ደማስቆ
ደማስቆ (ወይም ደማስቆስ፤ አረብኛ፦ دمشق) የሶርያ ዋና ከተማ ነው።
የሚኖርበት የህዝብ ቁጥር የአካባቢውን ኗሪ ሲጨምር 2,381,800 ሆኖ ሲገመት የራሱ የከተማው ኗሪ ቁጥር ደግሞ 1,861,900 ሆኖ ይገመታል። ከተማው 33°30′ ሰሜን ኬክሮስ እና 36°19′ ምሥራቅ ኬንትሮስ ላይ ተቀምጦ ይገኛል።
በአንዳንድ ሊቃውንት ዘንድ፣ ደማስቆ ከሁሉ ይልቅ ረጅሙ እድሜ ያለው ከተማ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘንድ በአብርሃም ዘመን ይገኝ ነበር። በፍላቪዩስ ዮሴፉስ ዘንድ በአራም ልጅ በዑፅ ተሠራ። ሚካኤል ሶርያዊው (12ኛው ክፍለ ዘመን) እና ባር ሄብራዩስ (አቡል-ፋራጅ) (13ኛው ክፍለ ዘመን) እንዳሉ ግን ዮሴፉስ ተሳተና «ሞርፎስ» ወይም «ሙሪፖስ» በተባለ ኬጢያዊ ሰው ተሠርቶ ነበር።
ደማስቆ በኤብላ በተገኙት የኤብላ ጽላቶች (2100 ዓክልበ. ግድም) «ደማሽኪ» ተብሎ ይጠቀሳል። የሁክሶስ ሕዝብ በ17ኛ ክፍለ ዘመን ዓክልበ. ግብጽን በገዙበት ወቅት፣ ደማስቆ በአሙሩ ግዛት ውስጥ ነበር። በአማርና ደብዳቤዎች (1350 ዓክልበ. ገዳማ) ዲማስቁ ተብሎ በንጉሱ ቢርያዋዛ እንደ ተገዛ ይጻፋል። ከ1100 እስከ 740 ዓክልበ. ድረስ የአራም ከተማ-አገር ነበር። በዚያን ጊዜ የአሦር ንጉስ 3 ቴልጌልቴልፌልሶር ያዘው።
ጅምር! ይህ አጭር ጽሑፍ መሠረት ወይም መዋቅር ነው። አሁን ሊያስፋፉት ይችላሉ! |