የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር

የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር (ኢ.ደ.ማ.) ፋሺስት ኢጣሊያ በ፲፱፻፳፱ ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ያደረገውን ጭፍጨፋ ፳፫ኛው ዓመት በሚታሰብበት የካቲት ፲፪ ቀን ፲፱፻፶፪ ዓ.ም.፤ የሀገር ፍቅር ቴአትር አዳራሽ በነበረው ኪነ-ጥበባዊ መሰናዶ ተመሠረተ።

ምሥረታ እና አመራር

ለማስተካከል

ኢ.ደ.ማ.፣ በእውቅ ሰዎች እና ደራስያን ሲመራ እና ሲስተዳደር ቆይቷል። ማኅበሩን ካቋቋሙት ደራስያን መካከልም ደጃዝማች ግርማቸው ተክለ ሐዋርያት፣ ብላታ ወልደ ጊዮርጊስ ወልደ ዮሐንስ፣ አቶ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ (የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት)፣ ጸሐፌ ተውኔት መንግስቱ ለማአቤ ጉበኛ፣ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድህንለማ ፈይሳከበደ ሚካኤልጳውሎስ ኞኞን የመሳሰሉት በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ። ቀዳሚ የማኅበሩ ርዕስ ክቡር ራስ ቢትወደድ መኮንን እንዳልካቸው (በዝነኛው “አልሞትኩም ብዬ አልዋሽም” ድርሰታቸው ይታወቃሉ) ሲሆኑ ቀጥለውም ደጃዝማች ግርማቸው ተክለ ሐዋርያት ማሕበሩን መርተዋል። ብላታ ጌታዬ አስፋው ተፈራም በጸሐፊነት ተመርጠው አገልግለዋል። ማኅበሩን በልዩ-ልዩ ሥልጣነ-ወንበር ካገለገሉት ሌሎች ደግሞ በከፊሉ፦ አቶ አምደ ሚካኤል ደሳለኝ፣ አቶ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ፤ አሰፋ ገብረ ማርያም፣ ደበበ ሰይፉማሞ ውድነህ እና አሁን በፕሬዝዳንትነት እየመሩት ያሉት ጌታቸው በለጠም ይገኙበታል።

"የኢትዮጵያ ድርሰት ማኅበር (ኢደማ) ተብሎ የተቋቋመው ይህ ድርጅት፣ መጠሪያውን በ፲፱፻፸ ዓ.ም. ወደ “የኢትዮጵያ ደራስያን አንድነት ማኅበር” ከለወጠው በኋላ፣ ያሁኑን መደበኛ መጠሪያውን “የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር” (ኢደማ) ያገኘው የካቲት ፲፩ ቀን ፲፱፻፸፰ ዓ.ም. ነው።[1]

በቅርቡ በ"ፍኖተ ነፃነት" ጋዜጣ ላይ ማኅበሩን ከመሠረቱት እና በጸሐፊነትም ካገለገሉት ከብላታ ጌታዬ አስፋው ተፈራ ጋር በተደረገ ቃለ-ምልልስ እንደተዘገበው፤- ማሕብሩ ሲመሠረት በዋናነት ዓላማው አድርጎ የተነሣው «በሀገሪቷ ያሉት የጽሑፍ ቅርሶች በዋናነት ተሰባስበው እንዲታተሙና ሌሎች አዳዲስ ጸሐፍትን ለማፍራት» እንደነበር እና «የአሁኑ የሀገሪቷ ፕሬዝዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ የደራስያን ማኅበሩ ገንዘብ ያዥ በነበሩበት ጊዜ መንግሥት የመጽሐፍ ህትመትን ወጪ ¼ኛ እንዲሸፍን» አድረገዋል። ብላታ ጌታዬ አስፋው ቀጥለውም፣ «ይኸንኑ ¼ መንግሥት ይሸፍነዋል የሚባለውን ወጪ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ሕትመቱን ካከናወነ በኋላ ያልተሸጠውን ትምህርት ሚኒስቴር እንዲገዛው ተደርጐ ትምህርት ቤቶች ለሪፈረንስ (ማጣቀሻ) እንዲጠቀሙበት ይደረጋል።» ብለዋል። ንጉሠ ነገሥቱም ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ «ለመጽሐፍ ትልቅ ፍቅር ስለነበራቸውና አርአያ ለመሆን ቲያትርን እንደሚመለከቱና እንደሚገመግሙ ሁሉ ወመዘክር (ብሔራዊ ቤተ-መዛግብትና መጽሐፍት ማዕከል) በመገኘት በመጽሐፍ ሂስና ውይይት ላይ ይካፈሉ እንደነበር» ብላታ ጌታዬ አስፋው ተፈራ ገልጸዋል። ከዚህም ሌላ የብላታ ጌታዬ ትውስታ፣ በዘመኑ «የ ዩ.ኔ.ስ.ኮ. ኃላፊ የነበሩት ክቡር አቶ አካለ ወርቅ ሀብተ ወልድ ፓሪስ ለስብሰባ በተገኙበት ጊዜ ሀገራችን በየዓመቱ ፵ሺ ዶላር ለመክፈል በመስማማት ግዴታዋን ስትወጣ በአንፃሩም በአባልነታቸው በርካታ መጽሐፎችን ያገኙ እንደነበር ይመሰክራሉ» ይላል። [2]

የአባላት ደራስያንን ሥራዎች ለኅትመት እንዲበቁ ለማድረግ የሚያስችሉ ምቹ ኹኔታዎችን ከሚፈጥርባቸው ነገሮች አንዱ ከማተሚያ ቤቶች ጋራ ያለው የሥራ ትብብር እና ስምምነት ነው። በዚህም ረገድ ከአርቲስቲክ ማተሚያ ቤት በተገኘ የ፪መቶ ፶ሺ ብር ‘ተዘዋዋሪ ድጎማ’ አያሌ የተለማማጅ እና አንጋፋ ደራስያንን እና ገጣምያንን ሥራዎች ለኅትመት እንዲበቁ አድርጓል። ተመሳሳይ ስምምነቶችም ከብርሃን እና ሰላም እንዲሁም ከብራና ማተሚያ ቤቶች ጋራም እንደተደረጉ ተዘግቧል። ማተሚያ ቤቶቹ በጥሬ ገንዘብ የሚሰጡት ብር ባይኖርም ከኢ.ደ.ማ. ጋራ እስከ ተስማሙበት የገንዘብ መጠን ድረስ ከማኅበሩ ገምጋሚ ኮሚቴ አልፈው የሚመጡትን የአባላቱን ረቂቆች በነጻ ያትማሉ።

በማኅበሩ የሥራ ደንብ፣ የአንድ ደራሲ ረቂቅ የገምጋሚ ኮሚቴውን ምዘና አልፎ፤ አርትኦቱ ተሠርቶ እና ታትሞ ለገበያ ከቀረበ በኋላ ከሚያገኘው ትርፍ ላይ የአርትኦት ክፍሎ፣ ለማተሚያ ቤቱ እና ለኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር የተወሰነ ክፍያ የማድረግ ግዴታ ይኖርበታል።

 

ኢ.ደ.ማ. ካከወናቸው ዐበይት ተግባራት አንዱ በ፳፻፪ ዓ.ም. የተከበረውን የ፶ኛ ዓመት የወርቅ በዓል አጋጣሚ በማድረግና የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅትን በማስተባበር በሀዲስ አለማየሁ ፣ በከበደ ሚካኤል ፣ በሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድህን እና በስንዱ ገብሩ ምስል ያሳተማቸው የመታሠቢያ ቴምብሮች አንዱ ነው። በዚህ ትብብር “የኢትዮጵያ ደራስያን ፪ኛ ዕትም” በሚል የታተሙትና ጳጉሜ ፪ ቀን ፳፻፬ ዓ.ም. በአዲስ አበባ ቴአትርና ባህል አዳራሽ የተመረቁት ቴምብሮች ደግም ደራስያን ነጋድራስአፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ፣ ቀኝ-ጌታ ዮፍታሄ ንጉሤብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ እና አቶ ተመስገን ገብሬ ናቸው። የቴምብሮቹ ምስሎች የተነደፉት በአገኘሁ አዳነና እሸቱ ጥሩነህ ሲሆን፤ የ፳ ሳንቲም፣ የ፹ ሳንቲም፣ የአንድና ሁለት ብር ዋጋ አላቸው። [3] እነዚህ አንጋፋ ደራሲያን በኢትዮጵያ ዘመናዊ ሥነ ጽሑፍ ታሪክ ውስጥ ጉልህ እና ዘላለማዊ አሻራ የተዉ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር በግማሽ ምዕተ ዓመት ሕይወቱ ጊዜያት በርካታ ውጣ ውረዶችን አሳልፏል። አቋሙ ዘለቄታ ባለው መልክ እንዲቀጥል ለማድረግ የመጀመርያው ፕሬዝዳንት የነበሩት የ“አርዐያ” እና “የኤደኑ ጃንደረባ” መጻሕፍት ደራሲ ግርማቸው ተክለ ሐዋርያት በጊዜው በብሔራዊ ቴአትር ለተወሰነ ጊዜ ከታየው “ቴዎድሮስ” ከተሰኘው ተውኔታቸው ገቢ ላይ ፲ሺ ብር ለማኅበሩ ለግሰው እንደነበር ተዘግቧል። ሆኖም፣ ማኅበሩ በገንዘብ አቅሙ የጠነከረ ስላልነበረ በተለያዩ ጊዜያት የሥራ ክንውኑን ያልቀለጠፈ እንዳደረገው ይነገራል። ደራሲ ማሞ ውድነህ ፕሬዝዳንት በነበሩበት ወቅት የአባላቱ ቁጥር አነስተኛነትና የገቢ ምንጮቹ ደካማነት የጽሕፈት ቤቱን የቤት ኪራይ እንኳን በአግባቡ እንዳይከፍል እስከማድረግ ደርሶ ነበር።

፲፱፻፺፯ ዓ.ም. ጌታቸው በለጠን ጨምሮ አዲስ የሥራ አስፈፃሚ ቡድን ከተመረጠ በኋላ ባሉት ጊዜያት ግን የሞያ ማኅበሩ በእጅጉ እየተቀየረ መምጣቱም ይነገራል። አዲሱ የሥራ አስፈጻሚ ለብዙ ዓመታት በአዲስ አበባ ብቻ ተወስኖ የነበረውን ጽሕፈት በአጭር ጊዜ እንዲስፋፋ አድርጓል። ማኅበሩ ዛሬ በሐረር፤ በባሕር-ዳር፤ በደሴ፤ በጎንደር እና በደብረ ማርቆስ ተጨማሪ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች አሉት። የገቢ ምንጮቹንም በተለያየ መንገድ እያሰፋ ነው። ማኅበሩ የአባልነት መሥፈርት ብሎ ያስቀመጣቸው እንደ መጽሐፍ ማሳተም እና ለኅትመት ታስቦ የተጠናቀቀ ረቂቅ ጽሑፍ መኖርን ነው። በተለያዩ የኅትመት ውጤቶች ላይ ጽሑፍ የሚያቀርቡ ጸሐፍትም አባል መኾን የሚችሉበትን መስፈርትም አካቷል። እነዚህን መስፈርቶች ማሟላት የማይችል ነገር ግን አባል የመኾን ፍላጎት ያለውን ሰው ደግሞ ወርኀዊ ክፍያ እንዲከፍል በማድረግ በደጋፊ አባልነት እንዲቀጥል የሚያስችል ምቹ ኹኔታ አለው።

“ብሌን” መጽሔት

ለማስተካከል

ብሌን የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር ይፋዊ ልሳን ነች፡፡ ይች መጽሔት የመጀመሪያ ዕትሟን ገጣሚ እና ደራሲ ደበበ ሰይፉ የማኅበሩ ፕሬዝዳንት ሳለ በነሐሴ ወር ፲፱፻፹፪ ዓ.ም. ለንባብ ያበቃች ሲሆን እስከ ማኅበሩ ፶ኛው የወርቅ ዓመት ድረስ በሃያ ዓመታት በጠቅላላው ስድስት ዕትሞችን ብቻ ነው ያስነበበችው። በአዲስ ነገር ድር-ገጽ ላይ፣ “የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር ከተኛበት እየነቃ ነው” በሚል ርዕስ በቀረበው መጣጥፍ እይታ የዚች የ’ብሌን’ መጽሔት ወቅታዊነት ብቻ ሳይሆን በአቀራረብ «ዐምዶቿም ተከታታይነት እና ወጥነት አልነበራቸውም»። እንዲሁም «ይህ ዐይነቱ አቀራረብ እና ብዙዎች ተወዳጅ አካሄድ ብለው የወሰዱት በኋላ ላይ በታተሙት የብሌን መጽሔቶች ላይ መደገም አልቻለም። አንዳንዶች መጽሔቷ በሥነ ጽሑፋዊ ብስለት እያሽቆለቆለች መጥታለች ሲሉ ትችት ያቀርቡባታል። የዐምድ መለዋወጡንም እንደ ዋነኛ ችግር የሚያነሱ አልታጡም።» በማለት ይተቻል።[4]

ማጣቀሻዎች

ለማስተካከል
  1. ^ http://www.ethiopianreporter.com/pre-rep/index.php?option=com_content&view=article&id=1247:---50-----&catid=105:2009-11-13-13-47-17&Itemid=625 “የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር 50ኛ ዓመቱን የፊታችን ዓርብ ማክበር ይጀምራል”
  2. ^ "ፍኖተ ነፃነት" ፪ኛ ዓመት ቅጽ ፪ ቁ. ፰ (፳፻፬ ዓ.ም.)
  3. ^ ‘ሪፖርተር’ Ethiopian Reporter, “የአራት ደራስያን መታሰቢያ ቴምብሮች ታተሙ” 09 SEPTEMBER 2012
  4. ^ http://addisnegeronline.com/2011/03/%E1%8B%A8%E1%8A%A2%E1%89%B5%E1%8B%AE%E1%8C%B5%E1%8B%AB-%E1%8B%B0%E1%88%AB%E1%88%B5%E1%8B%AB%E1%8A%95-%E1%88%9B%E1%8A%85%E1%89%A0%E1%88%AD-%E1%8A%A8%E1%89%B0%E1%8A%9B%E1%89%A0%E1%89%B5-%E1%8A%A5/ “የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር ከተኛበት እየነቃ ነው”

ዋቢ ምንጮች

ለማስተካከል
  • AddisNeger Online, “የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር ከተኛበት እየነቃ ነው”
  • ፍኖተ ነፃነት፤ ፪ኛ ዓመት ቅጽ.፪ ቁ.፰፤ " ከ” ኮ”ና “ካ” የፈለቀች አርቲስት -“የፍቅር ጮራ” ደራሲ ማነው?፤ ማክሰኞ መስከረም ፲፮ ቀን ፳፻፬ ዓ.ም.