አዋሽ ብሔራዊ የመዝናኛ እና የዱር አራዊት ጥበቃ ክልል

የአዋሽ ብሔራዊ መዝናኛ እና የዱር አራዊት ጥበቃ ክልል፲፱፻፶፰ ዓ/ም የተመሠረተ ክልል ሲሆን ከአዲስ አበባ በስተ ምሥራቅ አቅጣጫ በ፪መቶ ፲፩ ኪሎሜትር ርቀት ፤ በአፋርና በኦሮሚያ አዋሳኝ ክልሎች ሥር ይገኛል። ይህ ክልል ሲመሠረት በ ፱፻፮ ካሬ ኪሎሜትር የቆዳ ስፋት (ቦልቶን ፲፱፻፷፰) የነበረው ቢሆንም፤ ባሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን ማስረጃ እንዳስቀመጠው የክልሉ የቆዳ ስፋት ፯መቶ ፶፮ ካሬ ኪሎ-ሜትር ነው። የክልሉ ደቡባዊ ድንበር የአዋሽ ወንዝ ሲሆን፣ የተሠየመውም በዚሁ ታላቅ ወንዝ ስም ነው። ክልሉ የብዙ ዓይነት አራዊት እና አዕዋፍ መጠለያ ከመሆኑም ባሻገር ፍል-ውሓ እና የፋንታሌ ተራራ ይገኙበታል።

የአገሪቱ የዱር አራዊት ጥበቃ ባለ-ሥልጣን ሲመሠረት ለንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት በአማካሪነት የተመደበው እንግሊዛዊ ባቀረበው ኃሣብ መሠረት የመጀመሪያው ብሔራዊ የዱር አራዊት ጥበቃ ባለ-ሥጣን ከተመሠረተ በኋላ የቅድሚያ ሥራ የተደረገው፤ በታቀዱት ክልሎች የሚገኙትን የአገሪቱን የዱር አራዊት ኃብት መጠን ማረጋገጥ ነበር። ለዚህም ሥራ ከብሪታኒያ ተመልምሎ የተቀጠረው ባለ-ሙያ እንግሊዛዊው የሥነ-ሕይወት ባለሙያ ‘ሜልቪን ቦልቶን’ (Melvin Bolton) ነበር።

የቦልቶን ዘገባ፣ክልሉ በቀድሞ ታሪኩ የነገሥታት ማደኛ ክልል እንደነበረና ለብዙ ዘመናት በራሱ መላ ሲተዳደር የቆየ እንደነበር፤ በዚህም ቆይታው አንዳንዶቹ የዱር አራዊት ጠፍተው፤ ሌሎች ደግሞ ቁጥራቸው እየመነመነ መጥቶ እንደነበር ያስረዳል። በኋላ ግን ሥፍራው በአዲስ እርሻ መስፋፋት እና የውሐ-ቦይ ልማት ምክንያት ለአደጋ እየተጋለጠ መምጣቱ በ፲፱፻፶፰ ዓ/ም አዲስ የተቋቋመው የዱር-አራዊት ጥበቃ ባለ-ሥልጣን ቀዳሚ ሥራው አድርጎ በመያዝ የክልል አስተዳዳሪና የጥበቃ ቡድን በማደራጀት ሥፍራውን ቋሚ “የብሔራዊ መዝናኛና የዱር አራዊት ጥበቃ ክልል” መደረጉን አወጀ ይላል። [1]

አራዊት እና አዕዋፍ

ለማስተካከል

የአዋሽ ብሔራዊ መዝናኛ እና የዱር አራዊት ጥበቃ ክልል የበርካታ የዱር አራዊት፤ አዕዋፋት እና የውሐ አራዊት መኖሪያ ነው። በደቡብ አዋሳኙ በሆነው የአዋሽ ወንዝ አዞ እና ጉማሬ ሲገኝበት፤ በሰሜን ክፍሉ ደግሞ ጦጣዝንጀሮ፤ እንዲሁም ጅብ እና አጋዘን ይገኙበታል።

በክልሉ ከሚገኙት የዱር አራዊት በከፊሉ፦ ጉሬዛ (Colobus )፤ ተራ ዝንጀሮ (Anubis baboons)፤ ነጭ ዝንጀሮ (Hamadryas baboons)፤ ጦጣ (Grivet monkeys ) ሳላ (Beisa Oryx)፤ የሜዳ ፍየል (Soemmerring's Gazelle)፤ ሚዳቋ (Dikdik)፤ ትልቁ የቆላ አጋዘን (Greater Kudus)፤ አምባራይሌ (lesser Kudus)፤ ከርከሮ (Warthogs)፤ ቆርኪ (Swayne’s Hartbeest ) በብዛት የሚገኙ ሲሆን አንበሣነብር፤ ጀርባ-ጥቁር እና ተራ ቀበሮዳልጋ አንበሣ (Caracals)፤ አነር (Servals ) እና የዱር ድመት ደግም አልፎ-አልፎ ይታያሉ።

ባለፉት አሥር ዓመታት ጊዜ ውስጥ በተካሄደ ምዝገባ እንደተረጋገጠው፣ በክልሉ ውስጥ ፬መቶ ፷፪ ዓይነት የወፍ ዝርያዎች ተመዝግበዋል። ከነዚህም መኻል ስድስቱ በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ የሚገኙ ናቸው። እነዚህም መንቆረ-ጥቁር ጋርደም (Black-Billed Barbet)፤ ግንደ-ቆርቁር (Golden-Backed Woodpecker)፤ ክንፈ-ነጭ የገደል-ቻት፤ ጅራተ-ረጅም ወማይ፤ ቁራ እና ጋጋኖ ናቸው። [2]

የሰው ተጽዕኖ

ለማስተካከል

በቅርቡ በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ የወጣ ዘገባ እንደጠቆመው “በሰዎች ንክኪ የተነሳ አዋሽ ፓርክ በተለይ አስቸጋሪ ሁኔታ” ላይ መሆኑን እና የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን ከአካባቢው ፰ የኦሮሚያ ክልል ቀበሌዎችና ፫ የአፋር ክልል ቀበሌዎች ማኅበረ-ሰብ እና ከአስተዳዳሪውቹ ጋር በመመካከርና በመስማማት ቁጥራቸው እየተመናመነ የመጡትን እንስሳት ቁጥር ለማሳደግ ሥፍራው እንደገና እንዲከለል ተደርጓል። [3]

  1. ^ Bolton, Melvin (1976); p 184
  2. ^ የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን፣http://www.ewca.gov.et/en/awash_national_park Archived ኤፕሪል 28, 2014 at the Wayback Machine
  3. ^ ሪፖርተር፣“አዋሽ ብሔራዊ ፓርክና ሁለት መጠለያዎች ዳግም ተከለሉ”http://www.ethiopianreporter.com/pre-rep/index.php?option=com_content&view=article&id=797:2010-01-06-07-41-20&catid=98:2009-11-13-13-41-10&Itemid=617

ዋቢ ምንጮች

ለማስተካከል
  • Bolton, Melvin; Ethipian Wildlands; Collins & Harvill Press, Lndon (1976)