ኦፓኛ
ኦፓኛ በኢትዮጵያ እና በደቡብ ሱዳን የሚነገር የናይሎ ሳህራዊ ቋንቋ ነው። ንኡስ የቋንቋ ቤተሰቡ በስነልሳን ምሁራን ዘንድ ኮማን ሲባል ፥ በዚህ ንኡስ የቋንቋ ቤተሰብ ስር ከኦፖ በተጨማሪ በጋምቤላ እና በቤኒ ሻንጉል ክልልሎች የሚነገረው ኮሞኛ፥ በቤኒ ሻንጉል ክልል እና በደቡብ ሱዳን የሚነገሩት ኡዱክኛ እና ደቡብ ሱዳን ውስጥ ይነገር የነበረ ጉሌ የተባለ የሞተ ቋንቋ ይካተተሉ። በተጨማሪም ጉሙዝኛም በዚሁ ንዑስ የቋንቋ ቤተሰብ ሊካተት እንደሚችል ይገመታል።
ኦፖ በዋናነት ኢትዮጵያ ውስጥ የሚነገረው በጋምቤላ ክልል፥ ኢታንግ ልዩ ወረዳ፥ ዋንኬ እና ሜራ በተባሉ ሁለት ቀበሌዎች ነው። እነዚህ ቀበሌዎች ከጋምቤላ ከተማ በስተ ሰሜን የሚገኙ ሲሆን በሰሜን ከቤኒ ሻንጉል ክልል፥ ከምዕራብ ደግሞ ከደቡብ ሱዳን ይዋሰናሉ። የኦፖኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች እራሳቸውን ኦፓ ቋንቋቸውን ደግሞ «ጣ ኦፓ» ብለው ይጠራሉ። ጣ ኦፓ ማለት «የኦፖዎች ቋንቋ» ማለት ነው።
ኦፖኛ በኢትዮጵያ ከሚነገሩና በምጥፋት ላይ ከሚገኙ ቋንቋዎች መሀል አንዱ ነው። ምንም እንኳን የትምህርትን አስፈላጊነት በሚገባ በማህበረሰቡ ውስጥ ግንዛቤ ባለመኖሩ ልጆች በበቂ ሁኔታ በስረዓተ ትምህርቱ ውስጥ እየትሳተፉ ባይሆንም በአሁን ወቅት ስርዓተ ጽህፈት ተዘጋጅቶለት፤ የማስተማሪያ መጽሀፍቶች ተዘጋጅተውለት፤ የትምህርት ቋንቋ ሆኖ ተመሪዎች እየተጠቀሙበት ይገኛል።
ኦፖዎች በጋምቤላ ክልል ከሚገኙ ብሄረስቦች መሀከል እጅግ ዝቅተኛ ቁጥር ያላችው ሲሆን አጠቃለይ ቁጥራቸውም በኢትዮጵያ ከ2500 እንደማይበልጥ ይገመታል። ለምሳሌም በ2007 እ.ኤ.አ. የተደረገው የህዝብ ቆጠራ 999 ብቻ እንደሆኑ ይገልጻል።
ኦፖዎች በዋናነት የምጣኔ ሀብታቸው የተመሰረተው በግብርና እና በዓሳ ምርት ላይ ሲሆን በተጨማሪነት የማር ምርትም ይጠቀሳል።