አዕምሮ
(ከአይምሮ የተዛወረ)
አዕምሮ የአንድ ሰው ንቃተ ህሊና አካል ሲሆን በ"ማሰቡ"፣ በ"መረዳቱ"፣ ትዝታን በመፍጠሩ፣ ስሜትን በመረዳቱ፣ በመፍቀዱ እንዲሁም ወደፊት በመመልከቱ የሚገለጽ ነው። በአንዳንድ ፍልስፍናወች አዕምሮ ከአንጎል ይለያል። አዕምሮ እንደ አንጎል ከቁስ ነገር የተሰራ ሳይሆን በምናቡ አለም የተንሰራፋ ነው፡፡ ስለሆነም አዕምሮ ከሞላ ጎደል የማይታይና የማይጨበጥ "ሃሳብ" ስብስብ ነው።
የአዕምሮና የአንጎል ግንኙነት ለብዙ ዘመን በፍልስፍና የተጠናና እስካሁን ድረስ አከራካሪ የሆነ ነው። በአጠቃላይ መልኩ 3 አይነት የፍልስፍና አቋሞች አሉ፣ እነርሱም ሁለትነት፣ ቁስ አካላዊነትና ምናባዊነት ይባላሉ።
- ሁለትነት - እሚለው አዕምሮ ከሰውነት (አንጎል) ተለይቶ ህልው ነው (ይኖራል)።
- ቁስ አካላዊነት - እሚለው አዕምሮ የአንጎል ሴሎች ተግባር ውጤት ነው።
- ምናባዊነት - እሚለው አዕምሮ ብቻ ህልው ነው። አንጎልም ሆነ ሌላ ቁስ አካል የአእምሮ ቅዠት ውጤት ነው የሚል ነው።
ከሳይንስ አንጻር አእምሮና አንጎል ይገናኛሉ ተብለው ሲታመን ለዚህ እንደ ዋና ማስረጃ ሆኖ የሚቀርበው በተጨባጩ የአንጎል ክፍሎች ላይ የሚደርስ ጉዳት በአእምሮ (አስተሳሰብ) ላይ የሚያመጣው ለውጥ ነው። ሌላው ተጠቃሽ መረጃ አንድ አንድ መድሃኒቶች በአእምሮ ላይ የሚያመጡት ለውጦች ናቸው።