ያመላክታል፡ እራስን መካድ፣ በሃብት መቆጠብን፣ መታዘዝንና ችግርን መቋቋምን። ይህም ግመልን እራሷን ዝቅ አድርጋ የጭነት እንስሳ እንደሚያደርጋት ባህርይ ነው።

" ጫን ያለበት መንፈስ እንዲህ ይጠይቃል "ከሁሉ ነገር ከባዱ ምንድን ነው?" መልሶም "በጫንቃየ ላይ ጭነቴን አዝየ በጥንካሬየ ሐሴት ማድረግ አይደለምን? እራሴን በማዋረድ ኩራቴን መግደል አይደለምን? የዋህነቴን በማጋነን ጥበቤን መፎተት አይደለምን?"

ከዚህ የግመል አለም ወደ አንበሳነት የሰው መንፈስ ለሁለተኛ ጊዜ ይሻገራል። በዚህ ጊዜ ከጭነት ነጻ ይሆናል፣ ከላይ ወደታች በተዘርጋ የሃይል አሰላለፍ ቁንጮውን ለመያዝ ጥረት ያደርጋል፣ ራስ ገዝ ሆኖ ነጻነቱን በራስ ገዝነትና በሃያልነት ይደነግጋል። በታላቁ ዘንዶ ላይ ጦርነት ይክፈታል፣ የቀድሞውን ግብረገብ ጽንሰ ሃሳብ አውልቆ ይጥላል።

"ለራሱ ነጻነትን ለመቀዳጀት፣ በህግጋት ላይ ሳይቀር "እምቢ" ለማለት፣ ወንድሞች፣ ለዚያ ለዚያ አንበሳ ያስፈልጋል። አዳዲስ ህግጋትን የመፍጠር መብት እንዳለ ለማወቅ ለተሸካሚና ለአክባሪ ነፍሳት እጅግ አስቸጋሪ ነው። ይህ ተግባር ለነዚህ እንደ ማደን እና የሚታደን እንስሳ ስራ ነው።"

አንበሳ እንግዲህ የነበረውን እምቢ በማለት የሚያፈርስ እንጂ አዲስ የሚፈጥር አይደለም። ስለሆነም የሰው መንፈስ አዳዲስ ህግጋትን ለመፍጠር ለ3ኛ ጊዜ መሻገር ይኖርበታል። በዚህ የመጨረሻው ሽግግር መንፈሱ ከአንበሳ ወደ ህጻን ይቀራል። ህጻኑ አዲስ ጅማሬን፣ ንጹህ የዋህነትን የሚወክልና የድሮወቹን ህግጋት ድል ካደረገ በኋላ አዲስ ዋጋወችን ፈጣሪ ይሆናል።

"ሕጻን የዋህነት ነው፣ ያለፈውን መርሳትም ነው፣ አዲስ ጅማሬ፣ ጨዋታ፣ እራሱን የሚያሽከረክር ጎማ፣ የመጀመሪያ እንቅስቃሴ፣ ቅዱስ የሆነ "አወ-ማለት"። አወ! ወንድሞች፣ የፈጠራ ጨዋታ ቅዱስ የሆነ "አወ" ማለትን ይጠይቃል፡ መንፈስ የራሱን ፈቃድ ይፈቅዳል፣ አለሙን ያጣ እንግዲህ የራሱን አለም ያገኛል።"

ሁሉ ነገር በህጻን ልጅ ተጀምሮ እንደገና በህጻን ማብቃቱ የኒሺን የዘላለም ምልልስ ጽንሰ ሃሳብ የሚያንጸባርቅ ነው። በዚህ የዘላለም ድግግሞሽ የሰው ልጅ እራሱን በማሽነፍ ከነበሩበት ድክመቶች ሁሉ ነጻ በመውጣት አዲስ አይነት ሰው -- የራሱ ህግ/ዋጋ ያለው የበላይ ሰው ይፈጥራል።

እኒህን ነጥቦች ለተመረጡ ተከታዮቹ ካስተማረ በኋላ ዞራስተር ወደተራራ ዋሻው እንደተመለሰ መጽሃፉ ያትታል። የዚህ ምክንያቱ ያለሱ ተጽዕኖ ተከታዮቹ በራሳቸው ውሳኔ የራሳቸውን ሃሳብ እንዲያዳብሩ ነው። አስተማሪነቱን ማቆሙም ይህን የፍልስፍናውን ግብ ላለማጣረስ ነበር።

በሁለተኛው ክፍል ዞራስተር ከከተማውና ከገበያው በመሸሽ ወደ ተራራው ስለመመለሱ ያትታል።

"ዘሩን እንደዘራ ገበሬ ማደጉንም እንደሚጠባበቅ፣ ዞራስተር ከሰወች በማምለጥ ወደአምባው፣ ወደ የብቸኝነት ዋሻው ተመለሰ"

ዞራስተር በዚህ ወቅት ከተራራው ወርዶ ስላጋጠመው ሁኔታ ማንሰላሰል ጀመረ፣ በተለይ "ኃይልን መፈለግ" ("ኃይልን መፍቀድ") የሚለውን ጽንሰ ሃሳብ ተገነዘበ

በሄድኩበት ቦታ ሁሉ ያገኘሁት ህይወት ያለው ነገር ሁሉ ኃይልን ይፈቅዳል፣ የሚታዘዙት እንኳ ሳይቀር ጌታ ለመሆን ይፈቅዳሉ! ደካሞች ለጠንካሮች ለመታዘዝ በሌላ ሳይሆን በራሳቸው ፈቃድ ይስማማሉ፣ ደካሞቹ ደግሞ በተራቸው ከነሱ የበለጠ ደካማ ለሆነው ጌትነት ይፈቅዳሉ፡ ይህ ጨርሰው ሊተውት የማይፈቅዱት ደስታቸው ነው!
ታናናሾቹ ከነሱ ያነሱት ላይ ኅይል እንዲኖራቸው ለበላዮቻቸው ፈቀቅ እንደሚሉ ሁሉ ከሁሉ የበላይ የሆነው ለአደጋና ከባድ ፈተና እንዲሁ ፈቀቅ ይላል፣ ለኅይል ሲልም ህይወቱን አደጋ ላይ ይጥላል። የሁሉ ታላቅ ፈቀቅ ማለት ለህይወት አስጊ ለሆነ አደጋና በሞትና በህይወት ቁማር ለመጫወት ነው።

ይህ የጽሁፍ ክፍል ዞራስቶራ በ3ኛው የመጽሃፍ ክፍል የሚያጋጥመውን ፈተና በመተንበይ ይከናወናል፡

ይህን በምሳሌ እነግራችዋለሁ። ትላንትና ፣ ጸጥታ በሰፈነበት ሰዓት፣ ድንገት ከእግሬ በታች ምድር ተንሸራታ ጠፋች፡ ህልሜም ጀመረ። የጊዜ እጅ ወደፊት በሚነጉድበት፣ የህይወቴ ሰዓት ትንፋሹን በዋጠበት የሰማሁት ጸጥታ ልቤን በፍርሃት ሞላው።
በድንገትም ያለምንም ድምፅ አለኝ "ታውቃለህ ዞራስተር?"
ሹክሹክታው ስላስፈራኝ ጮኽኩ፣ ፊቴም ገረጣ፣ ግን ካፌ ድምጽም አልወጣም!
ቀጠለም "ዞራስተር ታውቃለህ ግን አትናገርም!"
በመጨረሻ በሚገዳደር ቃል ተናገርኩ "አወ! አውቃለሁ ግን መናገር አልፈልግም!"
ድምጽ የሌለው ሹክሹክታ ግን ጠየቀ " አትፈልግም? ይሄ እውነት ነው? በመገዳደር ቃል እራስክን አትደብቅ!"
በዚህ ወቅት አለቀስኩ፣ እንደህጻንም ልጅ ተንቀጠቀጥኩ፣ መለስኩም፡ "ስለእውነትስ እፈልግ ነበር! ግን እንዴት አድርጌ? እባክህ ተወኝ! ይሄ ከኔ በላይ ነው!"
ድምጽ የሌለው ሹክሽክታም መለሰ፣ አለም "አንተ ማን ነህ ዞራስተር? ይልቁን የምትናገረውን ተናገርና ሙት!"

በዚህ ክፍል ዞራስተር ሃሳቡን ወደታች የሚጎትተውን ጉልበት በማሸነፍ አዳዲስ ሃሳቦችን ያፈልቃል። ብሎም የዘላለም ምልልስን በግልጽ ይናገራል።

"ኦ! ዞራስተር" አሉ እንስሳቶቹ "ሁሉም ነገር ይሄዳል፣ ሁሉም ነገር ተመልሶ ይመጣል፣ ለዘላለም የህልውና ጎማ ይሽከረከራል። ሁሉም ይሞታል፣ ሁሉም እንደገና ያብባል፣ የህይወት ቀለበት በንዲህ መልኩ ለዘላለም ይቀጥላል። ሁሉም ይሰበራል፣ ሁሉም እንደገና ይጋጠማል፣ ላለም እስከ ዘላለም አንድ አይነት የኅልውና ቤት ይገነባል። ሁሉም ይለያያል፣ ሁሉም ከሁሉ ጋር እንደገና ይገናኛል፣ ለዘለዓለም የኅልውና ቀለበት በራሱ ላይ እንዲህ ይሽከረከራል።"

ይህን በሰማ ጊዜ ዞራስተር የዘላለም ምልልስን ማስተማር የህይወቱ አላማ መሆኑን ተገነዘበ። ስለዚህም ከነበረበት ተራራ ወረደ።

ከዘላለም መመላለስ በተጨማሪ ኒሼ ስለ አዳዲስ ህግጋት/ዋጋወች ማውጣት በዚሁ ክፍል አጥብቆ አስተምሯል።

"በተሰባበሩና ግማሽ ድረስ በተጻፈባቸው ጽላቶች ተከብቤ ተቀምጨ እጠባበቃለሁ። መቼ ይሆን ጊዜየ የሚመጣው?"

በክፍል 4፣ ዞራስተር ከትልልቅ ሰወች ጋር በመገናኘት እራሱን በኒህ ሰወች ይከባል፣ ምግብንም ከነሱ ጋር ይካፈላል፡፡ እነዚህ ታላላቅ ሰወች፡ የግራና የቀኙ ንጉሶች፣ የአረጀው ምትሃተኛ፣ የሮማው ፓፓ፣ ፈቃደኛው ለማኝና ጥላው፣ ንጹህ አዕምሮ፣ በጣም ፉንጋው ሰው ናቸው። እያንዳንዱ ታላቅ ሰው እንግዲህ በአዕምሮው ትክክል ነው ብሎ የተቀበለው ነገር ትክክል ሳይሆን ተጣሞበት (አምላክ፣ እውነት፣ ልብ) ስላገኘ፣ ሆኖም ግን ከዚህ በመነሳት ውሳኔ ላይ መድረስ አቅቷቸው ተስፋ የቆረጡ ነበሩ። በዚህ ምክንያት ድሮ ይሰሩት የነበረውን ስራ መስራት አቅቷቸው የድሮው ስራቸው ተዋናይ/ገጸ ባህርይ ወደ መሆን የወረዱ ነበሩ። ለነዚህ ሰወች ሃዘን ሊገባው የነበረው ዞራስተር ከሃዘኑ ጋር ትንቅንቅ በመፍጠር ሃዘኑን ማሸነፍ እንዳለበት ያሳያል።

[...] "የመጨረሻው ጥፋቴ ምን ይሆን?"
ከዚህ በኋላ ዞራስተር ወደ ራሱ አዕምሮ አተኮረ፣ ከትልቅ ድንጋይ ላይ ተቀምጦም አንሰላሰለ። በድንገት ተስተካክሎ ተቀመጠ፣ መለሰም፦
"ለታላላቆቹ ሰወች ከንፈር መምጠጥ! " በዚህ ጊዜ ፊቱ ወደ ንሐስ ተቀየረ

ከዚህ በኋላ በዚህ ክፍል ዞራስተር እንደ አዲስ ሰው ተቀየረ፣

"አንበሳውም መጥቷል፣ ልጆቸም ተቃርበዋል፣ ዞራስተርም በስሏል፣ ሰዓቴም ተቃርቧል፦ ጎሄ ቀደደ፣ ቀኔ ጀመረ፣ ተነሳ! ተነሳ! አንት ድንቅ ቀትር!"
እንዲህ በመናገር ዞራስተር ዋሻውን ለቆ ወጣ፣ ከድቅድቅ ተራራ መካከል እየተፈናጠቀች እንደምትወጣ የጠዋት ጸሓይ እያብረቀረቀ በጥንካሬ ተራመደ።


 
ወጋገን ፡ የመጽሃፉ መጀመሪያና መጨረሻ የቅኔ ምስል

ከፍካሬ ዞራስተር የተወሰዱ ጥቅሶች

ለማስተካከል
  • ህይወትን የምናፈቅር መኖርን ስለተለማመድን ሳይሆን ማፍቀርን ስለተለማመድን ነው።
  • በፍቅር ውስጥ ሁል ጊዜ ዕብደት አለ። በዕብደት ውስጥ ደግሞ ሁልጊዜ ምክንያት አለ።
  • አንቺ ታላቅ ኮከብ! ፍንትው ብለሽ የምታበሪላቸ ባይኖሩ ደስታሽ ምኑ ላይ ነበር?
  • መብረርን የሚማር ሰው መጀመሪያ መቆምን፣ ከዚያም መራመድን፣ ብሎም መሮጥንና ዛፍ መውጣትን እንዲሁም መደነስን መማር አለበት፣ አንድ ሰው ወደ መብረር መብረር አይችልም!
  • እውነትን መናገር - በጣም ጥቂት ሰወች ይችላሉ! ከነዚህ ከሚችሉት ግን የሚፈፅሙት የሉም`!
  • ደፋር፣ ደንታ የሌለው፣ ተሳዳቢ፣ ጸበኛ-- ጥበብ ከኛ እኒህን ትፈልጋለች፡ ሴት ናትና የምትወደውም ጦረኛን ብቻ ነው።
  • እራሱን የማያዝ መታዘዝ አለበት። ብዙወች እራሳቸውን ማዘዝ ይችላሉ፣ ነገር ግን ለራሳቸው ከመታዘዛቸው በፊት ብዙ ይጎላቸዋል!
  • ማህበረሰብ ተኩላውን አላምዶ ውሻ አደረገ። የሰው ልጅ ከሁሉም በላይ ለማዳ እንስሳ ነው!
  • አንድ ትውፊት አጀማመሩ በሩቅ የዘመን ጭጋግ እየተሸፈነ ከሄደ፣ አመሰራረቱም እየተምታታ ከመጣ - በክብር እያደገ ይሄዳል። ክብሩ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየጨመረ ይሄዳል። በመጨረሻ ትውፊት ቅዱስ ይሆንና በሰወች ዘንድ ድንቅ ይሆናል።
  • ሰው በንዴት አይገልም፣ በሳቅ እንጂ።
  • በቁመና ለማደግ፣ ወደብርሃንም ለመጠጋት በተፈለገ ጊዜ፣ ስርን ወደ መሬት መላክ ያስፈልጋል፣ ወደ ድቅድቅ ጨለማው፣ ወደ ጥልቁ - ወደ መጥፎው።
  • እውነተኛ ወንድ ሁለት ነገር ይፈልጋል፡ አደጋና ጨዋታ። ለዚያ ሲልም ሴትን ይፈልጋል፣ ከሁሉ በላይ አደገኛ የሆነች መጫወቻ።
  • "የታላላቆቹ ተራሮች አመጣት ከየት ይሆን?" ብየ ጠይኩ። ከባህር እንደመጡ ደረስኩበት፣ ማስረጃውም በአለቶቻቸውና በከፍተኛ ገጽታቸው ተጽፎ ይገኛል። ታላላቅ ከፍታወች የሚመጡት ከታላላቅ ጥልቀቶች ነው።
  • ነጻ ከምን? ለዞራስተር ደንታ ይሰጠው ይመስል! ይልቁኑ ብሩህ አይኖችህ እንዲህ ይበሉ፡ ነጻ ምን ለማድረግ?
  • ሳንደንስበት ያለፈን ቀን እንደጠፋ ቀን መቁጥር ይገባል። እንዲሁ በሳቅ ያልታጀበን እውነት ውሸት ማለት ይገባል።
  • መተኛት ቀላል ጥበብ አይደለም፡ ለዚህ ሲባል ቀኑን ሙሉ መንቃት ግድ ይላል።
  1. ^ C. Guignon, D. Pereboom. Existentialism: Basic Writings, 2nd ed., Hackett, 2001. pp. 101-113
  2. ^ Gutmann, James. "The "Tremendous Moment" of Nietzsche's Vision". The Journal of Philosophy, Vol. 51, No. 25. American Philosophical Association Eastern Division: Papers to be presented at the Fifty-First Annual Meeting, Goucher College, December 28-30, 1954. pp. 837-842.