ደበበ ሰይፉአማርኛ ባለቅኔ ነበሩ። ሚያዚያ 16 ቀን 1992 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው ደበበ ሰይፉ ዘርፈ ብዙ የጥበብ ሰው ነው፡፡ ገጣሚ፣ ሃያሲ፣ መምህር፣ ጸሐፊ-ተውኔት፣ የሥነ-ጽሑፍ ተመራማሪ… ነው፡፡ “የብርሃን ፍቅር” እና “ለራስ የተጻፈ ደብዳቤ” የግጥም ሥብስቦቹ የተደጎሱባቸው መጻሕፍቱ ናቸው፡፡ ከዚህ ቀጥሎ ያለው መረጃ /አቀናባሪ አሉላ ከ EthioCurrent Assimba –Voice Room/ አማካኝነት /የደበበ ሰይፉን 7ኛ ዓመት የሙት ዓመት ምክንያት በማድረግ ሚያዝያ16,1999ዓ.ም የተቀናበረ ነው፡- “..ደበበ ሰይፉ ሐምሌ 5 ቀን 1942 ዓ.ም. በሲዳሞ፡ ይርጋለም ተወለደ። የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በይርጋለምና በአዲስ አበባ ኮከበ ጽባህ ትምህርት ቤቶች ተማረ። ከአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሁፍ ትምህርት ክፍል ከፍ ባለ ማዕረግ የመጅመሪያ ድግሪውን አገኘ። በእንግሊዘኛ ሥነ ጽሁፍ የማስተር ድግሪውን ተቀበለ። ከ1966 እስክ 1984 በረዳት ፕሮፌሰርነት አገለገለ። ለበርካታ ዓመታት የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር ፕሬዜዳንት ሆኖ ሰራ። በቀድሞው ኩራዝ አሳታሚ ድርጅት ያልታተሙ መፃህፍት ገምጋሚም ነበር። ከ1985 ዓ.ም. ጅምሮ ለሰባት ዓመታት ታሞ ማቀቀ። ሚያዝያ 16 ቀን 1992 ዓ.ም. በተወለደ በሃምሳ ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ። ሚያዝያ 17 ቀን 1992 ዓ.ም. ንፋስ ስልክ በሚገኘው የቅዱስ ዮሴፍ ቤተ ክርስቲያን መካነ መቃብር በድኑ አረፈ። ከተማሪነቱ አንስቶ በርካታ ግጥሞች ጽፏል። «የብርሃን ፍቅር» የተሰኘ የመጀመሪያ የግጥም መድበሉን በ1980 ዓ.ም. በኩራዝ አሳታሚ ድርጅት አሳተመ። የብርሃን ፍቅር ሁለተኛ ክፍል የሆነውንና ፦ «ለራስ የተፃፈ ደብዳቤ» የተሰኘውን መድበሉን ደግሞ በ1992 ዓ.ም. በሜጋ አሳታሚ ድርጅት ታተመ። በተውኔቱ ዘርፍ «የቲያትር ጥበብ ከፀሐፌ ተውኔቱ አንፃር» የሚለው መጽሐፉ፤ «ሳይቋጠር የተፈታ» እና «ከባህር የወጣ ዓሣ» የተሰኙት ቲያትሮቹ ቢጠቀሱ ይበቃል…ጥናታዊ ፅሁፎቹም በርካታ ናቸው።
አታልቅስ አትበሉኝ
አትሳቅስ በሉኝ
ግዴለም ከልክሉኝ፤
የፊቴን ፀዳል
አጠልሹት በከሰል፤
የግንባሬን ቆዳ
ስፉት በመደዳ፤
ጨጓራ አስመስሉት።
ግዴለም።
አትጫወት በሉኝ
ዘፈኔን ንጥቁኝ
ግዴለም።
ብቻ ፤ አታልቅስ አትበሉኝ
አትጩህ አትበሉኝ ።
ከሰባት ዓመት በፈት ደበበ ሰይፉ እንዳረፈ ሰሞን ስሙን፦ በጋዜጣ፤ በመጽሔት፤ በሬዲዮና በቴሌቪዥን ሲነሳ ሲወሳ ከርሟል። እስከዛሬም ይታወሳል። ዛሬም ሰባተኛ የሙት ዓመቱን እንዘክረዋለን። ይህን የምናደርገው ፕሮፌሰር ስለሆነ ፤ ገጣሚ ስለሆነ ፤ አንደበተ ርቱዕ ስለሆነ ፤ ፀሐፊ ተውኔት ስለሆነ ፤ ጠቢብ ስልሆነ ብቻ አይደለም ። በዛሬው ዘመን ስለሱ ተወሳ - አልተወሳ ምንም ቁም ነገር የለውም። ሳንታሮ ታኒካዋ ፅፎት ጆርጅ ጊሽ ጀር የተረጎመውን፦ “What the dead man left behind” የሚለውን ግጥም አስታውሶ ትካዜ ባሟሸው ዝምታ ማለፍም ይቻል ነበር። ነገር ግን ጋሽ ደበበ ሁሉንም «ልዩ» ነገር እንደነበር የማያውቁት እንዲያውቁት ያስፈልጋል። ጋሽ ደበበ ሁሉንም «ልዩ» ነገር ነበር። ልዩ ፕሮፌሰር፤ ልዩ ባለቅኔና ገጣሚ፤ ልዩ ተናጋሪ (ኦራተር)፤ ልዩ ተፈላሳፊ፤ ልዩ ፀሕፊ ተውኔት፤ ልዩ ጠቢብ፤ ልይ ሩህሩህና ደግ፤ ልዩ «ቅዱስ» አማፂ፤ ልዩ ልዩ ነበር።

ፍርሃት አዶከብሬ
ፍርሃት አዶከብሬ
አያ እናት አይምሬ
የቁም መቃብሬ
የቅዥት አገሬ።
ከሥጋ ከነብሴ ከደሜ ቆንጥሬ
ከአጥንቴ ሰንጥሬ፤
ምስህን ሰጥቼህ ላመልህ ገብሬ፤
ያው ነህ አንተገና
ልጓምህ አይላላ።
ትጋልበኛለህ በእሾህ በቆንጥር ላይ
ጨለማ እንደ ግራር በቅሎበት በሚታይ
አንዲት ዘሃ-ጮራ
በማትደፍርበት
እውነት - ፍቅር - ውበት
በተቀበሩበት።

ቅዱስ አማፂ ሆኖ ሳለ ከውስጡ አልነቀል ያለውን የፍርሃት ርዝራዥ በ«ፍርሃት አዶከብሬ» ውስጥ ያሳየናል። ካልፈራህ እንዴት ቅዱስ አማፂ ትሆናለህ? ትፈራለህ፤ ትደፍራለህ። ድፍረት በፍርሃትህ ልክ ነው። በፈራኸው መጠን ትደፍራለህ። የማትፈራ ከሆንክ፦ የማትደፍር ነህ። የማትደፍር ከሆንክ የማትደፈር ነህ፤ (ብዙ ጊዜ)። የማትፈራም የማትደፍርም ከሆንክ ደግሞ በድን ነህ። ቅዱስ አማፂነትህ የፍርሃትና የድፍረትህ ድምር ውጤት የሚሆንበት (አብላጫ) ጊዜ አለ። «ጋሼ ደበበ እንዴት ኮሚኒስት እንደሆነ» አንድ ስው ሲያወጋ፡- ያኔ ተማሪ ነበር አሉ። ስታዲየም ዙሪያ አንድ ምግብ ቤት ገባ። እርቦታል። ምግብ አዘዘ። የመብል አምሮት የሠራው ምራቅ በአፉ ግጥም እያለ ትንሽ «አፋዊ» ኩሬ ይሰራል። ያዘዘው ምግብ እስኪቀርብለት በመጠባበቅ ላይ እያለ አንድ ሰው በዝግታ ወደ ውስጥ ገባ። ቡትቶ ለብሷል፤ ዓይኖቹ በደረቀ ፊቱ ውስጥ ተቀርቅረዋል። እንደራበው ያስታውቃል። ተያዩ። የዓይን ግጭቱ ቁም ነገር ያዘለ ከባድ ሃሳብ ሰራ። ያ ሰው ሊናገር ከሚችለው በላይ ለጋሽ ደበበ መልዕክቱ ደረሰው፦ «እርቦኛል ፤ በልተህ ሲተርፍህ እንድትሰጠኝ» ነው ያሉት የሰውየው ዓይኖች። ጋሽ ደበበ ግን ከዚህ በላይ ገባው። አምሮት በሰራው ምራቅ ግጥም ያለ አፉ ክው አለ። የታዘዘው ምግብ እየመጣ ነበር። እፈቱ ተቀመጠ። መብሉን አየው ጋሽ ደበበ። ከመቀመጫው ተነሳ። አነሳው ምግቡን። ለሰውየው ሰጠው። መስጠት ጀምሮ መስጠቱ ከማብቃቱ በፊት በአንድ ጊዜ ሁለት ነገሮች ሆኑ…ከውጭ ግር ያሉ ቡትቶ የለበሰው ሰውዬ ጉስቁል አጃቢዎች መሻማት ጀመሩ። ይሄ አንዱ ነገር ነው። የምግብ ቤቱ ባለቤት ባለቡትቶውን ሰውዬ መቀጥቀጥ ጀመሩ፤ ይሄ ደግሞ ሌላው ነገር ነው። ምግቡ ተደፋ። ጐስቋላው ሰውዬ ደማ። ምግቡ፤ ደሙ፤ አሸዋው፤ አፈሩ፤ ጠጠሩ ሺህ ዓመት እዚያ ቦታ የቆመ ያህል ተሰማው። ተነቀሳቀሰ። ወዴት እንደሚሄድ ሳያውቅ መራመድ ጀመረ። ከዚያን ቅፅበት ጅምሮ በኮሚኒዝም ተጠመቀ። ታላቁ መብረቅ ከሰባት ዓመት በፈት አመለጠ። ትናንት ከኛ ጋር ነበር፤ ዛሬ የለም። የጊዜ ጉዳይ ነው። በጊዜ ላይ ሲፈላሰፍ የቋጠራቸው ስንኞች ስለስብዕናው የሚሰጡት ስዕል አለ።