የቱማል ዜና መዋዕል
የቱማል ዜና መዋዕል ወይም የቱማል ጽሑፍ ለሱመር ጥንታዊ ዘመን ታሪካዊ ምንጭ ነው። በኩኔይፎርም ጽሕፈት በሱመርኛ ተጽፎ መጀመርያው ክፍል ተገኝቶ በ1906 ዓ.ም. በትርጉም ታተመ። የተረፈው ክፍል በ1947 ዓም ተገኘ።
ጽሑፉ በኒፑር ከተማ የተገኘው የሱመር ዋነኛ ቤተ መቅደስ ወይም «ቱማል» ታሪክ ይናገራል። የቱማል መቅደስ በኪሽ ንጉሥ ኤንመባራገሲ (2384 ዓክልበ. ግ.) እንደ ተመሠረተ ይላል። ከዚያ በልጁ አጋ ዘመን (2383-2375 ዓክልበ. ግ.) መቅደሱ ተለማ፤ ከዚያም ለመጀመርያው ጊዜ መቅደሱ በፍርስራሽ ወደቀ።
ከዚያ የኡር ንጉሥ መስ-አኔ-ፓዳ (2345-2314 ዓክልበ. ግ.) ቱማሉን እንዳሳደሰው ሲለን ቀደም ተከተሉ ከጊልጋመሽ በኋላ ስለ ሆነ ጊልጋመሽን እዚህ ዘልሎ ይመስላል። በመስ-አኔ-ፓዳ ልጅ መስኪአጝ-ኑና ዘመን (2314-2310 ዓክልበ. ግ.) ቱማሉ እንደ ተለማ፣ በኋላም ለ፪ኛ ጊዜ በፍርስራሽ እንደ ወደቀ ይላል።
ከዚያ በኡሩክ ንጉሥ ጊልጋመሽ (2382-2350 ዓክልበ. ግ.) እና በልጁ ኡር-ኑንጋል (2350-2345 ዓክልበ. ግ.) ዘመናት ቱማሉ ታድሶ እንደ ተለማ ይለናል። ይህ ግን ከመስ-አኔፓዳ አስቀድሞ መጠቀስ ይገባ ነበር። (እንዲሁም በአንዱ ቅጂ ቀደም-ተከተሉ ትክክለኛ ነው[1]) ከዚያም መቅደሱ እንደገና በፍርስራሽ እንደ ወደቀ ይለናል።
ከዚያ በኡር ንጉሥ ናኒ (2187-2182 ዓክልበ. ግ.) እና በልጁ መስኪአጝ-ናና (2182-2152 ዓክልበ. ግ.) ዘመናት ቱማሉ ታድሶ እንደ ተለማ ይላል፤ በኋላ መቅደሱ ለ፬ኛ ጊዘ በፍርስራሽ ወደቀ።
ከዚያ በኡር ንጉሥ ኡር-ናሙ (1984-1966 ዓክልበ. ግ.) እና በልጁ ሹልጊ (1966-1918 ዓክልበ. ግ.) ዘመናት ቱማሉ ታድሶ እንደ ተለማ ሲለን በኋላ መቅደሱ ለ፭ኛ ጊዘ በፍርስራሽ ወደቀ።
ከዚያ ከኡር ንጉሥ ሹ-ሲን (1909-1901 ዓክልበ. ግ.) እስከ ኢሲን ንጉሥ እሽቢ-ኤራ ዘመን (1878-1872 ዓክልበ. ግ.) ድረስ፣ ቱማሉ ታድሶ ተለማ።
ጽሑፉ እራሱ በእሽቢ-ኤራ ዘመን ስለ ተቀረጸ ከዚያ በኋላ መረጃ የለውም።
ዋቢ ምንጭ
ለማስተካከል- ^ http://etcsl.orinst.ox.ac.uk/cgi-bin/etcsl.cgi?text=c.2.1.3&display=Crit&charenc=&lineid=c213.1#c213.1 (ሱመርኛ)
http://etcsl.orinst.ox.ac.uk/cgi-bin/etcsl.cgi?text=t.2.1.3# Archived ሴፕቴምበር 24, 2018 at the Wayback Machine (እንግሊዝኛ)