አባል:Temene/ቀዳማዊው የሐዋርያው ጠመኔ መልዕክት

የሐዋርያ ጠመኔ መልዕክት ወደ እኛ ሠዎች

በትውልድ ኢትዮጲያዊ የሆንኩት ወንድማችሁ ጠመኔ፣ ምንም እንኳን በአካል ከእናንተ ተለይቼ በሐገረ ካናዳ፣ በቶሮንቶ ከተማ የምገኝ ብሆንም፣ ዕለት በዕለት ሰዓት በሰዓት ስለ እናንተ አስባለሁ።

እንኳንስ ዛሬ ሀገራችን አደጋ ላይ ሆና ይቅርና ጥንትም አብረዉን የኖሩትን ረሀብ፣ ድህነትና በሽታ እንዴት ይጠፉ ይሆን? እያልኩ ሳስብ ውዬ ማደሬን የምነግራችሁ፣ ተወልጄ ላደግሁባት ሀገሬ ያለኝን ፍቅርና ቅንዓት ይገልፅልኝ መስሎኝ ነው።

እናንት የሀገሬ ልጆች፣ በመካከላችሁ አንዳንድ የሚያሳዝኑ ነገሮች መከሰታቸዉን ሰማሁ። በእናንተ መካከል ስል እናንተ እንደኔው በአንዲት ኢትዮጲያ የምታምኑና ሰላም የሰፈነባትን፣ ዲሞክራሲ የተረጋገጠባትን ኢትዮጵያን ለማየት የምትመኙ፣ የሐይል አገዛዝን የምትቃወሙ፣ ኢትዮጵያውያንን ማለቴ ነው።

እነዛንማ፣ ከእናንተ ዉጪ ያሉትን፣ በኃይል የሚያምኑት መሣሪያቸዉን አስቀምጠው ጠረጴዛ ጋ እስኪመጡ ድረስ ከእነሱ ጋር ለመወያየት እንዴት ይቻለኛል? በፍቅርና በወንድማማች መዋደድ እንጂ በአመፃና በተኩስ አላምንምና ከእነሱ አይደለሁም።

ውድ ኢትዮጵያውያን ወንድሞቼ፣ እንደመነሻ ይሆነኝ ዘንድ ወታደራዊው መንግስት በወደቀበት አመት የወቅቱ የኢህአዴግ ጋሻጃግሬ በሐውዜን ዕልቂት መታሰቢያ ላይ ተገኝተው የተናገሩትን ልንገራችሁ።

….. ዕልቂቱ የደረሰባቸው ወገኖች፣ ዕልቂቱን ያደረሠዉን ጎሳ፣ እስካሁን እንደ አረመኔ ያዩታል። የዚያ ማህበረሰብ ስም ሲነሳባቸው፣ ቋንቋው ሲወራባቸው ወባ እንደያዘው ሰው ይንቀጠቀጣሉ...” ሲሉ ተደምጠዋል።

ጋሻጃግሬው የወቅቱ ዲሞክራሲ ሲዘፈን አቀንቃኝ ነበሩና ያ ጎሳ አማራ፣ ያ ቋንቋ አማርኛ መሆኑ ግልፅ ነበር። እኔና እናንተ ኢትዮጵያዊ ወንድሞቼ እስከምናውቀው ድረስ የሰሜን ሸዋው አማራ እንኳን ሌላውን ሊያጠቃ ቀርቶ ለራሱም ሰግቶ ገደል አፋፍ ላይ የሚኖር ሕዝብ ነው፡፤

የጎንደሩ አማራ እንኳን ሌላውጋ ሔዶ ሊነጥቅ ይቅርና እንካ ብለዉትም የማይቀበል ግድርድርና በይሉኝታ የታሰረ ሕዝብ ሲሆን፤ ጀት አብርሮ ሀውዜንን ሊደበድብ ቀርቶ ሮቢላን ብርቅ የሆነበት፣ የሰማይ ፈረስ የሚል የዋህ ገጠሬ ነው። ስለ ጎጃም እኔ ከምናገር እንግዳ ተቀባዩን የቢቸናን ሕዝብ፣ ፍልቅልቁን የቆላ ደጋ ዳሞትን፣ የደብረ ማርቆስን፣ ሰጥቶ የማያልቅበትን የቡሬን፣ የደጀንን፣ ሕዝብ ሐዶ ማየት በቂ መሰለኝ።

ጋሻጃግሬው አረመኔ የሚል ቃልም ተጠቅመዋል። አረመኔ አንድም ሀይማኖት የለሽ፣ ሁለትም ጨካኝ ማለት ነው።

የአማራን ሕዝብ ሀይማኖት የለሽ ማለታቸው ከሆነ የደብረ ሊባኖስ ገዳማት፣ የጎንደር አድባራት፣ የወሎ መቅደሳት፣ የጣና መነኮሳት እንዳይሰሙ። ላሊበላን ለአምልኮ ከአንድ ድንጋይ ያነፁ፣ ይህን አለም ትተው በጣና ቂርቆስ የመነኑ መነኮሳትን፣ ከመቶ የበለጡ የቅኔና የቅፀላ ኮሌጆችን የያዘውን ጎጃምን፣ ሀይማኖት የለሽ ቢሉ ሰይጣናቸዉም የሚታዘባቸው ይመስለኛል።

ሌላው አረመኔ ጨካኝ ማለት ነው። ከምን ተነስተው እንዲህ አሉ? ስለ ጥቁር ደም ያውቁ ይሆን? አማራው የባህሉ ባሪያ ነውና አይን ለአይን፣ ጥርስ ለጥርስ እንዲሉ ወገኑን የገደለበትን ይገላል፤ እንጂ ለገበያ የወጣ ያዉም ሴትና ሕፃናትን የሚገድል አይደለም። ሳያውቅ ሕይወት አልፎበትም ከሆነ ካሳ ለመክፈል ጉማዉን ሊሞላ እጆቹን በሠንሠለት አስሮ ከቦታ ቦታ የሚንከራተት ኮበሌ አልገጠማቸዉም መሠል። እንጂ ሰላማዊ ሕዝብን መፍጀት፣ አርጎትም አያቅ። ለዚህም አንድ ጥሩ ታሪካዊ ምሳሌ አለ። ያኔ ሀገራችን በጣሊያን ስትወረር፣ አማራው ከተማ መሐል ጥቃት ከመሰንዘር ይልቅ ራሴን ችዬ እሞታለሁ፣ ሰላማዊ ሕዝብ አላስጨርስም ብሎ ጫካ መግባቱ የሰላማዊ ሕዝብን ዕልቂት ጠልቶ አይደለምን?

በሀገሩ ጉዳይ ግን አማራው ነፍሰ-ጡር ሚስቱን ባዶ ቤት ትቶ ድንበሩን ለማስከበር እስከመሔድ ድረስ ጨካኝ ነው።

ያ ያሉት ማኅበረሰብ አማራ ካልሆነ ደሞ፣ የወታደራዊው መንግስት ጥቃት የአማራዉንም፣ የኦሮሞውንም፣ የጉራጌዉንም፣ የደቡቡንም ልጆች በየመንገዱ ረሽኗል። የኦሮሞው ልጆች በቀይ ሽብር ዱላ ተቀጥቅጠዋል። የደቡቡ ሕዝብ ልጆች ያጨዱትን ሳይሰበስቡ በሔሊኮፕተር ታፍሰዋል። የደርግ ዱላ በአንድ ብሔረሰብ ላይ ብቻ የተነጣጠረ አልነበረም።

ይመስለኛል የየሐውዜኑ መታሰቢያ ንግግር ተናጋሪ ችግራቸው አማራውንና ጨቋኝ ገዢዎቹን መለየት አለመቻላቸው ነው። እነዛ ጨካኝ ገዢዎች ማጨድ ብርቅ የሆነበትን የወሎን ገበሬ ጎተራዉን እያጠጡ፣ ሳር ያልጠገቡና ከድርቅ የተረፉትን ከሲታ ከብቶቹን ባጋቾቻቸው እያስጎተቱ ይወስዱ የነበሩ ናቸው።

የጎጃሞቹ ገዢዎች ከሚያስጎትቱት ቅቤና ሙክት ጀምሮ ወይዛዝርቱንም የማይተዉና የገበሬዉን የደረሱ ልጃገረዶች የሚያስነውሩ ነበሩ።

የጎንደር ገዢዎች ደግሞ የገበሬዉን ልጆች በድንጋይ መጫኛ መኪና ወደ ገደል የጨመሩ ናቸው። እነዚህ የአማራ ገዢዎች ጨካኝ የሆኑት በግለሰባዊ ባህሪያቸው እንጂ አማራ ስለሆኑ አይደለም።

ዛሬ ደግሞ አንዳንዶች እንደዛ እንደወያኔ ጋሻጃግሬ፣ ተመሳሳይ መርዝ እየረጩ ነው። ለመሆኑ የትግራይ ሕዝብና የኢህአዴግ ባለስልጣኖች አንድ ናቸው እንዴ?

የትግራይ ሕዝብ እስካሁን ድረስ ከጠፍር ሸበጥ አልወጣም፤ አዳፋ ልብሱን እንዳልቀየረ፣ ጎጆው የድሀ ጎጆ፣ ልጆቹ ያው ደሀ አደግ እንደሆኑ ነው የምናውቀው

የኢህአዴግ መሪዎች ግን ምንም እንኳን ለስልጣን የበቃነው በእፍኛችን ውኃ እየዘገንን፣ ጣራችን ዳሸን፣ መኝታችን የደደቢት ኮረብታዎች ነበረ ቢሉንም፣ ዛሬ ዉስኪ የሚጠጡበት መለኪያ አንዷ 300 ብር የተገዛች፣ የሚተኙት ከስዊድን በውድ ዋጋ በተገዛ አልጋ ላይ፣ መኖሪያቸው ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከውጭ ለሚመጡ እንግዶች የያዛቸው ውድ የገስት ሀውስ ቪላዎች ውስጥ ነው።

ያ የትግራይ ገበሬ ግን ከመሬቱ ጋ የሚመሳሰለዉን ጋቢ ቀይሮ አያውቅም። አልጋው ያው ቁርበቱ ነው። ዛሬም ውኃ የሚጠጣው በቅልና ዕርዳታ በተቀበለበት ጣሣ ነው ፣ሚስቱ ዉኃ ለመቅዳት ለሰዓታት መጓዟ አልተቋረጠም። የደረሰ ወንድ ልጁ ጎጆዬን ያቀናል ፣ እርፌን ይቀበለኛል፣ የሚለው ተስፋው ሞቷል።

አድዋ የወጣው የወያኔው አውራ፣ የገበሬው ስም ከአፉ የማይጠፋው ጠ/ሚ/ር ልጁን በውጭ ሀገር ሲያዝናና የአድዋው ገበሬ ልጆች ግን እዛው ከአድዋ አቧራና አፈር ጋር ይጫወታሉ። አፈር ነው መኝታቸው አፈር አፈር ነው ሽታቸው። የኢህአዴግ ባለስልጣኖች ልጆቻቸዉን ለትምህርት ወደ ሰሜን አሜሪካና ወደ አውሮፓ ሲልኩ የትግራይ ገበሬም ልጆቹ በአዲስ አበባ አውራ ጎዳናዎች እንዲለምኑ ይልካል።

እና ወንድሞቼ የትግራይን ሕዝብና በስሙ ስልጣን የያዙትን ለይተን እንይ። እነዛ የአማራዉን የበኩር ልጆች በድንጋይ መገልበጫ ገደል የጨመሩ ጨካኝ ገዢዎችንና ሕፃናት ላይ ጥይት እንዲረጭ፣ አባወራ ሌሊት ከመኝታው እንዲጎተት፣ እህት ወንድሟ እስኪገኝ እንድትታገት ትዕዛዝ ያወጡትን አጥብቀን አብረን እንቃወም፤ እንጂ

ኢትዮጲያዊ የኢትዮጲያዊ ቤት አቃጠለ የሚል ወሬ በእናንተ ዘንድ አይሰማ። ይህ እኛ የተነሳንበትም፣ የምንደርስበትም አላማችን አይደለም። እኛን ለመበታተን ለሚፈልጉ ግን በር ይከፍታል።

እንግዲህ እንደ መልዕክቴ ስለ ሀገሬ እንደናንተው እቀናለሁና ሀሳቤ ሀሳባችሁ ይሆን ዘንድ አንዳንዶች በመሀከላችሁ በሚያስነሱትን ጥፋት እንዳትተባበሯቸው ለሀገሬ ባለኝ ቅንዓትና ፍቅር አደራ እላለሁ።

ኢትዮጲያዊው ሀዋርያ ጠመኔ ነኝ ከቶሮንቶ

temenew@yahoo.ca