3 ቴልጌልቴልፌልሶር (አሦርኛቱኩልቲ-አፒል-ኤሻራ) ከሚያዝያ ወር 753 ዓክልበ. ጀምሮ እስከ 735 ዓክልበ. ድረስ የአሦር ንጉሥ ነበረ።

ዙፋኑን በመንፈቅለ መንግሥት ከመያዙ አስቀድሞ፡ ስሙ ፑሉ የተባለ የካልሁ አለቃ ነበረ። (ይህም ፑሉ በአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ «ፎሐ» ተጽፎ ይገኛል።[1])

754 ዓክልበ. የአሦር ቤተ መንግሥት የተገኘበት ሠፈር ካልሁ በአመጽ ተያዘ። በድካሙ ንጉሥ 5 አሹር-ኒራሪ በደረሰው ብሔራዊ ሁከት መካከል፡ በ13 አያሩ ወር (ሚያዝያ አካባቢ) 753[2]፣ የካልሁ ጦር አለቃ ፑሉ በግፍ ተነሣና ንጉሡን አስገድሎ የዘውዱ ስም «ቱኩልቲ-አፒል-ኤሻራ» በመባል ነገሠ። (ይህም ስያሜ በዕብራይስጥና በግሪክ መንገድ በአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ቴልጌልቴልፌልሶር ተለውጧል።[3])

በመጀመርያው፣ ነጻነቱን አዋጅቶ የነበረውን ባቢሎንን ለአሦር ግዛት ለመመልስ ዘመቻ አደረገ። በመስከረም 752 ዓክልበ. ፑሉ የባቢሎንን ንጉስ ናቦናሳርን ለአሦር አስገበረው። በሚከተሉት አመታት ከኡራርቱ መንግሥትና ከኬጢያውያን ከተሞች ጋር ሲዋጋ ዘመቻዎች በሶርያ አደረገ። በ748 ዓክልበ. አርፋድንና ሐማትን ያዘ። ከዚህ በኋላ ወደ ፊንቄፊልሥጥኤም ወርሮ የእስራኤልን ንጉስ ምናሔምን 1000 መክሊት ብር አስገበረ። በ745 ዘመቻ በሜዶን (የአሁን ፋርስ) አደረጉ።

3 ቴልጌልቴልፌልሶር መንግሥት

በኋላ (740) የእስራኤል ንጉስ ፋቁሔአራም ንጉስ ረአሶን ጋራ አደጋ በይሁዳ ላይ ሲጣሉ፣ የይሁዳ ንጉሥ አካዝ የመቅደሱን ወርቅ ሰጥቶ ከቴልጌልቴልፌልሶር እርዳታ ጠየቀ። ከዚያ ቴልጌልቴልፌልሶርም ደማስቆን አጠፍቶ የአራም ሕዝብና የእስራኤል ግማሽ ሕዝብ በምርኮት ወደ ሌላ አገሮች ሰደዳቸው።

በጥቅምት 736 ዓክልበ. ቴልጌልቴልፌልሶር ወደ ባቢሎን ወርዶ ንጉሱን ናቡ-ሙኪን-ዜሪ ማረከና እራሱ «የባቢሎን ንጉስ ፑሉ» ተብሎ ዘውዱን ተጫነ። በ735 ሲሞት ልጁ ኡሉላዩ የንጉሥ ስም 5 ስልምናሶር ተብሎ ዘውድ ተጫነ።

  1. ^ መጽሐፈ ነገሥት ካልዕ 15፡19፣ መጽሐፈ ዜና መዋዕል ቀዳማዊ 5፡26
  2. ^ የአሦር ነገሥታት ዜና መዋዕሎች Archived ኖቬምበር 14, 2016 at the Wayback Machine (እንግሊዝኛ)
  3. ^ መጽሐፈ ነገሥት ካልዕ 15፡29፣ 16፡7፤ መጽሐፈ ዜና መዋዕል ቀዳማዊ 5፡6፣ 5፡26፣
    መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልዕ 28፡20
ቀዳሚው
5 አሹር-ኒራሪ
የአሦር ንጉሥ
753 – 735 ዓክልበ.
ተከታይ
5 ስልማናሶር
ቀዳሚው
ናቡ-ሙኪን-ዜሪ
የባቢሎን ንጉሥ
737 – 735 ዓክልበ.